>
10:32 pm - Wednesday February 1, 2023

አህመዲን ጀበል ያቺን ሰዓት! (ሃብታሙ አያሌው)

ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በፅኑ መታመሙን ስሰማ ልቤ በእጅጉ አዘነ። ፎቶውን ሳየው ትላንት የማውቀው አህመዲንን በአይነ ህሊናዬ አስታውሼ ስሜቴ ምስቅልቅል አለ። ወዲያው ጣቶቼ ከህሊና ጓዳ ትዕዛዝ ደርሷቸው ይፅፉ ጀመር።

የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ወደ ወህኒ ቤት በተጋዙ ጊዜ እኔ በእስር አልነበርኩምና ለጥየቃ ወደ ወህኒ ቤቱ አቀናሁ። ቂሊንጦ ዞን 1 አብዛኛውን የኮሚቴውን አባላት አግኝቼ ዘየርኳቸው፤ ከዚያም ወደ ዞን 3 በማቅናት ኡስታዝ አህመዲን ጀበልን ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል አገኘሁት። ጊዜውና ሁኔታው የፈቀደልንን ያህል አውግተን ተለያየን። ብዙ ሳይቆይ ወህኒ ቤቱ አዲስ መመሪያ በማውጣት “አንድ ሰው በአንድ ቀን ከአንድ ዞን ውጪ መግባትና መጠየቅ ክልክል ነው” በማለቱ አብዛኛውን የኮሚቴውን አባላት በአንድ ጊዜ ለማግኘት ስል ዞን አንድ በማዘውተሬ ከአህመዲን ጋር ለረጅም ጊዜ ሳንገናኝ ቀረን።

ይሁን እንጂ የዘመናችን ቁልቁለት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “በዘመነ ህወሓት የኢትዬጵያ ህዝብ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባል፤ ይህውም የታሰረ ፣ ታስሮ የተፈታ ፣ ወደፊት የሚታሰር” እንዳሉት ነውና። የኔ የእስረኛ ጠያቂው የመታሰሪያ ጊዜ ሲደርስ ከአራቱ የማዕከላዊ የፍዳ ወራት በኋላ ቂሊንጦ ዞን 3 ሁለተኛ ቤት አህመዲን ጀበል እና የዞን 9ኙ ብሎገር ናትናኤል ፈለቀ (ናቲ) ወዳሉበት ክፍል መሬት ለመርገጥ ተቸግሮ በሚጎተት እግሬ ምትክ በእስረኛ ተደግፌ ገባሁ። ናቲ ደመ ግቡው ሎጋ ወጣት በጥልቅ ወንድማዊ ስሜት ተቀብሎ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ወደ ደረሰችው አንዲት ቀጭን ፍራሽ ወደተጣለባት የብረት አልጋ ወስዶ አሳረፈኝ።

ለአራት ወራት በምድራዊው ሲኦል ለቆየ ሰው ቂሊንጦ የመፈታት ያህል ነበር። ቀን እና ለሊቱ ከማይለይበት መቃብር ወጥቶ በአንዲት ጠባብ አጥር ውስጥ 1,200 እስረኛ መሃል መገኘት በእጅጉ የተለየ መልክ ነበረው። በአንዱ ክፍል ከ130 በላይ እስረኞች ይኖራል። የገደለም ፤ የዘረፈም ፤ የደፈረም፤ ስለመብት የተሟገተም ተደባልቆ በጅምላ ይታጎራል። ያ ሁሉ እስረኛ በህወሓት የጫካ ዘመን የግፍ እስር ቤት የባዶ ሽዱሽተ አስተዳዳሪና ጠባቂ በነበሩት የህወሓት ጉጅሌዎች ይጠበቃል።

ከሚተራመሰው እስረኛ መካከል ደንዳና ሰውነት ያለው በልበ ሙሉነቱ እንኳን እስረኞች አሳሪዎቹ የሚገረሙበት አንድ ወዳጄ ወደ እኔ ሲንደረደር አየሁ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ነበር። አህመዲን ሁኔታዬን ሲያይ በንዴት ጦፈ፤ በቁጭት ጥርሱን ነከሰ፤ በጀርባዬ አስተኝቶ የተጎዳ እግሬን አገላብጦ አየ፤ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ነጭነት የተቀየረው ፀጉሬን፣ ፂሜን፣ የሰውነቴን መጎስቆል ሁሉ አይቶ ሳግ አነቀው። ቁጣ እንደተሞላ ብድግ ብሎ ወጣና ብዙ ሳይዘገይ በፔርሙዝ የሞቀ ውሃ ቫዝሊን እና በእስረኛው መካከል የታወቀ አንድ ማሸት የሚችል ወጌሻ አስከትሎ ተመለሰ። ናቲ የምበላው ነገር ለማቅረብ ጉድ ጉድ እያለ ሳለ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ ከያሉበት እየተጣደፉ ወደ ተንጋለልኩበት አልጋ መጡ። በክስ መዝገብ በአንድ ካደራጁን አስር ተከሳሾች መካከል ጓዛችንን በፌስታል አንጠልጥለን ወደ ዞን ሶስት እንድንገባ የተመደብነው የሰማያዊው የሺዋስ አሰፋ፤ ወዳጄ ዮናታን ወልዴ፤ ከጎንደር ይዘው ያመጡት ተስፋዬ ተፈሪ ዙሪያውን እንደተሰየሙ ነበር። አህመዲን በናቲ አልጋ ዙሪያ መጋረጃ ጨርቀ ወጠረ…

ይቀጥላል…

Filed in: Amharic