>

ሁለት ብር አጥቶ የተማረ 5 ሚሊዮን ዶለር ተሸለመ (በጉማ ሳቄታ)

እኚህ በፎቶው ላይ የምታይዋቸው እናት ወ/ሮ ሞቲ አያኖ ይባላሉ ። እኚህ እናት በወቅቱ በወር ሁለት ብር በማጣታቸው ምክንያት ያለ አባት የሚያሳድጉት ልጃቸው ከትምህርት ቤት ቀርቶ ከብት ሲጠብቅ ሊኖር እንደሆነ በመረዳታቸው በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ትምህርት ቤት ሄደው”እኔ ምስኪን ነኝ ለልጄ የትምህርት ቤት የወር ክፍያ የሚሆን ሁለት ብር ማግኘት አልችልምና እባካችሁ አንድ ብር አርጉልኝና ልጄ እንደ እኩዮቹ ተምሮ ይግባ …”
ብለው የትምህርት ሀላፊዎችን ጠየቁ ።ይህ የእናት ልመና ምን ማለት እንደሆነ የተረዳው ት/ቤት በጠየቁት መሰረት በወር አንድ ብር ከፍለው ልጃቸው እንዲማር
ፈቀደላቸው ። በዚህም መሰረት የዛሬው አለም አቀፋዊ ተመራማሪ ገቢሳ እጀታ ከፊደል ገበታ ጋር ተዋወቀ ።እሱን የማሳደግ ሃላፊነት በእሳቸው ትከሻ ላይ ብቻ ያረፈው እኚህ እናት እንደምን ተቸግረው ልጃቸው ገቢሳ የአንደኛና ደረጃ ትምህርቱን በመሪነት ደረጃ እያጠናቀቀ ኮሌጅ መግባት ቻለ። ከዚያም ከጅማ የእርሻ የቴክኒክ ት/ቤት በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቀ።
ቀጠለናም ከሃረማያ ዩኒቨርሲቲ በፕላንት ሣይንስ በከፍተኛ ማዕረግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያዘ ።ትምህርት የስኬት ቁልፉ እንደሆነ የተረዳው ገቢሳ ከፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ባገኘው ስኮላርሺፕ እ.ኤ.አ በ1976 የማስተርስ፣ በ1978 የፒኤችዲ ትምህርቱን በፕላንት በሪዲንግ እና በጄኔቲክ አግኝቷል፡፡ ዛሬ ላይ የወ/ሮ ሞቲ አያኖ ጥረት ለቁምነገር በቅቶ
ፕሮፌሰር ገቢሳ በተለያየ ጊዜ በማሽላ ላይ ባገኙት አስደናቂ ምርምር የተለያዩ ሃይብሪድ የሆኑ የማሽላ ዘሮችን መፍጠር የቻሉ ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪም ከሰባ በላይ ለሆኑ ሃገር ኣቀፍና አለም አቀፍ ድርጅቶች አማካሪ ነው ከሁለት መቶ በላይ የምርምር መጽሃፍቶችን አሳትመዋል ከ17 በላይ ታላላቅ ሽልማቶችን አግኝተዋል የሮክፌለር ፋውንዴሽን፣ የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) እና የአሊያንስ ግሪን ሪቮሉሽን የክብር አባልም ናቸው ።ከሮክፌለርና ከጌትስ ፋውንዴሽን ጋር አብረው የሚሰሩ ሲሆን የሣይንስ ካውንስል፣ የሣሣካዎ ግሎባል የቦርድ አባል …የ2009 የworld food prize ተሸላሚም ሆነዋል ።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ ዛሬ ላይ ደግሞ ጥገኛ አረምን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን ለማዳቀል ለሚሰሩት ምርምር ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ግብረ-ሰናይ ድርጅት አምስት ሚሊዮን ዶላር አሸንፈዋል ።ፕሮፌሰር ገቢሳ ለአራት አመታት በሚዘልቀውን የገንዘብ ድጋፍ እየታገዙ ከምርምር ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ማሽላን የሚያጠቃ ጥገኛ አረም ዘረ-መል ላይ ያለውን እውቀት ለማሳደግ በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆንአፍሪካን እየታደጉ ስላሉት ታላቅ ተመራማሪ እኛ ያነሳነው እጅግ ጥቂቱን ነው ። ለፕሮፌሰር ገቢሳ እጀታ መልካም የምርምር ጊዜ እንዲሆንላቸው እንመኛለን ።
ያ በሁለት ብር እጦት የከብት እረኛ ይሆን የነበር ልጃቸውን ለዚህ ላበቁት የፕሮፌሰር ገቢሳና ለልጃቸው ሲሉ ሁለመናቸውን ላጡ እናቶች ክብር ይሁን
Filed in: Amharic