>
10:07 pm - Friday October 22, 2021

ሽማግሌ የሌላት ሀገር ! (ብሩክ ይባስ)

ስንት ዘመን ተሻግርን። ስንተና ስንት መከራን ተጋፈጥን። ዛሬም መከራው በገፍና መልኩን እየቀያየረ እየተጫነን ሌላም መጣሁ መጣሁ እያለ ነው።የሚመጣው ግን ያስፈራል ህልውናን ይፈታተናል።
ሀገራችን ሁሉም ብሄር ማለት ይቻላል ለሚከሰቱ ችግሮቻችን መፍሔን መስጫ መንገድ መላ በርግጥኝንት አላቸው ብዪ አምናለሁ። “ያበሻ ነገር መርፌ ለመስራት ማረሻ መስበር ” ሆነብ እንጂ።ለችግሮቻችን መፍሔን ለማምጣት የምናመነጨው መፍትሄ በራሱ ችግር እየሆነብን መከራን እየወለደብን ተደራራቢ ችግሮችን ታቅፈናል። የሆነ ሆነና በዘመናት የሚደራረቡብን የመከራ መግተልተል መፍተሔን ሳያገኝ ድምር ውጤቱ ከምንሸከመው በላይ እየሆነ ነው።ለዚህ ነው ስነሳ ሽማግሌ የሌላት ሀገር ያልኩት።ሽማግሌዎቻችን የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ የችግሩ አካል ሆነው በማየቴ ነው። ሀግሪቷ ካሉዋት መልካም ባህል መካከል ለሚከሰቱ አለመግባባቶች እና ችግሮች ሽማግሌዎቻችን “አንተም ተው አንተም ተው” ትላንት የነበረው ይሻላል በማለት ተቆጥተው፣ መክረው፣ አስታርቀው፣ ፍቅር አልብሰው፣ ቄጤማ ጎዝጉዘው እና ሰንጋ ጥለው ይሰዱ ነበር ። ይህንን አይተናል። በነግራችን ላይ ሽማግሌዎቻችን ስል በእድሜ፣በእውቀት፣በዝና፣ በሀብት፣በስልጣን ላይ ያሉትን ሁሉ ማለቴ ነው። ክዚህ በተጨማሪ ከምልካም ትውፊታችን ጋር ተጣብቀን አለመቅረታችን ቢያሳስበኝ።
ትላንት ስለመለያየት ደፍሮ የሚናገር ትውልድ የሀግሪቷ ማህጸን አይሸክምም ነበር። ዛሬ ግን ጥቂቶች በፈጠሩት ትንሽ ዓለም የተጠለፉ ትንንሾች ይህንን እያዜሙት እያየን ወየው ጉድ አልን። ታዲያ ልዚህ ነው ሽማግሌዎቹን ለመውቀስ ያነሳሳኝ ሀገሬ መሸከም ከምትችለው በላይ የመከራ ካባ ተጭኗት ሳለ ወዴት አሉ ለማለት ቢያሰኘኝ ነው?።

ሽማግሌዎቻችን ያሉት ደግሞ እዚሁ መከራው ከተጫነው ህብረትስብ መካከል ነው። በዛ ላይ ሽማግሌዎቻችን በእድሜም በእውቀትም የገረጀፉ ናቸው ። እነዚህ የምወቅሳቸው በአብዛኛው የሚኖሩት ህብረተሰቡ ክብር በሚሰጣቸው አካባቢ ቦታዎች ነው። ለምሳሌ በሀይማኖት ተቋማት የጎሳ ስርዓት በሚከናወንባቸው ፣ማህበረሰቡ የሚያከብራቸው ተቋማት ውስጥ ። ይበልጥ በዚህ ወቀሳዮ ተቃዳሚዎቹ የሀይማኖት አዛውንቶችን ይሆናል።
ሀይማኖት በባህሪው መልካም ስነምግባር የሚሰበክበትና የሚዘወተርበት ቦታ ነው።ከምናየው በላይ ለማናየው የምንኖርነት፣ለማናየው ዓለም በምናየው ዓለም የምንሰራነት። ታዲያ ሀገሪቷ በመከራ ስትናዎጥ የሀይማኖት አዛውንቶቹ ወዴት ሄዱ? ምነውስ የራሳችሁ ጉዳይ አሉን? በርግጥ የሀገሪቷ ችግር ከገዢው ስርዓት ጋር የተገናኘ በመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት ይህንን ማለፍ ይጠይቃል። ስርዓቱ ደግሞ ይህ እንዲሆን በፍጹም አይፈልግም።እነሱም ይህን ተቀብለው ምርኩዛቸውን ተደግፈዋል።
ባለፍነው ሩብ ምዕተ ዓመት የአንድ ሀገር ዜጎች መለያየትን ስንሰብክ ሽማግሌዎቻችን ምንም አለማለታቸው እነሱም የስርዓቱ እቁብተኞች ስለሆኑ መሆኑን ከመመስከር ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም።በርግጥ ገፍተው ያልሄዱ ጥቂት ሙከራዎች አይተናል። እርስ በእርስ ስንገዳደል ለግንዘትና ለፍትሀት ከምቆም ውጪ ሌላ ምንም አለማድረጋቸው ከገዳዪች ጋር ማበር እንጂ ሌላ ምን ስያሜ ይሰጠዋል?።
እነሆ አሁን የመጨረሻው ውርደት ላይ ስንደርስም እንኳ እነሱ እቴ ! ምን ተዳቸው። መቆጣትና መገሰጽ ሲግባቸው እድሜአቸውንና እውቀታቸውን ተደግፈው ዝም ብለዋል ። ተኮር አድርጌ የሀይማኖት አባቶችን እወቅሳልሁ።ጠዋት ተነስተው ሳህታትና ማህሌት የሚያስቆሙት ለሰማዩ ቤት ንሰሀ ግባ ብለው ወንጌል የሚጠቅሱለት ህዝብ ሲገዳደልና ሲገፋፋ ዝም ማታቸው የሰማዩስ ይቀበልው ይሆን ?
ጠዋት በአዛን የሚቀሰቅሱት፣ ቁርአን የሚነግሩት ምእመን የዘር ልክፍት በያዛቸው ሲገፉ እየተመልከቱ ጆሮ ዳባ ማለት ለአላህ ይመቸው ይሆን?
አሁንም እላለሁ የቤተ ክርስትያን አዛውንቶች ከወንጌሉ በላይ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሳይግባቸው አይቀርም ። ምክንያቱም ዜጎች እየተገደሉ ስለልማት ይነግሩናል።
የመስጂዱ ሽማግሌዎች ከቁርአኑ ይልቅ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በድንብ ይተነትኑታል ማለት ይቀል ይመስለኛል።ዜጎች የስቃይ ድምጽ እያሰሙ የመንግስታችን ውጤት ይሉናል።
ህዝቡማ የማይፈልገውን ሲቃወም ዓመታ ተገደለ ፣ ዓመታት ተንገላታ። ከሽማግሌ መሪዎቹ ይልቅ ህዝቡ የተሰበከው ገብቶት ግራውን ሲመታ ቀኙን ሊሰጥ ቆሟል ። የኋላ ኋላ ግን ወየው ለእናንተ። በንግራችን ላይ በህገ መንግስቱ ላይ መንግስት በሀይማኖት ሀይማኖትም በመንግስት ጣልቃ አይገቡም ማለት ህዝብ ሲገድል ዝም በሉ ማለት አይደልም።ሁለቱም በሀገር ሁለቱም በህዝብ ነውና የሚመሩት። ከሰሞኑ የሰማነው ነገር መቼም በኢትዮጳያ ምድር ይከስታል ብዪ አስቤው አላውቅም ለዚህም ጽሁፍ መንሻ የሆነኝ ጉዳይ ይህ ነው።
የሱማሌው ክልል ፕሬዘዳንት አቶ አብዲ ኤሊ ያደራጇቸው እሳቸውን መሳይ አውሬዎች የለማ መገርሳን ሀገር ልጆች ሲያሳደዱ ተመልከትን እናም አብዲ ህዝቡን ገድሎ እና አፈናቅሎ ስላልበቃው የለማን ሀገር ልጆች አትድረሱ ማለቱ ሽማግሌዎቹን ባያማቸው እኔን አመመኝ።
ይባስኑ ትምህርት ሚኒስቴር ይህንንኑ የአትድረሱ ስብከት ማህተም አበጅቶለት እውነት ነው ለማም አብዲም ከመንደራችሁ አትውጡ ማለቱ አስፈሪ ነው። ቀጣዩ ነገርስ ?ብሎ ነው መጠየቅ። ቀጣዩማ የአብዲ እብደት ሌሎችም ላይ እየተጋባ ሁሉም አውሬ ማሰልጠን እየጀመረ መሆኑን እየሰማን ነው ። ሽፈራውና ሀይለማርያም የሲዳማ ተወላጆችን ጠልፈው ውስደው ስልጠና ሰጥተው መስደዳቸውን ስንሰማ ሌላ ምን ሊከተል ይችላል ?
ሀገራችን በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ሆና እንኳ ሽማግሌዎቹ ለጥ ብለዋል። በቃ ለጥ። እኔ እምለው እድሜ በራሱ ሰዓት ተጭኖ ሲመጣ ማለፋችን አይቀርም ከማለፋችን በፊት ግን ለሀገራችን ምንም ሳንሰራ ማለፍ አይቆጭም ይሆን? እውነትን እየተመልከትን ዝም ማለት የሰማዩ እንኳ ባይኖር ህሊና አይጠዘጥዝም።ዜጋ ሲገድል፣ሲታሰርና ሲሳደድ መመልከት የጽድቅ መለኪያ ይሆን? ስላልገባኝ ነው።
እንግዲህ ሀግሪቷን ከምጧ ለመገላገል ሽማግሌዎች ትልቁን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።አሁንም ስላልረፈደ። ሌሎቻችንም የምንችልውን በማድረግ የተኙትን በመቀስቀስ ቀዳዳችንን መስፋት አለብን። የአብዲ አይነቶቹ ዳግም አንዳይወለዱ/ህወቶች የአብዲን አይነት ብቻ ስለሚወልዱ/ ማለቴ ነው። ዘረኞችና ከፋፋዮች ከፊታችን እንዲገለሉ ጎጠኞች ቦታ እንዳይኖራቸው ትንፋሻችንን ዋጥ አድርገን ላንዴና ለመጨራሻ ግዜ አብረን መቆም ግዜው አሁን ነው። መቻቻል ይሉትን ቋንቋ ትተን ቁስላችንን መጣጋገን ይኖርብናል። ከመቻቻል በላይ ነንና ።

ለታላላቅ የሀግሪቷ ዜጎችም ጥያቄ አልኝ? ሙሁራን ልሂቃን ነን ብላችሁ የምትኮፈሱ ፣ከያኒ ነን የምትሉና የህዝብን ሙገሳ ተከናንባችሁ የምትለጠጡ ፣ በሰንደቁዋ ስም አለምን ያስደመማችሁና ህንጻ ግንብታችሁ ሌላውን ማየት የተሳናችሁ፣እድል ስጥቷችሁ የሚድያውን በራፍ ይዛችሁ አለባበስ አሳምራችሁ ከኛ በላይ ላሳር የምትሉ። የሞተ፣እየታሰረ፣እየተገረፈ፣እየተሳደደ ያለው ይህ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ የሚሞተው ሚሊዮን ህዝብ አያስጨንቃችሁም ? በርግጥ ከህዝብ በላይ ገዢዎቻችሁን ትፈራልችሁ? ህዝብ መቼም አሸናፊ መሆኑን ግን በፍጹም እንዳትረሱ። ይህ ጥያቄ የማይመልከችሁ ጥቂቶች አላችሁ። የግዜ ጉዳይ አንጂ ክብራችሁ ይዘክራል።
በመጨረሻም የእድሜም፣ የእውቀትም የሀብትም ፣ የስልጣንም ሽማግሌዎቻችን ሀገር ማዳን ከመሞቱዋ በፊት መሆኑን በልጅ ምክር ተናግሬ ላብቃ ለድፍረቴ ይቅር በሉኝ።አብቃሁ

እምዮ ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር።

Filed in: Amharic