>

ፕ/ር መስፍን እና እኛ "ባለዕውቀቶቹ" (ሳምሶን ጌታቸው)

ብዙ ጊዜ አይታችሁ ከሆነ ንብ በመስተዋት የተሰራ መስኮት ያለው ቤት ትገባና እና የምትቀስመውን ቀስማ ጉዳይዋን ጨራርሳ ለመውጣት ስትፈልግ፤ በመስተዋቱ አሻግራ ወደ ‘ምታየው ብርሃን ለማለፍ በማለም ቀጥታ በርራ ከመስተዋቱ ጋር ሄዳ ትላተማለች፡፡ ትወድቃለች፡፡ እንደገና ትነሳና በመስተዋቱ አልፋ ለማለፍ ትንደረደራለች፡፡ ግን መውጣት አይቻላትም፡፡ ከላይ ወደታች ከታች ወደላይ ወደ ግራ ወደ ቀኝ መስተዋቱን አልፎ ለመብረር ባለ በሌለ ኃይሏ በጣም ትጥራለች፣ ትፋለማለች፡፡ ዝዝዝዝዝ ገጭ ዝዝዝዝዝዝ ግው ዝዝዝዝዝ….. ያቅታታል፡፡ ብስጭትጭት ትላለች፡፡ መስተዋቱ ስለማይወጋላት ነው እንጂ ልትነድፈውም ሳትፈልግ አትቀርም፡፡ “ወይኔ አምላኬ ምን ሆኛለሁ?” ሳትልም አትቀርም፣ በንብኛ፡፡

ከሁኔታዋ መስተዋቱ ለምን እንደያዛት ሳይሆን፤ በመስተዋቱ አልፎ ወደ ሚታያት የውጭው ዓለም ለምን መቀላቀል እንዳቃጣት ሳይገርማትም ግራ ሳይገባትም፣ አይቀርም፡፡ ፊት ለፊቷ ዛፉን፣ ቅጠሉን፣ ብርሃኑን፣ ቀኑን ታየዋለች፤ ክንፎቿም ይበራሉ ግን ባለችበት “ከመንጣዘዝ” ባለፈ የትም መድረስ አልቻለችም፡፡ በእልህ በሙሉ ጉልበቷ በተደጋጋሚ ከላይ እስከታች መስተዋቱን አልፋ ለመሄድ ትወድቃለች፣ ትነሳለች፣ ትታገላለች፣ ትሞክራለች፣ ትላተማለች ግን ምንም ለውጥ የለም፡፡ በዚያ ላይ ንብ በባሕርይዋ ፍጥን ፍጥን ያደርጋታል፡፡

ነገሩን በሰውኛ ስናየው፤ ከመስኮቱ በጥቂት ሴንቲ ሜትር ርቀት ወደ በሩ አቅጣጫ ብትበር በመስተዋቱ ያልተከለለ ክፍቱን መውጫ በር ማግኘት እንደምትችል በቀላሉ እንረዳለን፡፡ ግን ንቧ ደግሞ ከመስኮቱ ተነስታ ወደ በሩ መውጫ ለመሄድ፤ ብርሃን አልባ የሆነውን የቤቱን የግድግዳ ክፍል ማለፍ ይጠበቅባታል፡፡ ያቺን አንሰተኛ ብርሃን አልባዋን ቦታ ስታልፍ፣ እውነተኛውን የቤቱን መውጫ እንደምታገኘው አታውቅም ወይም አታገናዝብም፡፡ ምክንያቱም ለእሷ ትክክለኛ የመብረሪያ አቅጣጫ የበለጠው በዓይኗ የምታየው ብርሃናማው ሥፍራ፣ የመስኮቱ መስተዋት ነው፡፡ ስለሆነም ለረዥም ሰዓታት እዚያው የመስኮቱን መስተዋት ለማለፍ በመሞከር፣ በመገጫጨትና በመላተም ትቆይና በመጨረሻ በድካም ብዛት ተዝለፍልፋ ትወድቃለች፣ በዚያው ትሞታለች፡፡ ማሩም ሳይሰራ፣ ዓላማዋንም ሳታሳካ፣ ወይ ደግሞ በባሕላቸው መሠረት ቀፎ የነካ ጠላታቸውን ነድፋ የጀግና ንብ አሟሟት ሳትሞት ወጥታ የትም ትቀራለች፡፡ ታሳዝናለች፡፡ ምክንያቱም መውጫ አጥታ የመዳከሯ ነገር እኛን እኛን የዚህን ዘመን ኢትዮጵያኖችን ትመስላለችና፡፡

አንድ ነገር በተደጋጋሚ ተሞክሮ ሲከሽፍ፤ ጊዜ፣ ጉልበትና ሕይወት ብቻ እየበላ ውጤት ካላስገኘ፣ የተያያዙትን ጎዳና ትክክለኝነት መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ያልተሄደበትን መንገድ መሞከር በጣም ብዙ ጊዜ ለውጤት ያበቃል፡፡ በእርግጥ ያለተሄደበት መንገድ ባለመለስለሱ ለመጀመሪያ ተጓዦች ሲጓዙበት ሻካራ፣ አባጣ ጎርበጥባጣ፣ አድካሚና ጨለም ያለ ይሆን ይሆናል፡፡ ቢሆንም ቢሆንም…

ከብዙ ዝምታ በኋላ ሰሞኑን ታላቃችን ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ከዕድሜ የተማሩትን፣ በዕውቀት ያፈሩትን፣ በልምድ ያካበቱትን ተጠቅመው፤ ለሀገራችንና ሕዝቧ ቢሆን ይበጅ ይሆናል ያሉትን መናገራቸው ምኑ ነው እንዲያ ውርጅብኝ የሚያስወርደው? የሚያስቆጣው? በመጀመሪያ ትልቅ ሰው ያውም ታላቅ የሆነ ትልቅ ሰው፤ አንድ ነገር በሚናገርበት ጊዜ “ይሄ ሰው ምን አስቦ ነው እንዲህ የተናገረው? ምን ቢሰማው ነው እንዲህ ይሁን የሚለው?” ብሎ መጀመሪያ ከራስ ጋር መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ቀጥሎ በኃሣቡ ካልተስማሙ የተሰነዘረውን የይበጃል ኃሣብ በተጠየቅ የሚያስኬድ አለመሆኑን ለማስረዳት መጣር ነው፡፡ የራስንም አቅም የት ድረስ እንደሆነ ለመለካት ከማስቻሉም በተጨማሪ ከኃሣብ ሰንዛሪው ጋር መልክ የያዘ ውይይት ለመፈፀም ያስችላል፡፡ ኃሣቡንም አፍታቶ እንዲያብራራ ዕድል ይሰጣል፡፡ ካልሆነ ደሞ አንድን ትልቅም ታላቅም የሆነን የሀገር ሰው ለማጣጣል “እኔ ማን ነኝ?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ፌስቡክ ላይ አይደለም፣ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ስለሀገራችን የእሳቸውን የሩብ ሩብ የለፋን፣ የወጣትነት ዘመናችንን የገበርን በቁጥር ስንት እንሆናለን?

እውነት ለመናገር ፕ/ር መስፍንን ለማንጓጠጥ ቀርቶ ለማወደስም ሰፋ ያለ ብቀታ ይጠይቃል፡፡ በጣም የሚገርመው እኛ አብዛኛው ኢትዮጵያኖች በሐይማኖታችን ወይ ክርስትያኖች ወይ ሙስሊሞች እንደሆንን ይታወቃል፡፡ “ታላቅህን አክብር” የአፍ መፍቻችን፣ የሕሊና መግሪያችን፣ የሥነምግባር “ሀሁ” አችን አልነበር? ታዲያ ከየት ያመጣነው ፈሊጥ ሆኖ ነው እንዲህ ሀገር አቀፍ ዘርጣጮች ሆነን የተገኘነው? በእርግጥ የአቅመ ቢሶች እና የዕውቀት አጠሮች ሁሉ ድርጊት፤ የተሰነዘረን ኃሣብ በብርቱ ኃሣብ ከመሟገት ይልቅ በዘለፋ፣ በሽርደዳና በተራ ስድብ ለመዋጋት መሞከራቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች መብዛታቸው ነው እንጂ የሚያሳዝነው፡፡ በተሳዳቢዎች እና በአውቃለሁ ባይ ቀባጣሪዎች የተነሳ ሀገራችን ይኸው የሀገር ሽማግሌ፣ መካሪ የሌላት ሆና ቁጭ ብላለች፡፡ እስቲ እንካ ተብሎ ቢሰጠው ከምኑ ጀምሮ ወደ ምኑ እንደሚኬድ የማያውቅ ሁሉ የስድብ ጦሩን ሰብቆ አይዝ አያሲዝ ሲሆን ይገርማል፡፡ ፍርጃ ነው፡፡

ፕ/ር መስፍን በዚህ ዕድሜያቸው የሚያስዋሽ የሚያስቀጥፍ ምንም ምክንያት የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ ወይም በወጣትነታቸው ያልነበረባቸውን የሥልጣን ጥም በዚህ ዕድሜያቸው አይቀሰቀስባቸውም፡፡ በአጠቃላይ ደግሞ ፕ/ሩ የጥቅም ምላሽ ጠብቀው የሚናገሩ እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የሚናገሩት ንግግር መመርመር የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ለሀገር ሲለፋ የኖረ የሀገር ባለውለታ ሁሉ እየረገመን ማለፍ የለበትም፡፡ በዚያ መልኩ ገና ያልተወራረደ ብዙ ሂሳብ ይቀርብናል፡፡ የነበረው ስለሚበቃን ባንጨምርበት ጥሩ ነው፡፡ ፕ/ር መስፍንን አንተ ብሎ ከክብር በወረዱ ቃላት ለማጣጣል መሞከር ስድቡንና ውርደቱን እሳቸው ይዘውት አይወርዱም፡፡ ትልቅ ሰው ሲናገር በኃሣቡ ካልተስማማን ከቻልን መሞገት፣ ካልሆነ ባላዬ ማለፍ ይቻላል፡፡ ያለ ነገር አይናገርምና፡፡

በእርግጥ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ሌሎችንም የዕውቀት ዘርፎች ጨምሮ የፖለቲካ አዋቂ ምሁር ናቸው፡፡ ግን ደግሞ በእኔ ዕይታ የዘመኑ ፖለቲከኛ አይደሉም፡፡ ንግግራቸው በታላቅ ወንድምነት ስሜት ስለሆነ ለዲፕሎማሲያዊ ቃላት ብዙም የሚጨነቁ አይመስልም፡፡ ፍርጥ አድርገው ይናገራሉ፡፡ የልምምጥ ቃል እሳቸው ዘንድ የለችም፡፡ ግን ሁሉንም ነገር በጥራዝ ነጠቅነት ሳይሆን በዕውቀት ይተገብራሉ፡፡ መመርመር የእኛ ድርሻ ነው፡፡

ለሀገራችን ከምንም በላይ የዕርቅና የይቅርታ መንገድ፣ ያልተሄደበት የፖለቲካ መንገድ ነው፡፡ ለዘመናት መውጣት ካቃተን የቂም በቀል የፖለቲካ አዙሪት ለመገላገል የምንችልበት ብልሃት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ እንደው ራሷን በራሷ አቁሳላ ራሷን በራሷ የምታክም ሀገር ናት፡፡ አለቀላት በሚባልባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ አፈሯን አራግፋ ድንጋይዋን ፈነቃቅላ ቁልጭ ትላለች፡፡ የእኔ እናት! ተመሥገን ነው ሌላ ምን ይባላል፡፡ በመሆኑም የጥፋት ደጋሾቿ ሁሉ ተሸማቀውና ትዝብት ውስጥ ገብተው ቁጭ ይላሉ፡፡ ለሁሉም ግን እኛ ልጆቿ ከምናደርገው ትግል ጎን ለጎን ያልተሄደበትን የእርቅና የይቅርታን መንገድ ለመሞከር ቢያንስ በልባችን ትንሽ ክፍት ቦታ ማኖር ይጠበቅብናል፡፡ መረን ከለቀቀ ዝርጠጣ ካልተቆጠብን የሀገር ሽማግሌዎችና አዋቂዎች እያዘኑም ቢሆን ላለመሰደብ ወደ መድረክ ድርሽ አይሉም፡፡ እኛም ከገባንበት አዘቅት ለመውጣት መፍትሔ አናገኝም፡፡ ይታሰብበት፡፡

Filed in: Amharic