>
6:19 pm - Wednesday December 8, 2021

''በጨለማዋ አህጉር'' ዋሻ ጭላንጭል ብርሃን ይታያልን? ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም (ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ)

በየጊዜው ተስፋቢስነቷ እየጨመረ የመጣው የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታአወዛጋቢ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡  አንዳንዶቹ ጨለምተኝነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ በሙስና በተዘፈቁ መሪዎቿ እና ሥር በሰደደው ጥልቅ ድህነት ሳቢያ በመጥፎ ሁኔታ ላይ ተንጠልጥላ ያለች ዕድለቢስ አህጉር በማለት ሲፈርጇት ሌሎቹ ብሩህ ተስፋ የሚታያቸው ሰዎች ደግሞ በአህጉሩ ለውጥ ለማምጣት ተስፋቸውን በወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ጥለዋል፡፡ 

(የጸሐፊው ማስታወሻ፡ ይህ ትችት የአፍሪካ አህጉር ዕጣ ፈንታ በያዝነው ምዕተ ዓመት አጋማሽ ምን እንደሚመስል ለመገምገም ተዘጋጅቶ በፓምባዙካ ድረ ገጽ/Pambazuka.org   እ.ኤ.አ ሜይ 29/2014 የታተመ ነው፡፡ እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስት እና የህግ ባለሙያነቴ የእራሴን የመከራከሪያ ጭብጦች በማቅረብ የእራሴን ሙያዊ የ “ትንበያ” ግምገማ አድርጊያለሁ፡፡)

ታዋቂው የአሜሪካ የዱላ ክዋስ (ቤዝ ቦል) የነበረው ላውሬንስ ዮጊ ቤራ ቀልድ በሚመስል መልኩ ሲናገር : “ትንበያ” መስጠት አስቸጋሪ ነገር ነው በተለይም ስለወደፊቱ ብሏል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እ.ኤ.አ በ2050 እና ከዚያም በኋላ ባሉት ጊዚያት በተለይም ከጨለማው የአፍሪካ አህጉር ዋሻ መጨረሻ ብርሃን ስለመኖር እና አለመኖሩ፡፡ ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት በነበሩ ነባራዊ እውነታዎች ሁኔታ ላይ በመመስረት ስለአፍሪካ ትንበያ መስጠት ትንበያ ሰጭውን ሟርተኛ ወይም የመጥፎ አጋጣሚ ትንበያ ሰጭ የሚል ፍረጃ ያሰጠዋል፡፡ በኋላ መስታወት ሳይመለከት ለመተንበይ የሚሞክር ጠንቅዋይ ነው  ፡፡ ከዚህ አንጻር እኔ ከሁለቱም አይደለሁም፡፡

እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስት በታዋቂው የዘመናዊ የፖለቲካ ሳይንስ ‘መስራች አባት‘ ኒኮሎ ማካቬሊ ያለዉን እከተላለሁ: “ማንም የወደፊቱን ለማየት የሚፈልግ ሁሉ ያለፈውን ክስተት መዳሰስ አለበት፣ በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የወደፊት ክስተቶች ካለፈው ታሪክ ጋር ተመሳሳይነት አላቸውና”፡፡ ማካቬሊ ሰዎች ከስህተታቸው የመማር አቅም ያላቸው ለመሆናቸው ጨለምተኝነት የተንጸባረቀበት አስተሳሰብን አራምደዋል፡፡ የሰው ልጅ ከስህተቱ ሊማር  አይችልም የሚል አምነት ነበረው::

እንደ ህግ ባለሙያነቴ የምከተለው  ደግሞ “የሰው ልጅ በነፃነት እንዲኖር ተፈርዶበታል፣ ምክንያቱም ወደዚህች ዓለም ከመጣ ጀምሮ ለማንኛውም ለሚሰራው ስራ ሁሉ ሰው ኃላፊነትን ይወስዳል“ በማለት ጂን ፓውል ሳትሬ ያወጁትን ማሳሰቢያ እወስዳለሁ፡፡ ሳትሬ ከእርሳቸው በፊት በነበሩት ጃኩ ሩሶ በተባሉት ምሁር አስተሳሰብ አንፀባርቀዋል፡፡ ጃኩ ሩሶ እንዲህ በማለት አውጀዋል፣ “የሰው ልጅ ነጻ ሆኖ ተፈጥሯል፣ ግን በየትኛውም ቦታ ነፃነቱን አጥቶ ታስሯል፡፡ እራሳቸውን የሌሎች ጌታ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች እራሳቸው ከሌሎች የባሰ  የበታች ባሮች ናቸው፡፡” ሰለዚህ አፍሪካውያን/ት በህግ የበላይነት፣ ፍትሀዊ እና ትክክለኛ ህጎች ጥላ ስር ነጻ ሆነው ይኖራሉ? ወይስ ደግሞ ቀደም ሲል በቅኝ ገዥዎች እና በኋላም በእጅ አዙር ቅኝ ገዥ ጌቶቻቸው አገልጋይ ሆነው ይቀራሉ?

የያዝነውን ምዕተ ዓመት አጋማሽ የወደፊት ትንበያ በመስጠት ረገድ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ እመራለሁ፡፡ እነርሱም 1ኛ) የአፍሪካ ‘የወደፊት ታሪክ’ ‘ባለፈው ታሪክ’ የሚወሰን ነው ወይስ ደግሞ ገና ባልተወለዱት ነጻ አፍሪካውያን/ት የሚጻፍ ታሪክ ነው? 2ኛ) የሰው ልጅ መፈጠርያ የሆነችው አህጉር እ.ኤ.አ በ2050 እና ከዚያ በኋላ የነጻነት እና የሰብአዊ መብቶች መቃብር ልትሆን ትችላለችን?

የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመተንበይ የኋላ መስተዋት መመልከትን፣ የዕጣ ፈንታ ነጋሪ ጠንቋዮችን ወይም ደግሞ የሂሳብ ሞዴል ቀመሮችን አልጠቀምም፡፡ ይህንን ጉዳይ ለወደፊቱ ለፕሮፌሽናሎች እና ትንበያ ሰጭዎች እተወዋለሁ፡፡ እንደ ፖለቲካ የህግ ባለሙያነቴ እና  የሰብአዊ መብት ተሟጋችነቴ የምያሳሰበኝ ጥያቄ የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሁኔታ በደብዛዛው መስታወት ፍትህን፣ ነጻነትን፣ የህግ የበላይነትን፣ እኩልነትን እና ሌሎችን ከፍተኛ የሞራል ስብዕና የሚጠይቁትን ጉዳዮች ለመመልከት እመርጣለሁ፡፡ ለእኔ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው የህዝብ ስብጥር እና ውልደት፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ፣ የከባቢ አየር ሁኔታ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2050 እና ከዚያም በኋላ የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊወስኑ የሚችሉ የሰዎች የልማት ጉዳዮች አይደለም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ለእድገት ለደህነነት ያለምንም ጥርጥር ወሳኞች ናቸው፡፡ የእኔ የትኩረት አቅጣጫ ያነጣጠረው በአፍሪካ አህጉር የህግ የበላይነት እና መልካም አስተዳደር፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የፖለቲካ እና የአካባቢ ስነምህዳር የውድመት አማራጭ የምጻት ቀንን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ለማመላከት ነው፡፡

አንድ የኡጋንዳውያን/ት የቆየ እንዲህ የሚል የማስጠንቀቂያ አባባል አለ፣ “ወደየት እንደምትሄድ ካላወቅህ/ሽ ማንኛውም መንገድ እዚያ ያደርስሀል፡፡“ በቀጣዮቹ 50 ዓመታት አፍሪካ ወደየት ነው የምትሄደው? አፍሪካውያን/ት የማንዴላን ረዥሙን የነጻነት እና የብልጽግና ጉዞ በመከተል እ.ኤ.አ በ2050 እና ከዚያም በኋላ ግባቸውን ለማሳካት ጥረት ያደርጋሉ ወይስ ደግሞ በድህነት አዘቅት ውስጥ እና በአምባገነኖች ወጥመድ ተጠፍረው የእርስ በእርስ የጎሳ ጥላቻን፣ የኃይማኖት ጽንፈኝነትን፣ ሙስናን እና ያልተገደበ የህዝብ እድገትን የምጻት ቀናቸውን በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ? በ2050 እና ከዚያ በኋላ ተስፋ የተጣለባት አፍሪካ ለአፍሪካውያን/ት ትሆናለች ወይስ ደግሞ አዲስ የማትመች እና አሁን አንዳለችበት ሁኔታ ‘የለማኞች አህጉር’ ትሆናለች? አፍሪካ በ2050 እና ከዚያ በኋላ አሁን እንደምናውቃት አፍሪካ ልትኖር ትችላለችን? በአሁኑ ጊዜ ስለአፍሪካ መተንበይ እርባናየለሽ ተግባር ነውን?

የፖለለቲካ ሳይንቲስቱ የማካቬሊ ነብያዊ ቃላት በእኔ ጆሮ ውስጥ እንዲህ በማለት ያንሾካሹካሉ፣ “አፍሪካ ከነጭ አምባገነናዊ የቅኝ ግዛት ጭቆና በመላቀቅ ብቻ በጥቁር አፍሪካውያን/ት መዳፍ ስር ወድቃ በመማቀቅ ላይ ትገኛለች፡፡ ለ50 ዓመታት በዘለቀው የነጻነት ጉዞ አፍሪካ መረን በለቀቀ አምባገነናዊ ስርዓት፣ ሙስና፣ ድህነት፣ ጦርነት፣ የጎሳ ጥላቻ፣ ረኃብ እና በሽታ ተንሰራፍተውባት ትገኛለች፡፡ 2050 ለአፍሪካ የምጻት ቀን ነው፡፡ አፍሪካ በ “ፕሌቶ ዋሻ” ጥላውን እንጅ ብርሀንን ሳታይ እስረኛ ሆና ትቀጥላለች፡፡ የዓለም ፍጻሜ ይሆናል፡፡ አፍሪካ ብሩህ ተስፋ አይታይባትም፡፡“

እንደ የመከላከል የህግ ባለሙያነቴ የብሩህ እና የደስታ ቃላት እንዲህ በማለት በጆሮየ ላይ ያቃጭላሉ፡፡ “የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደ ጸሐይ የሚያበራ ነው፡፡ በአፍሪካ እያስገመገመ በሚመጣው የህዝቦች የነጻነት ፍላጎት ምክንያት አምባገነናዊነት እንደቆሻሻ ተጠራርጎ በታሪክ የቆሻሻ ማስቀመጫ ቅርጫት ውስጥ ይጣላል፡፡ የአንድ ፓርቲ የፈላጭ ቆራጭነት ስርዓት ተገርስሶ እውነተኛ በሆነ የብዙሀን ፓርቲ ስርዓት ይተካል፣ ኢፍትሀዊነት እና አድሏዊነት በህግ የበላይነት ይወገዳል፣ ሙስና በግልጽነት እና በተጠያቂነት ብርሀን ተንኖ ይጠፋል፣ ብልጽግና ድህነትን ያስወግዳል፣ ሰላም በጦርነት ላይ ድልን ይቀዳጃል፣ የጎሳ ጥላቻ በጎሳ ፍቅር እና መተሳሰብ ይተካል፣ ረሀብ በተትረፈረፈ ምርት ይወገዳል፣ ድርንቁርና በትምህርት ብርሀን ይገፈፋል፡፡ ከዋሻው መጨረሻ ደማቅ ብርሀን የምታበራ ጸሐይ ትታያለች፣ የህግ የበላይነት በህገ አራዊት ላይ ድልን ይቀዳጃል፡፡ ያ ጊዜ በአፍሪካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ በመሆን የመጀመሪያ ሆኖ ይመዘገባል፡፡“

ስለሆነም እ.ኤ.አ በ2050 እና በኋላ በአፍሪካ በፖለቲካ ሳይንቲስት እና በህግ ባለሙያ የተተነበዩ ጥቂት ሆኖም ግን ጠንካራ ተስፋዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንቲስት፡ እ.ኤ.አ በ2050 እና በኋላ የአፍሪካ ዋናው ችግሯ ረሀብ እና ቸነፈር ወይም ደግሞ ዓለም አቀፍ የድህነት ወትወዋቾች በሚስማማቸው መልኩ እንደሚጠሩት ‘የምግብ ዋስትና እጦት’ ነው፡፡ አሁን ያለው 1.1 ቢሊዮን የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ ብዛት በመጨመር በ2050 ቢያንስ 2.4 ቢሊዮን እንደሚሆን ይገመታል፡፡ የናይጀሪያ 174 ሚሊዮን የሆነው ህዝቧ በ2050 በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ 440 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 በዩናይትድ ስቴትስ የስታቲስቲክስ ቢሮ በቀረበው ዘገባ መሰረት ኢትዮጵያ በተለየ መልኩ የአንድ እናት የውልደት መጠን 6 ልጆች በመሆን በ2050 በዓለም አቀፍ ደረጃ በህዝብ ብዛት ከፍተኛ ከሆኑት አገሮች በ13ኛ ደረጃ ላይ ከነበረችበት በመውረድ ወደ 7ኛ ደረጃ ላይ በመሆን በሶስት እጥፍ በማደግ አሁን ካለችበት ከ91 ሚሊዮን ወደ 278 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡  በ2050 አፍሪካ በድህነት ወጥመድ (በመልካም አስተዳደር እጦት እና የኢኮኖሚ አመራር ብልሹነት ምክንያት ትውልድ አቀፍ ድህነት) ውስጥ እራሷን እንደምታገኝ እና ‘የማልቲሲያን ህልዮት’ (የህዝብ ብዛት የምግብ አቅርቦትን እንደሚበልጥ) እንደምትተገብር ይገመታል፡፡ አፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን ህዝቧን ለመመገብ የሚያስችል የምግብ እህል አቅርቦትን ለማሳደግ አትችልም፡፡ ‘የህዝብ ብዛት ቦምብ’ በምዕተ ዓመቱ አጋማሽ የአፍሪካን ህዝብ ይጭርሳል፡፡ 

የህግ ባለሙያ፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 70 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ እድሜው ከ35 ዓመት በታች ያለ ነው፡፡ የወጣቱ የህብረተሰብ ከፍል ብዛት በምዕተ ዓመቱ የበለጠ የሚጨምር ይሆናል፡፡ ለአፍሪካ ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት አስፈላጊነት እና የወጣቶች ፍላጎቶች እና እሴቶች መቀያየር ትልቅ የነበረውን ባህላዊውን የቤተሰብ ብዛት እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡ አዲሱ ትውልድ የቤተሰብ ምጣኔ እና የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች እና አገልግሎቶችን ተጠቃሚ በመሆን የውልደት መጠንን የማዘግየት ልምዶችን በስራ ላይ ያውላል፡፡ የአፍሪካ ወጣቶች የአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና የስራ ፈጠራ ዕድሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ወጣቶች የመንግስት የስልጣን ልጓምን በመጨበጥ መልካም አስተዳደርን በማጎልበት እና በማጠናከር የስርዓቱ እሴት እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ አፍሪካ እውነተኛ የሆነ የብዙሀን ፓርቲ ስርዓት ዴሞክራሲ እንዲኖራት በማድረግ በነጻነት የሚሰሩ የፍትህ አካላት፣ ዳኝነት፣ ነጻ እና ወገንተኛ ያልሆነ ፕሬስ እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት እና በየተወሰ ጊዜ የሚካሄዱ ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫዎች እንዲኖራት ያደርጋሉ፡፡ አፍሪካ በታደለቻቸው ለም መሬቶቿ እና በአህጉሩ ባሉት የውኃ ኃበቶቿ ጸጋዎች የዓለም የዳቦ ቅርጫት ትሆናለች፡፡ የአፍሪካ ብሩህ ቀኖች በመምጣት ላይ ናቸው!

የፖለቲካ ሳይንቲስት፡ ጆርጅ አይቴይ እንዲህ ብለዋል፣ “አፍሪካ ደኃ ናት ምክንያቱም ነጻ አይደለችም፡፡” በእርግጥ አፍሪካ ደኃ አይደለችም፡፡ አፍሪካ በተፈጥሮ ኃብት ረገድ በጣም ኃብታም አህጉር ናት፡፡ አፍሪካ ደኃ ናት ምክንያቱም አመራሩ በሞራል ዝቅጠት የበከተ ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ለምንም ነገር የማይውሉ አምባገነኖች፣ በሙስና የበከቱ እና እርባናየለሾች ናቸው ፡፡ በአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት አለ እየተባለ ቢነገርም (ባለፉት አስርት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ እድገት ካስመዘገቡት አስር አገሮች ውስጥ ሰባቱ ከአፍሪካ ናቸው) እየተባለ በዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች እና ለውጥ ለማምጣት ፍላጎቱ የሌላቸው የምዕራቡ ዓለም የዜና ባለሙያዎች ቢደሰኮርም ሀቁ ግን ድህነት ከ85 በመቶ በላይ ከሚሆነው እና በቀን ከአንድ ዶላር በታች እያገኘ ከሚኖረው የአፍሪካ ህዝብ ህይወት ጋር በቅርበት ተቆራኝቶ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ2050 ድህነት እና በሽታ የአፍሪካውያንን/ትን አማካይ የመኖር አድሜን ከ37 ዓመት በላይ እንዳይዘል በማድረግ ቀንሶታል፡፡ ስለሆነም አፍሪካ በድህነት እና በአምባገነናዊ የወጥመድ ድር በመተብተብ ተይዛ ትቆያለች፡፡       

የህግ ባለሙያ፡ የሚመጣው አዲሱ የአፍሪካ ትውልድ አሁን ባለው የድህነት እና አምባገነናዊ የወጥመድ አሽክላ ተጎጂ ይሆናል፡፡ በምዕራቡ ዓለም እርዳታ ተመጽዋችነት እራሳቸውን ተገዥ አያደርጉም፡፡ ይልቁንም ይህንን የለማኝነት ባህል ከናካቴው ያጠፋሉ፡፡ አፍሪካን ከችግር ለማላቀቅ እና ከድህነት ወጥመድ ውስጥ ለማውጣት ወጣቶቹ የእራሳቸውን እውቀት እና ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ፡፡ ለሚገጥማቸው ውድቀት እራሳቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በቅኝ ግዛት፣ በኢምፔሪያሊዝም፣ ኮሙኒዝም እና በሌሎች ለአፍሪካ ውድቀት ተጠያቂ ናቸው እያሉ ጊዜ በማባከን ላይ አያሳብቡም፡፡ የአፍሪካን ድህነቶች በሙሉ አያስወግዱም ሆኖም ግን በእርግጠኝነት የአፍሪካን የአመራር ሽባነት ያስወግዳሉ፡፡ ወጣቶቹ በእራስ የመተማመን ጠንካራ ስሜታቸው አፍሪካን ከድህነት እና ከአምባገነናዊ የወጥመድ አሽክላ ውስጥ መንጥቀው ያወጣሉ፡፡

የፖለቲካ ሳይንቲስት፡ “ራዕይ በሌለበት ጊዜ ህዝቦች ይጠፋሉ“ ተብሎ ተጽፏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን/ት በደቡብ ሱዳን፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ፣ በማሊ፣ በቻድ፣ በሶማሌ እና በሌሎቸም እያለቁ ነው፡፡ አፍሪካ ራዕይ በሌላቸው (ድሁር እና እውር) አምባገነን መሪዎች እየተሰቃየች ነው፡፡ የሞ ኢብራሂም የአፍሪካ አመራር ሽልማት ከዓለም ትልቁ በየዓመቱ የሚሰጥ ሽልማት (በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እና የህይወት ሙሉ ኢንዶውመንት ሁለት መቶ ሺ ዶላር)  እ.ኤ.አ በ2007 ከተመሰረተ ጀምሮ ሶስት ጊዜ ብቻ ሰጥቷል፡፡ ተሸላሚዎቹ ከሞዛምቢክ፣ ቦትስዋና እና ኬፕቬርዲ አገሮች የመጡ ናቸው፡፡ ‘አዲሱ የአፍሪካ መሪዎች ዝርያ’ እየተባለ በቢል ክሊንተን እና በቶኒ ብሌር ሲዘመርላቸው የነበሩት አምባገነኖች አንዳቸውም ከዚህ ሽልማት በር ላይ እንኳ አልደረሱም፡፡ በአፍሪካ ያለው የአመራር ቀውስ እ.ኤ.አ በ2050 እና በኋላ አፍሪካን በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ይዘፍቃታል፡፡

የሀግ ባለሙያ፡ እ.ኤ.አ በ2050 የአፍሪካ መሪዎች በሰከነ መልክ አስበው የሚሰሩ እንጅ እንደ ቀደምቶቹ ነገርን የሚያጦዙ አምባገነን መሪዎች አይሆኑም፡፡ በጥሩ ሁኔታ የተማሩ እና ስልጠና የወሰዱ (በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ወንበር ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው እንደሚገኙት መሰኛ የደናቁርት ስብስብ አይሆኑም) የሚሆኑ ናቸው፡፡ ችግሮችን ከጅምሩ ለመፍታት በሰከነ መንፈስ አስበው እና አቅደው የሚንቀሳቀሱ እንጅ እንደቀደምቶቹ ችግርን በችግር ላይ የሚቆልሉ አምባገነኖች አይሆኑም፡፡ እንደሁኔታው እራሳቸውን ከአዳዲስ ክስተቶች ጋር አጣምረው የሚሄዱ እና ከነገሮች ጋር እራሳቸውን ማዛመድ የሚችሉ ናቸው፡፡ የአዲሱን ትውልድ ድምጽ የሚሰሙ እና ፍላጎታቸውን አጥንተው የሚተገብሩ ናቸው፡፡ አእምሯቸው ለበጎ ነገሮች እና ለለውጥ ክፍት እንዲሁም የሚመጡ ችግሮችን አስቀድመው መተንበይ የሚችሉ እና መፍትሄ መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡ በ2050 እና በኋላ የአፍሪካ መሪዎች ታማኞች፣ ግልጽነትን የተላበሱ፣ ተጠያቂነት እና በእራስ የመተማመን ስሜት የሚታይባቸው እንዲሁም የፈጣሪነት እና የተነሳሽነት ስሜት የሚስተዋልባቸው ናቸው፡፡ የሚከተሉትን የማንዴላን መርሆዎች እና ትዕዛዞች ተከትለው የሚሄዱ ናቸው፡ 1ኛ) ከኋላ ሆኖ መምራት ሌሎችን ከፊት ሆነው እንዲመሩ በማድረግ በተለይም መልካም ነገሮች ከተከናወኑ በኋላ በሚደረግ የድል አከባበር ስርዓት ላይ ማሳተፍ፣ 2ኛ) አደጋ በሚኖርበት ጊዜ ከፊት ሆኖ መምራት፣ በዚህም ሳቢያ ህዝብ ይወድሀል እምነትም ይጥልብሀል፡፡

የፖለቲካ ሳይንቲስት፡ ‘አፍሪካ የጨነገፉ መንግስታት አህጉር ናት፡፡ አፍሪካ የጨነገፈች አህጉር ናት፡፡’ በምዕራቡ ዓለም የመገናኛ ብዙሀን ብዙ ነገር እየተባለ የተለያዩ ትርጉሞች ይሰጣሉ፡፡ የጨነገፉ እና በቋፍ ላይ ያሉ አገሮች የሚለው ትርጉም ያፈጠጠውን እና ያገጠጠውን እውነታ ለመደበቅ ሲባል የሚውል የማደናገሪያ ስያሜ ነው፡፡ እውነታው ግን የአፍሪካ አገሮች መሪዎች የወሮበላ ስብስቦች፣ መንታፊ ዘራፊዎች እና  በሙስና የበከቱ ሞራለቢሶች ናቸው፡፡ የአፍሪካ መንግስታት የአገሮችን ግምጃ ቤቶች እና ብሄራዊ ሀብቶች ዘርፈው ወደ ውጭ አገር ባንኮች በእራሳቸው የሂሳብ ደብተር የሚያስቀምጡ የታወቁ የማስመሰያ የወንጀለኛ ተቋሞች ናቸው፡፡ ከአፍሪካ አህጉር በስተቀር በመሬት ላይ በየትኛውም የዓለም ክፍል ቢሆን እንደ አፍሪካ ያለ በሙስና የበከተ፣ በብልሹ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አያያዝ ስርዓት የተተበተበ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ የተንሰራፋበት አይገኝም፡፡ በ2050 ሁሉም የአፍሪካ መንግስታት በሚባል መልኩ የጨነገፉ መንግስታት ወይም ደግሞ በዘራፊዎች የሚጦዙ ወሮበላ መንግስታት ይሆናሉ፡፡ ጥቂት የአፍሪካ መንግስታት በጣም ወሳኝ የሆኑ የፖለቲካ ትሩፋቶችን ለእራሳቸው ዜጎች ይሰጣሉ፡፡ ጥቂት መንግስታት በእራሳቸው ዜጎች ዓይን እይታ ህጋዊነትን ይላበሳሉ፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በእራሳቸው ዜጎች  እና በሌሎችም ይዘለፋሉ፡፡ የአፍሪካ መንግስት በዓለም ላይ የተዋረደ እና የተናቀ ይሆናል፡፡ በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር የሆኑት ጆን ማኬይ እንዲህ ብለው ነበር፣ ናይጀሪያ በመሄድ ቦኮ ሀራም በተባለ አሸባሪ ቡድን ተጠልፈው የተሰወሩትን 300 ልጃገረዶችን ከአደጋ ለማዳን “ጉድላክ ጆናታን ከሚባል አንድ ሰው የሆነ ፈቃድ መሳይ ነገር አልጠብቅም፡፡“ ጉድላክ ጆናታን ልጃገረዶች ያሉበትን ቦታ ፈልጎ ከአደጋ ሊታደጋቸው የሚችል የጦር ኃይል ገና እያሰማሩ ነው፡፡ ናይጀሪያ ልጃገረዶችን ከአደጋ ለማዳን በምታደርገው እንቅስቃሴ በእራሷ ልትወጣው ስላልቻለች የናይጀሪያን የጦር ኃይል ለመርዳት ዩናይትድ ስቴትስ ወታደር እና ሰው አልባ አውሮፕላን አሰማርታለች፡፡ ‘የታላቋ አፍሪካ’ ዕጣ ፈንታ እንግዲህ እንደዚህ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ፣ ኮትዲቯር እና ማሊ ውስጣዊ ቀውስ እና ጥላቻ በገጠማቸው ጊዜ እራሳቸውን ከእራሳቸው ለመጠበቅ ለድሮ ቅኝ ገዥዎቻቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በምዕተ ዓመቱ አጋማሽ አፍሪካ በጣም ትንንሽ ወደሆኑ ብጥስጣሽ የወሮበላ ግዛቶች (መቶ የሚሆኑ የተበጣጠሱ በወሮበላ አምባገነኖች ንጉሶች እና ባንዳዎች ቁጥጥር ስር የሆኑ መንግስታት) ትከፋፈላለች፡፡ አፍሪካ ከጨነገፉ እና በቋፍ ላይ ካሉ መንግስታት አህጉርነት ፍጹም ወደ መከኑ እና የወደቁ መንግስታት አህጉርነት ትቀየራለች፡፡

የህግ ባለሙያ፡ አፍሪካ በምዕተ ዓመቱ አጋማሽ ከአምባገነናዊነት ወደ ብዙሀን ፓርቲ ዴሞክራሲ ሽግግሯን ታጠናቅቃለች ምክንያቱም ከጥፋተኝነት ነጻ ትሆናለች፡፡ በ2050 እና በኋላ አብዛኛው የአፍሪካ ክፍል እንደ አሁኗ ቦትስዋና ይሆናል (በቦትስዋና መንግስት የ “ሳን” ህዝብን (“የጫካ ህዝቦች”) ማፈናቀሉን እና ማስፈሩን በመመርመር አውግዣለሁ)፡፡ ነጻ እና ፍትሀዊ የሆነ የብዙሀን ፓርቲ ምርጫዎች ይኖራቸዋል፡፡ የአፍሪካ ህዝቦች እንደ ጋና እና ደቡብ አፍሪካ በአቦ ሸማኔው (ወጣቱ ትውልድ) እየተመሩ የዴሞክራሲያዊ መንገድን ይከተላሉ፡፡ ጠንካራ ተቋማት ማለትም ነጻ ፍርድ ቤቶችን፣ ፕሮፌሽናል ሲቪል ሰርቫንቶችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትን ጨምሮ ይመሰረታሉ፡፡ የህግ የበላይነት ተቋማዊ ይሆናል እናም ሰብአዊ እና የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበራሉ፡፡ የአፍሪካ አዲሱ ትውልድ የግልጽነት እና የመቻቻል ባህሉን በማጠናከር እራሱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ያዘጋጃል፡፡ አህጉሩን የማህበረሰቦች ጭራ እንዲሆን ጠፍንገው የያዙትን በህግ ያለመጠየቅ ወንጀልን እና ሙስናን ያወግዛል፣

የአፍሪካ ባለብሩህ አእምሮ ባለቤቶች የሆኑት የተማሩ ወጣቶች የአህጉሩን ዕጣ ፈንታ መወሰን እና መቆጣጠር ይጀምራሉ እንዲሁም የነቀዘውን እና የነፈዘውን የቀድሞውን ትውልድ ኋላቀር ልማድ እና አሰራር ያስወግዳሉ፡፡ በምዕተ ዓመቱ አጋማሽ የግንኙነት ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ውጤታማ በሆነ መልኩ በመጠቀም የአፍሪካ አህጉር የነበረባትን የዴሞክራሲ ጉድለት ታካክሳለች፡፡ የአፍሪካ ወጣቶች ከዓለም ወጣቶች ጋር የግንኙነት መስመራቸውን በማጠናከር በመላው አፍሪካ ያልተጠበቀ እና ታላቅ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የአፍሪካ ችግሮችን ለመፍታት ከሌሎች አገሮች በትውስት እና በኩረጃ የተገኘውን እውቀት፣ ብልሀት እና የተወሳሰበ ቴክኖሎጂን መጠቀም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካውያን/ት ባህል ላይ የተመሰረቱ ወጥ ሀሳቦችን፣ ማህበረሰቦችን እና ራዕዮችን አስተባብሮ በስራ ላይ ያውላሉ፡፡ በምዕተ ዓመቱ አጋማሽ የአፍሪካ ረዥሙ፣ ቀዝቃዛው እና ጠንካራው የክረምት አምባገነንነት፣ ድህነት እና የደስታ እጦት የብሩህ አእምሮ ባለቤቶች በሆኑት ወጣቶች የአፍሪካ የጸደይ አብዮት ተካሂዶ ፍቅር የነገሰባት እና ዴሞክራሲ ያበበባት አህጉር ትሆናለች፡፡

በጨለማ ውስጥ ጨለማውን አህጉር በመስታወት ውስጥ በመመልከት ከዋሻው መጨረሻ ያለውን ብርሀን ማየት አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ የአምባገነኖች ጭጋግ፣ ሙስና እና ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም በአህጉሩ ላይ ተንሰራፍተው የሚገኙት በቀላሉ ብርሀንን ለማየት የሚፈቅዱ አይደሉም፡፡ ያልተገደበ የህዝብ እድገት፣ ቁጥጥር የማይደረግበት የከተማ እድገት፣ ስር የሰደደ ሙስና፣ በዜጎች መካከል የሚከሰት ከፍተኛ የሆነ የገቢ ልዩነት፣ አውዳሚ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ፣ መረን የለቀቀ የምሁራን ፍልሰት እና በተደጋጋሚ የሚደርስ ግጭት እና ጥላቻ ከዋሻው ጫፍ ያለውን ብርሀን ለማየት በጣም አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ጸሐይ ነገ እንደምትወጣ እርግጠኛ ሆኘ መናገር ስለምችል ለጨለማው አህጉር በ2050 እና በኋላ ብሩህ ተስፋ ይፈነጥቅበታል፡፡ ከሙያ እና ከስራ አድሏዊነት በጸዳ መልኩ ስለአፍሪካ ብሩህ ተስፋ አላሚ ሰው ነኝ፡፡ ከሁሉም በላይ በአፈጣጠሬ ተምኔታዊ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡

ለጨለማው አህጉር ከዋሻው መጨረሻ ብርሀን የለም፡፡ ብሩህ የአፍሪካ ጸሐይ ነው ያለችው!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ.ም

Filed in: Amharic