>
2:54 pm - Saturday October 23, 2021

አህመዲን ጀበል ያቺን ሰዓት! (ክፍል 2) [ሃብታሙ አያሌው]

በቂሊንጦ ዞን 3 ሁለተኛ ቤት የተንጋለልኩባትን ቀጭን የብረት አልጋ ዙሪያዋን በአንሶላ ጋርዶ ናቲ ያዘጋጀውን ምሳ እስክንመገብ እሱ ኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ እና ኡስታዝ መሐመድ አባተ ወዳሉበት ወደ ስድስተኛ ቤት ሄደ። የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት ሆነው በህዝብ ውክልና ስለ ህዝቡ መብት በመታገላቸው ለዘግናኝ እስር እና ስቃይ ከተዳረጉት መካከል ዛሬም ለስቃያቸው መቋጫ ያልተገኘላቸው 4ቱም (አህመዲን ጀበል 2ኛ ቤት፤ አህመድ ሙስጠፋ 6ኛ ቤት፤ ካሊድ ኢብራሂም 4ኛ ቤት ፤ መሐመድ አባተ 6ኛ ቤት) ያን ጊዜም በአንድ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በሚደረግበት በዞን 3 ነበሩ። ከተፈቱት መካከል ካሚል ሸምሱ 5ኛ ቤት፣ ሼህ መከተ ሙሄ 2ኛ ቤት፣ በድሩ ሁሴን 1ኛ ቤት ምድባቸው እንደ ነበረ አስታውሳለሁ። እነዚህ ወንድሞች “መቅዱሶች” ናቸው፤ መቅዱስ ማለት በእስር ቤት ቋንቋ የምግብ አጋር ማለት ነው። አህመዲን ከመቅዱሶቹ ጋር 6ኛ ቤት ምሳ በልቶ ሲመለስ ወለሉ ላይ ምንጣፍ ጣል አድርጎ ከጎኔ ተቀመጠና ህመሜን እንዳላስብ በጥያቄ እያጣደፈ በወሬ እየጠመደ ወጌሻው የተጎዳ እግሬን እና ወገቤን በጥንቃቄ እንዲያሽ ካደረገ በኋላ ሁለት መቶ ብር ከፍሎ ጥቂት እንዳንቀላፋ እስረኛውን ከጎኔ ገለል አድርጎ ወደ ቦታው ተመለሰ።

አመሻሽ ላይ እንደ እንሰሳ በር ላይ ተሰልፈን እየተቆጠርን ከገባን በኋላ ባለ ሁለት ተከፋቹ የብረት በር በላያችን ላይ ተከረቸመ። የቅሊንጦ ወህኒ ቤት ቆይታዬን አንድ ብዬ ጀመርኩ ፤ በቤቱ ውስጥ 130 እስረኛ ይተራመሳል። የምሽቱ የሶላት ሰዓት ሲደርስ በግምት ከ50 የማያንሱ እስረኞች ሶላት ለማድረግ ቦታቸውን ያዙ፤ ግድግዳ ላይ የተለጠፈችው የህወሓት የፕሮፖጋንዳ ልሳን ትንሿ ቴሌቪዥንም ተጠረቀመች፤ እስረኛው በአንድነት ፀጥ እረጭ አለ። ሶላቱ ተጠናቅቆ ምንጣፎች እስኪነሱ የእስረኛው ፀጥታና አክብሮት የሚገርም ነበር። አህመዲን የሰገደባትን ምንጣፍ ሊያነሳ ጎንበስ ሲል ሁለት ሦስት እስረኞች የንጥቂያ ያህል ተሻምተው አነሱ። ሁኔታውን በአግራሞት እከታተል ነበር፤ የልጆቹ ሙስሊም አለመሆን ደግሞ የበለጠ ትኩረቴን ሳበው። አህመዲን ለካ የቤቱ አባወራ ነበር። ‘አቅል የለውም ከፈሱ የተጣላ ነው’ የሚባል ዱርዬ አህመዲንን በሙሉ አይን አያየውም፤ ዱርዬው ብቻ ሳይሆን የህወሓት ምድብተኛ ከሆኑት ትግሬኛ ተናጋሪ ከሆኑት ኃላፊዎች በቀር ከሌላ ከማንኛውም ብሔረሰብ የተገኙ ወታደሮችም ቢሆኑ ለአህመዲን ያላቸው አክብሮት የተለየ ነው።

ማንኛውም እስረኛ ሙስሊም ሆነ ክርስቲያን ወይም ኢ አማኒ ቢታመም፣ የሚበላው ወይም የሚጠጣው ቢቸገር፤ በዋስትና እንዲወጣ ተፈቅዶለት የሚከፍለው ቢያጣ፤ ጠበቃ አጥቶ ቢቸገር እውነት ለመናገር ከአህመዲን ቀድሞ የሚደርስ ማግኘት ዘበት ነው። አብዝቶ ስለሰው ይራራል፤ ፍርሃት ብሎ ነገር የማያውቅ ደንዳና ልብ ያለው ነው፤ ፈፅሞ እንደታሰረ ሰው ሆኖ አያውቅም፤ አሳሪዎቹን እንደሱ አብዝቶ የሚንቅም አላጋጠመኝም። በተለይ በአንድ ወቅት ኤርሚያስ ለገሰ “ምንጣፍ ጎታቹ” የሚለው የኦህዴዱን አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ በርካታ ባለ ስልጣናት ወህኒ ቤት ድረስ መጥተው “እንፍታችሁና አርፋችሁ ተቀመጡ ሲሉ ተማፅነዋል፤ ምላሹ ግን እንደጠበቁት አልነበረም። “ህዝቡ ለሰጠን አደራ መታሰር እና በእናንተ ሲዖል መሰቃየት ብቻ ሳይሆን ገና እንሞትለታለን፤ የህዝባችን ጥያቄ ሳይመለስ ሌላ ድርድር የለም። ” በአራት ነጥብ ተዘጋ።

በሌላ የቀን ጎዶሎ እንዲሁ “በድር ኢንተርናሽናል ” የሚባለው በሰሜን አሜሪካ ያለ ድርጅት ተወካይ ናቸው የተባሉ ሰዎች መጥተው “ከመንግስት ጋር በመደራደር ልናስፈታችሁ ነው ቢሉ የኮሚቴው ምላሽ የሚቀመስ አልሆነም ። “የኛ ጉዳይ መታሰርና መፈታት አይደለም፤ መንግስት የምትሉት አካል ከኛ ጋር የሚደራደረው ህዝባችን ያነሳቸውን ሶስት ጥያቄዎች በተመለከተ ነው፤ የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ እስካልተመለሰ መታሰር ብቻ ሳይሆን የሞት ፅዋም ቢሆን ከመጨለጥ በቀር ድርድር የለም። ጥያቄያችን የማይመለስ ከሆነ የመፈታት ያለመፈታት ድርድር ይዛችሁ አትምጡ። ” ቁርጥ ያለ ምላሽ ፋይል ተዘጋ።

አህመዲን በኮሚቴው ውሳኔ ጉልህ ድርሻ የነበረው ፈፅሞ መንበርከክ የማያውቅ በጓሮ ለሚደረግ ድርድር እጅ የማይሰጥ “የግምባር ስጋ” የሚባል አይነት ሰው ነው። በቀን ከሶስት ሰዓታት በላይ አይተኛም። ሰዓቱን ጠብቆ ሶላቱን ያደርሳል ከዚያም ያለ እረፍት ይፅፋል ያነብባል። መረጃ የሚያገኝበት መንገድ እንቆቅልሹ ዛሬም አልተፈታም፤ አንድ አንድ ጊዜ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ዳኞቹን ከየትኛው የመንግስት ባለስልጣን ጋር የትኛው ቢሮ ሆነው በመዝገቡ ላይ አቋም እንደያዙ ጭምር እየተናገረ ያስደነግጣቸዋል። ከፍርድ ቤት መልስ ማታ ማታ ሁል ጊዜም ስለ ውሎአችን እንመክር ነበር፤ በቋሚነት ለረጅም ጊዜ በወጌሻነት ለሚያገለግለኝ፣ መኝታ ለሚያነጥፍና ለሚያነሳልኝ፣ ቤተሰብ የሚያመጣልኝን ምግብ ወደ ማደሪያችን ለሚያስገባልኝ ለአገልግሎቱ ሁሉ በወር በመደበኛነት እየከፈለ ከህመሜ እንዳገግም የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። ከስቃዬ ሳገግም ዛሬ “ከህወሓት ሰማይ ስር” በሚል እርዕስ የታተመውን መፅሐፌን እንድጀምረው የፃፍኩት ሁለት ምዕራፍም የሚከፈለው ተከፍሎ ከወህኒ ቤቱ እንዲወጣ ከፍተኛ ሚና ነበረው።

አህመዲን በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ የሚሰጣቸው አስተያየቶች በደል ነበር ከሚል አንግል ብቻ የሚነሱ በመሆናቸው ሚዛን እንደሚጎላቸው፤ አንድ ሀገር ትላንት በዓለም በነበረው ነባራዊ ሁኔታ በተለይም በሀገር ግንባታ ወቅት ባጋጠመ ውጣ ውረድ መፃዒ እድሏን መወሰን እንደማይቻል እንደማይገባም ብዙ ጊዜ ተከራክሬዋለሁ። በተለይ የኔ የመጀመሪያው (ሀገርና ፖለቲካ) የሚለው መፅሐፌን መነሻ አድርገን ብዙ ተወያይተናል፤ ሃሳቡን ለሱ የመሰለውን ከማስረዳት ያልመሰለውን ከመሞገት በቀር ተናዳጅ ግንፍልተኛ አይደለም፤ ጆሮ ገብ ንግግሩ የማይጠገብ ለመናገር የማይቸኩል አዳማጭም ነው። በተለይ በምክንያት የሚቀርብን መከራከሪያ አዳምጦ ለመቀበል ችግር የሌለበት መሆኑ ሁሌም ያስገርመኝ ነበር።

አንድ ቀን የሀገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ የነበረውና ከመለስ ሞት በኋላ ታስሮ ቅሊንጦ እኛው ዞን የነበረውን ወልደስላሴ ወልደሚካኤልን እንዴት በጥንቃቄ ይዘን መረጃ ማግኘት እንደምንችል ተማከርን፤ በዚህ ምክር ውስጥ በአሁኑ ወቅት እዚህ አሜሪካ ተሰድዶ ያለ ያን ጊዜ ከእኛ ጋር ታስሮ የተፈታ በእኛ መዝገብ 6ኛ ተከሳሽ የነበረው ዬናታን ወልዴ እና አሁን ስሙን የማልጠቅሰው የሙስሊሙ የኮሚቴ አባል እንዲካተቱ አደረግን። ነገሩን ለመጀመር የተስማማነው በማስደንገጥ ስለነበረ አህመዲን ወልደስላሴና መለስ በሚስጥር ሰሩት የተባለውን ወንጀል በፊቱ ፍርጥ አድርጎ ቀልቡን በመግፈፍ ነገርዬውን ጀመረው፤ ወልዴ ፊቱ ላብ አቸፈቸፈ…

ይቀጥላል …

Image may contain: 3 people, people standing
Filed in: Amharic