>
5:13 pm - Thursday April 19, 3753

ወደ ኋላ እያየን ወደፊት ልንጓዝ አንችልም (ኢሳት)

“ጠላቶቻችን አይናቸው ደም ይለብሳል እንጅ እኛ አንድ ነን” ሲሉ አባገዳዎች ተናገሩ

በባህርዳር በተከሃደው የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች የምክክር መድረክ ላኢ የተገኙ አባገዳዎች ፣ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ አንድ ህዝብ መሆኑን በማውሳት፣ ጠላቶች ሁለቱ ህዝብ የተለየ ታሪክ እንዳላቸው እየነገሩ ለማጋጨት የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም ብለዋል።

ለአመታት የኦሮሞና የአማራን ህዝብ በማጋጨት ስልጣናቸውን ለማራዘም የሚሞከሩ ሃይሎች ከእንግዲህ አይሳካላቸውም በማለት መናገራቸውን የክልሉ ወኪላችን ገልጿል።

“የኦሮሞና አማራ ህዝብ አብሮ የቆየ፣ አብሮ የኖረ ተጋብቶ ተዋልዶ በሰላም የኖረ ህዝብ ነው። ጠላቶቻችን አማሮችን ‘ግብዞች’ ይላሉ፣ ኦሮሞችን ደግሞ ጠባቦች ይላሉ። እነዚህን ሁለት ህዝቦች ለማጋጨት ይፈልጋሉ። ኦሮሞ ራሱን ብቅ ሲያደርግ አማራን ሄደው ‘ ኦሮሞ መጣብህ፣ ጠፍተሃል ተነስ’ ብለው በኦሮሞ ላይ ያነሳሳሉ፤ አማሮች ደግሞ ራሳቸውን ብቅ ሲያደርጉ ‘ አማራ መጣብህ አንተን ሊያጠፋ ነው ተነስ ምን ትጠብቃለህ’ ብለው በውሸት እያነሳሱ በህዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠር ሞክረዋል። ግን አልተሳካላቸውም። ቢሆንም አንዳንድ ግጭቶችን ፈጥረዋል። ከእንግዲህ ለጠላት ግንኙነታችን የራስ ምታት ይሆንባቸዋል እንጅ ምንም ለማድረግ አይችሉም። ግንኑነታችን ይበልጥ መጠንከር አለበት።” በማለት አባገዳው ተናግረዋል “የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ሲሉ አማራ እንዲህ ነው፣ ክፉ ነው በእገሌ ላይ ጉዳት አደረሰ እያሉ ሲያወሩ የነበረውና አሁን በአይኔ ያየሁት ተለያይቶብኛል፣ ዳግም እንደተወለድኩ አይዋለሁ” በማለት ሌላው አባገዳ ስሜታቸውን ገልጸዋል “የእኛ ልጆች ይህን ሊረከቡት ይገባል፣ ትልቅ ነገር ነው” በጣም ደስ ብሎናል በማለት ስሜታቸውን የገለጹት ሌላው አባ ገዳ፣ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክራቸውን ለግሰዋል።

በዝግጅቱ ላይ የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ “የሀገራችን ህዝቦች ትናንት ለሀገራችን በጀግንነት መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩት ተቀጥረው አይደለም። ለሀገር ህይወቱን አሳልፎ የሰጠው ይህ ህዝብ ለሀገሩ ፣ለአንድነቱ ነው፡፡ትናንት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ደሙን የገበረው ለኢትዮጵያ ነው፡፡ለሀገራችን አሁንም መስራት ይጠበቅብናል፡፡ወደ ኋላ እያየን ወደፊት ልንጓዝ አንችልም፡፡ያለፈውን እንርሳው ፡፡ለሀገራችን አንድነት በጋራ እንቁም” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው የኦሮሞና የአማራን ህዝብ ላማገጨት በማህበራዊ ሚዲያዎች ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የሁለቱ ህዝብ ትስስር ከእኛ ከአመራሮች ግንዛቤ በላይ ነው ብለዋል። የኦሮሞና የአማራ ህዝብን ግንኙነት የሚያሻክሩ ቅስቀሳዎችና ታሪክን በፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት በመጠቀም የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ለማዳከም ለአመታት የተሰራ ቢሆንም የሁለቱ ህዝቦች አሁንምጠንካራ አንድነት ይዘው መቀጠላቸው ነው በማለት አክለዋል።

Filed in: Amharic