>
5:16 pm - Sunday May 23, 7852

ህውሀት በጽኑ የተመረዘውን የፖለቲካ ካንሰር በፓራሴታሞል እድናለሁ በሚል ቀቢጸ ተስፋ መፈራገጡን ተያይዞታል

                                                                          ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን
የኢኮኖሚ ቀውስ ህወሀትን በአፍጢሙ ሊደፋው ተቃርቧል። የፖለቲካ ግለቱ ከቤተመንግስቱ አፋፍ ተጠግቷል። የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውሶች አንድ ላይ ሲከሰቱ ደግሞ አይጣል ነው። አንዳቸው በተናጠል ቢመጡ እንኳን የመንግስት ለውጥ የማምጣት አቅማቸው ከፍተኛ ነው። እያየን ያለነው ደግሞ ሁለቱም ተያይዘውና ተደጋግፈው በፍጥነት እየገሰገሱ መሆናቸው ነው። ሌላም ቀውስ ከአጠገባቸው አለ። ማህበራዊ መናጋት። ይህም ቀውስ ስር ይዞ አድፍጧል። ለብዙዎች ይህ ወቅት የደርግን የፍጻሜ ዘመን ያስታውሳቸዋል። ወደ ኋላ ራቅ ላለው ትውልድ ደግሞ የ66ቱ አብዮት ኮፒ ሆኖባቸዋል።
የኢኮኖሚ ቀውስ
ለኢኮኖሚ ባለሙያዎች አሁን የሚታየው ቀውስ አላስገረማቸውም። ቀድሞውኑ የታመመ፡ የተበላሸ፡ በእርዳታና ብድር የተጠጋገነ፡ በሪሚተንስ ስጋና አጥንት ለብሶ የቆመ ኢኮኖሚ እንጂ በራስ አቅምና ትጋት የተገኘ የኢኮኖሚ እድገት አይደለም። የኤድመንተኑ ነዋሪ ኢኮኖሚስት ዶ/ር ሽፈራው አዲሎ እንደሚሉት በእርዳታና ብድር ተደግፎ የቆመው ኢኮኖሚ አሁን የሚደገፈው ሲያጣ ወድቋል። ብድርና እርዳታ ደርቀዋል። እዳ መክፈል የማይችለው ኢኮኖሚ ሀገሪቱን አበዳሪ አሳጥቷታል። ለህወሀት የልብ ወዳጅ የሆኑት እነቻይና ፊት መንሳት መጀመራቸው ይሰማል። የምዕራቡ ዓለምም ለእርዳታ እጁን መሰብሰብ ጀምሯል። በተለይ የትራምፕ አስተዳደር በከፍተኛ መጠን የእርዳታ ገንዘብ እንዲቀንስ በማድረጉ በሌሎች ሳምባ የሚተነፍሰው የህወሀት ኢኮኖሚ ከሞቱ አፋፍ ይጠጋ ዘንድ ግድ ሆኗል። ኢትዮጵያውያን ከባህር ማዶ ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት የውጭ ምንዛሪም አደጋ ላይ ነው። ለታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያ ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው የህወሀት ኢኮኖሚ ሁልጊዜም ”ግራ የሚያጋባ፡ ከኢኮኖሚክስ ፍልስፍና ውጭ የሆነ፡ ለኢኮኖሚስቶችም ለመረዳት እጅግ ያዳገተ ውስብስብ” ኢኮኖሚ ነው።
ሰሞኑን የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የተናገሩት የህወሀት መንግስት በቋፍ ላይ የሚገኝ ስርዓት ለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው። የታመመውን ኢኮኖሚ ለማዳን ከ700 ቢሊየን ብር በላይ(አሁን ባለው የምንዛሪ ተመን 30ቢሊየን ዶላር) ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል አሉ። እንደ ባንክ ገዢው ማስጠንቀቂያ ይህን ያህል ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ቤት ካልገባ ኢኮኖሚው ባለበት ይቆማል ሲሉ አስፈራሩ። መቆሙ ባልከፋ። ተንገዳግዶ መገንደሱን አንደበታቸው ለማውጣት አልደፈረም። እሳቸው ገንዘቡን ሲጠሩት ለምላሳቸው አልጎረበጣቸውም። 4ቢሊየን ዶላር ማግኘት አቅቶት 40 በመቶ ለመድረስ 7ዓመት የፈጀበትን የአባይ ግድብ መጨረስ ያልቻለ መንግስት አገልጋይ የሆኑት የባንኩ ገዢ 30ቢሊየን ዶላር ተመኝተዋል። ምኞት አይከለከልም። አበዳሪዎች ተሰላችተው ፊታቸውን ባዞሩበት በዚህን ወቅት የዚህን ያህል የገንዘብ መጠን ያለው ኢንቨስትመንት ከሌለ ኢኮኖሚው ይቆማል ማለታቸው አስገራሚ ነው።
የኢትዮ ቴሌኮም ስራአስኪያጅ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሰሞኑን ያቀረቡት ሪፖርትም አስደንጋጭ ነው። እንደጥገት ላም የኢትዮጵያን ህዝብ ያለተቀናቃኝ እያለበ የሚገኘው፡ የህወሀት የአፈና ተቋም በመሆን የሚያገለግለውና በህወሀቱ ም/ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔል የበላይነት የሚመራው ኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ምንዛሪ በማጣት ስራ መስራት፡ ብድር መክፈል እንዳልቻለ አስታውቋል። ህወሀቶች የገጠማቸው ፈተና እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚጠብቁትን ኢትዮ ቴሌኮምን እንኳን ሊታደጉት የሚችሉት አልሆነም። ከምንም በላይ ለስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ የሚጠቀሙበትን የአፈና ጡንቻቸውን የሚያላሽቅባቸውና በሂደትም ከስልጣን ገፍትሮ የሚጥላቸው አደጋ ነው የመጣባቸው።
የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንት ቀርጥፎ የበላው ገንዘብ 9ቢሊየን ብር መድረሱን ሰሞኑን ሰምተናል። ጋምቤላን 70 በመቶ ተቆጣጥረው በዘር መስመር ብድር በገፍ የወሰዱ የትግራይ ባለሀብቶች፡ አንድ ኩንታል እህል ሳያመርቱ፡ መቀሌና አዲስ አበባ ፎቆች ገንብተው፡ ውድ አውቶሞቢል እያሽከረከሩ ሲንፈላሰሱ ከርመው የተበደሩትን ብር ከጨረሱ በኋላ ተጨማሪ ብድር መጠየቃቸውን ስንሰማ በእርግጥ ልንገረም እንችላለን። ገደብ የለሽ ስግብስግብነታቸውንና ሃፍረተቢስነታቸውን ለሚያውቅ ግን ብዙም አይደንቀውም። የስኳሩም ተመሳሳይ ነው። 77ቢሊየን ብር የተመደበለትን የስኳር ኮርፖሬሽን በህወሀቱ አባይ ጸሀዬ አዝማችነት የህወሀት ጄነራሎች ተቀራምተው በልተውታል። 10 ስኳር ፋብሪካዎች ተገንብተው ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ የሚተርፍ የስኳር ምርት እናገኛለን እያሉ ለዓመታት ምራቅ ሲያስውጡን ከርመው በ7ቢሊየን ብር ከውጭ ስኳር መግዛታቸውን ደረታቸውን ነፍተው እየነገሩን ነው።
በሌሎች ዘርፎችም ተመሳሳይ ነው። ቀውሱ በየአቅጣጫው ነው። የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው ጠብ ያለ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት ተስኖት እየተንገታገተ ነው። በአጠቃላይ የውጭ ንግድ የኋላ ማርሽ አስገብቶ ወደ ገደል እየተመዘገዘገ ነው። የብር የመግዛት አቅምን በ15በመቶ በመቀነስ ከመጣው ጥቅም ይልቅ ያስከተለው መዘዝ ኢትዮጵያውያንን ዋጋ እያስከፈለ ነው። ኑሮ ቃላት ከሚገልጸው በላይ ተወዷል። ህዝባችን የመኖር ህልውናው አደጋ ውስጥ ወድቋል። በልቶ ማደር ብርቅ እየሆነ ነው። ረሃብና ድርቅ ዜና መሆናቸው እስኪቀር ተለምደዋል። በአንዳንድ አከባቢዎች ሰዉ የከብት መኖና ስራስር መመገብ መጀመሩን ስንሰማ ውስጣችን አልቅሷል። ሾልከው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በቅርቡ የነዳጅ ራሽን ሊጀመር ነው። የህወሀት መንግስት በመጠባበቂያ ውስጥ የሚገኘው ነዳጅ ከሁለት ወር በላይ የሚያቆየው አይደለም። እናም በኩፖን ነዳጅ ማቅረብ ይጀመራል። የመጠባበቂያ የነዳጅ ዲፖዎችን ለመሙላት የሚያስችል ግዢ ለመፈጸም የውጭ ምንዛሪ የለም። ለግል መኪና 50ሊትር ለድርጅት 70ሊትር ለታክሲዎች 100ሊትር በሳምንት በራሽን እንዲከፋፈል ውሳኔ ላይ ተደርሷል። ይህን ተከትሎ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ይከሰታል ተብሎ ከወዲሁ ተሰግቷል።
ስኳር የለም። ነዳጅ የለም። ዘይት የለም። መብራት የለም። ውሃ የለም። ከዛሬ ደግሞ ነገ ይበልጥ አይኖርም። እየተሟጠጠ ባለው የውጭ ምንዛሪ የገቡት ምርቶች ካለቁ ሌላ ምርት ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ስለሌለ ሀገሪቱ ቀጥ ትላለች። ማህበራዊ መናጋት ከወዲሁ ሀገሪቱን ምስቅልቅል እያደረጋት ነው። ስደቱ ወደ ውጭም፡ ውስጥ ለውስጥም ሆኗል። ግጭት በየቦታው ነው። ህዝቡ ተሰላችቷል። ተስፋ ቆርጧል። የሚበላው ያጣው ህዝብ መሪውን ሊበላ እያፋሸከ ነው። በአጠቃላይ አንድ ስርዓት ሲፈራርስ የሚታዩባቸው ምልክቶች ፈጠውና አግጠው በመታየት ላይ ናቸው። ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው እንደሚሉት የህወሀት መንግስት ድንገት ሊወድቅ ይችላል። የሚታዩትና እየገፉ የመጡት ክስተቶች ማዕከላዊ መንግስቱን ሊገነድሱት እንደሚችሉ ነው ብዙዎች የሚገልጹት።
የፖለቲካው ቀውስ
ህወህቶች በመቀሌ በር ዘግተው መጠዛጠዛቸውን ቀጥለዋል። የኢኮኖሚው ቀውስ አስደንግጧቸዋል። የፖለቲካ ትርምሱ ብርክ አሲዟቸዋል። ግን እጅ ለመስጠት አልፈለጉም። በድንቁርና የተሞሉ በመሆናቸው ነገን የሚያስተውል ህሊና ነስቷቸዋል። አፍንጫቸው ስር ያደፈጠውን ውድቀታቸውን ማየት አልቻሉም። በልባቸው የታመቀውን ስጋትና ጭንቀት እንደያዙ ”አልሞትንም። አልደከምንም። ገና እንኖራለን” የሚል መልዕክት ከመቀሌ ልከዋል።
በድረ ገጽ የህወሀት አፈቀላጤ የሆነው አይጋ ፎረም ስለጌቶቹ የመቀሌ ስብሰባ የነገረን በአጭሩ ”ተረጋጉ። ዝሆኖቹ ተስማምተዋል” የሚል ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቁን የሚያሳይ መግለጫ ወጥቶ በወጉም ሳናነበው እንደገና ወደ መቀሌ መግባታቸው ተነገረን። በመሃል ተቋረጠና ባለፈው ማክሰኞ ለሶስተኛ ጊዜ ቀጠለ። ዛሬ አይጋ ፎረም ”ተረጋጉ” ባለው ሰበር ዜናው አሁንም ስብሰባው እንዳልተጠናቀቀና ለቀናት እንደሚዘልቅ ጠቆም አደረገ። ለዜናው ማጀቢያም እሳትና ጭድ ናቸው የሚባሉትን አባይ ወልዱንና ደብረጺዮንን እየተሳሳቁ በ’ፍቅር’ እፍ በማለት እየተያዩ የተነሱትን ፎቶግራፍ ለጥፎ አሳይቶናል።
የህወሀት ካድሬዎችንና ደጋፊዎችን ለማረጋጋት የታለመችው የአይጋ ፎረም ‘ተረጋጉ’ ዜና ብዙ ነገሮችን ትነግረናለች። ስብሰባው በውጥረት የተሞላ አንዳንዴም የሚያስጨንቅ እንደሆነ አይጋ አልደበቀም። መሰረታዊ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ከስምምነት ላይ መደረሱንም አትቷል። አይጋ ፎርም ‘ በዚህ ስብሰባ ህወሀት ከምንጊዜውም በላይ ጠንካራ ድርጅት ሆኖ ይወጣል። በፌደራል መንግስቱ ውስጥ የሚታየውን መዝረከረክ ለማስተካከል የሚያስችል ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ መድረስ ተችሏል።’ የሚልም ቩቩዜላ ታክሎበታል።
የአይጋ ፎረምን ዜና ስናፍታታ የተወሰኑ ነገሮች ይታዩናል። ”ስብሰባው በውጥረት የተሞላ የሚያስጨንቅ…..” የሚለው ምን ማለት እንደሆነ በዝርዝር እንዲነገረን አንጠብቅም። የአይጋ ዓላማ ወገንን ማረጋጋት፡ ‘ጠላትን’ ኩም ማድረግ ስለሆነ ነው። የዝሆኖቹ ፍጥጫ ሀሜት አይደለም። ህወሀት መንደር የገባው መተራመስ ‘ጠላት’ የፈጠረው ልብወለድ አይደለም። የአደባባይ እውነት፡ ጸሀይ የሞቀው ሀቅ እንጂ። ሁለት ዋና ዋና ሃይሎች መፋጠጣቸውን ከሹክሹክታ ያለፈ ስለመሆኑ በገሃድ የሚታዩትን አንዳንድ ክስተቶች በማንሳት መግለጽ ይቻላል።
በእርግጥ ለመስማማት እየታገሉ ነው። እየመጣባቸው ያለው የህዝብ ማዕበል ሁሉንም ጠራርጎ እንደሚወስዳቸው ያውቁታል። የሚተርፍ የለም። ውድቀታቸው አንድ ላይ ነው። የጋራ ጠላት አላቸው። ያ ጠላት በቅርብ ርቀት አድፍጦ ሊሰለቅጣቸው ተዘጋጅቷል። ልዩነታቸው ከውድቀታቸው አይከፋም። የሚያጣላችው ጉዳይንና በጋራ የመጣባቸውን ጥፋት ሚዛን ላይ አስቀምጠው ማወዳደራቸው ይጠበቃል። ለጊዜው ከጥፋት የሚድኑ ከሆነ አንድ ላይ መሆንን ይመርጣሉ። ቅዝምዝሙን ለማለፍ መስማማታቸው የማይቀር ነው። በተለይ ካድሬዎቻቸውን ማረጋጋት አለባቸው። በሀገር ቤትና በውጭ የሚኖሩ የህወሀት ደጋፊዎችና አባላትን የሚያረጋጋ መልዕክት ከመቀሌ ይጠበቃል። ካድሬው በፍርሃት እየራደ ነው። አባሉ በስጋት እየተናጠ ነው። ህወሀቶች ልዩነታቸውን በልባቸው አዳፍነው የስምምነት መግለጫ ሊያወጡ ተዘጋጅተዋል።
የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሰሞኑ እንቅስቃሴዎች ከመቀሌው ”ተረጋጉ” መልዕክት ጋር የተቃኙ ናቸው። የፌደራል መንግስቱን የወላለቀ ጥርስ መልሶ ለመትከል በሚል ከመቀሌ በተላለፈ ቀጭን ትዕዛዝ ብሄራዊ የደህንነት ም/ቤት የአንድ ዓመት እቅድ ማውጣቱ ይፋ ተደርጓል። የአስቸኳይ አዋጁ ታናሽ ወንድም የሆነው ይህ እቅድ የህወሀት የመጨረሻ ተስፋ ነው ማለት ይቻላል። የፖለቲካ ቀውሱን ለማርገብ የሚቧጠጠውን ሁሉ ሊቧጥጥ የተዘጋጀው የህወሀት ቡድን በአንድ እጁ ዱላ በሌላኛው የለበጣ ለውጥ ይዞ ለመምጣት ወስኗል። የሚታሰሩ እንዳሉ ይገመታል። ከወዲሁም ሃይለማርያም ዘራፍ እንዲል ተፈልጓል። ህወሀቶች ትንፋሽ እንዳላቸው፡ ፌደራል መንግስቱ እንዳልተዳከመ’፡ ከእጃቸውም እንዳልወጣ፡ ለማሳየት እየተንደረደሩ ነው።
እነለማ መገርሳ የሚፈተኑበት ወቅት ላይ ይገኛሉ። ህወሀቶች ከመቀሌ ሲመለሱ ለመደፍጠጥ እጃቸውን እያሟሹ ያሉት በእነለማ መገርሳ ኦህዴድ ላይ ነው። የውስጥ ምንጮች እንደሚገልጹት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ የሚመራ ገልባጭ አንጃ በኦህዴድ ውስጥ እግር አብቅሎ እየተራመደ ነው። እነለማ የፈጠሩትን ኢትዮጵያዊ ስሜት የሚቀለብስ፡ ወደ ቀድሞው የዘረኝነት ቋት ውስጥ የሚወተፍ፡ በሂደትም የእነለማ መገርሳን ቡድን በማንሳት በሌላ የሚተካ ዘመቻ ውስጥ ለውስጥ ተጀምሯል። ጭራውን ቆልፎ፡ አንገቱን ደፍቶ፡ ድምጹን አጥፍቶ ያለውን የውጭ አክራሪ ቡድን የሚያነቃቃ አጀንዳ ለመክፈት ታቅዷል።
ከወዲሁ ወርቅነህ ገበየሁ በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ በእነለማ ተቃራኒ የሆነ ዲስኩር መልቀቅ ጀምሯል። እነለማ የሰቀሉትን ኢትዮጵያዊ ዓርማ በማውረድ የብሄር ታፔላ ይዞ ብቅ እንደሚል ይጠበቃል። ትልቋን ኢትዮጵያ አንስተው ”ኢትዮጵያ ሱስ ናት” የሚል አስደማሚ ንግግር በማድረግ አዲስ የአንድነት መዓዛ እንዲታጠን ያደረጉትን የኢትዮጵያን ምድር እነ ወርቅነህ በዘረኝነት ጠረን ሊያገለሙት እያሟሟቁ ናቸው። ለዚህም የአዲስ አበባን አጀንዳ አንስተዋል። ለማ መገርሳን በአዲስ አበባ የወቅቱ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ለመተካትም ታስቧል ይላሉ ምንጮች።
ህውሀት እየተፍጨረጨረ ነው። በጽኑ የታመመውን የፖለቲካ ካንሰር በፓራሴታሞል እድናለሁ በሚል ቀቢጸ ተስፋ መፈራገጡን ተያይዞታል። ከፖለቲካው ቀውስ የመዳን ተስፋው የመነመነ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። አሁን ካለው ቀውስ የበለጠ በቀጣዮቹ ቀናት፡ አልያም ሳምንታት፡ ወይም ወራት የሚኖረው ህዝባዊ ንቅናቄና አመጽ የህወሀትን ግብዓተ መሬት ሳይፈጽም የሚመለስ አይሆንም። የኤድመንተኑ ኢኮኖሚስት ዶ/ር ሽፈራው አዲሎ እንደሚሉት ፖለቲካዊ ቀውስ እንኳን ባይኖር የኢኮኖሚው ቀውስ ብቻውን የህወህትን መንግስት ይጥለዋል። በዚህ ሀሳብ ፕ/ር ጌታቸው በጋሻውም ይስማማሉ። ”በተአምርም በማይጠገነው የኢኮኖሚው ቀውስ የህወሀት መንግስት ድንገት Collapse ማድረጉ የማይቀር ነው። ፖለቲካው ሲጨመርበት ደግሞ ሞቱ ይፈጥናል”
Filed in: Amharic