በየትኛው ራጅ በየትኛው ስካነር
የለማ መገርሳ የነ’ አብይ ነገር
እንደምን ይመርመር ?
ወቅቱ የክረምት ወቅት በመሆኑ ከዜሮ በታች ሰባት ዲግሪ ያዘቀዘቀ እና የቀዘቀዘ ጭምር ነበር ፡፡ አንድ ወዳጄ ታህሳስ 14 ቀን 2017 ዓ. ም የልጁን ልደት ለማክበር አዳራሽ ስለሚፈልግ ለጠራው ሰው ቁጥር አዳራሹ ይበቃ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዳይለት ስለቀጠረኝ ነበር ከቀጠረኝ ሥፍራ የተገኘሁት ፡፡ ይህ ሰው ከአስራ ሰባት አመት በፊት ወደ ኖርዌይ ሲመጣ በኦነግ ፖለቲካ አባልነት ተሳትፎው የፖለቲካ ጥገኝነት አግኝቶ ወደ ኖርዌይ የመጣ ሰው ስለነበር የኦነግ ታማኝነቱን ለማስመስከር ቦታ የማይበቃው ኮበሌ እና ተጋፊ ነበር በዚያን ወቅት ዛሬ ግን ወዳጄ ነው ፡፡ በአንድ ወቅት ጽሁፌ የዚህን የአሁን ወዳጄን የዚያን ጊዜ ደግሞ ለሱ እንደ ባላንጣ የሚቆጥረኝን ታሪክ ያነሳሁ ይመስለኛል ከደጋገምኩባችሁ ይቅርታ ፡፡
May 1, በየአመቱ ኦስሎ ውስጥ በዓለም የሠራተኞች ቀን ምክንያት ታላቅ ሠላማዊ ሰልፍ ይደረጋል ፡፡ በዓሉን አስታኮ ይህ ቀን ነጻነት የሚሹ እና በአምባገነን አገዛዝ ተሰቃየን የሚሉ በኖርዌይ የሚኖሩ መጤዎች ሁሉ የሚካተቱበት ብሶት ማሰሚያ መድረክ ነው ፡፡ ቀድሞ ኤርትራውያን ጭምር ይሰለፉ ነበር የዛሬውን አያድርገውና ፡፡ በዚህ ቀን ነው ከዛሬው ወዳጄ ጋር እኔን ጨምሮ ከኔ ጋር ከነበሩ ወገኖች ጭምር ይህ ሰው ቦክስ በአደባባይ የጨበጠብን ፡፡ በዚያን ቀን የያዙት መፈክር « ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ውጭ !! » የሚል ስለነበር ምን ማለት እንደነበር በሰለጠን መንገድ ቀርበን ስንጠይቃቸው በነበር ጥያቄ ነው አለመግባባት ተፈጥሮ ከዚህ የዛሬው ወዳጄ ጋር ቡጢ የተማዘዝነው ፡፡ በወቅቱ የመታም ፥ የተመታም አልነበረም ፡፡ ያ ሁሉ አልፎ የኔና የርሱ ልጅ በሚማሩበት ትምህርት ቤታቸው ውስጥ አንድ ክፍል በመመደባቸው ርስ በርስ ልጆቻችን ጓደኛሞች ይሆናሉ፡፡ ይህ ሁኔታ እኔና እሱንም አቀራርቦን ከፖለቲካ ልዩነት ባሻገር ያ የነበረው የቡጢ መጨባበጥ ሁሉ ተረስቶ ዛሬ እጅግ ቅርብ ነን ፡፡
ሊከራይ ያሰበውን አዳራሽ አብረን ካየን በኋላ ወደ ከተማ ብቅ ብለን የአገራችንን የወቅቱን ፖለቲካና ሁኔታ በኢትዮጵያ ቡና ለማወራረድ በሜትሮ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን ፡፡ ከስፍራው ደርሰን የሜትሮውን በር ከፍተን እኛ ስንወጣ ፣ አቶ ሌንጮ ለታ ደግሞ ሲገቡ በሩ ላይ ተገናኘን ፡፡ ከኔ ጋር ትውውቅም ሆነ ሰላምታ ስለሌላቸው ወዳጄ ከድሮው አለቃው ጋር ሰላምታ ይለዋወጣል ብየ ስጠብቅ ተያይተው ተላለፉ ፡፡ አይ የጦቢያ ፖለቲካ አልኩኝ በልቤ ፡፡ አቶ ሌንጮ እንደተለመደው በጀርባቸው ሁሌ የሚያዝሏትን ቦርሳ አንግተዋል ፡፡ የዛሬ ሶስት ዓመት ግድም ይመስለኛል በአሜሪካን ድምጽ የአማርኛው ፕሮግራም ላይ ቀርበው ፣ የኖርዌው ብርድ አጥንታቸው ድረስ እየገባ ስለጠዘጠዛቸው ሻንጣቸውን ሸክፈው ወደ አገር ሊገቡ እንደሆነ የተናገሩት ፡፡መንገድ ላይ የተጠበሰ በቆሎ ሽታ ቢናፍቃቸውም ፥ የኦሮሞ ህዝብ ጨጨብሳና እርጎ ውል ቢላቸውም ዛሬም አሉ አልገቡም ፡፡ ቢገቡም ከአንድ ቀን የሸራተን አዲስ አዳር በኋላ እንደተጠርዙ በዚያው በቪኦኤ የነገሩን ይመስለኛል ፡፡
የጽሁፌን ርዕስ ለዚህ ነው ያመጣል መንገድ ይወስዳል መንገድ ያልኩት ፡፡ ድንገተኛው ከአቶ ሌንጮ ጋር ያገናኘን ሜትሮ ፣ ባቡሩ ላይ የነበረንን ወግ አስቶ በአቶ ሌንጮ ዙርያ እንዲሆን አደረገ ፡፡ ምነው ደህና ? ሰላም አትላቸውም እንዴ አልኩት ? አልለውም ናይሮቢ አንድ ለሊት ሙሉ ክርክር ገጥመን ሳንግባባ ስለተለያየን ፣ ኧንደውም እሱ ፊውዳል አማራ ነው ኦሮሞ አይደለም ብሎ ስሜን ስላጠፋ አላናግረውም አለኝ ፈርጠም ብሎ ፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ይደክማሉ እንጂ ሌንጮን ይዘን እናሸንፋለን የሚሉ ሁሉ ያዩታል አለኝ በመቆጨት ፡፡ ለምን ? ቢያንስ የአቶ ሌንጮ ለታ ስም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ታዋቂ ስለሆነ እሳቸውን ይዘው ቢጓዙ አይቀልም ትላለህ አልኩት ወዳጄን ? በፍጹም የችግሩ መንስኤ የሆኑ ሰዎች የችግሩ መፍትሄ አምጪ አይሆኑም አለ አሁንም ፈርጠም በማለት ፡፡ እሱ ! አለ አቶ ሌንጮን ማለት ነው ፣ የወጣት እድሜያችንን ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም ብሎ ከርክሞ ካሳደገን በኋላ ነው ዛሬ ተመልሶ ኢትዮጵያዊ ነን የሚለው አይነት እሮሮ አሰማኝ ፡፡ ከኦሮሞ ህዝብ ልብ ውስጥም እንደወጡ አስረግጦ ነገረኝ ፡፡
ወጋችንን ቀጥለን እያወጋን ሳለ ፣ እኔም በአንድ ወቅት ስለ አቶ ሌንጮ ለታ ያጋጠመኝን አወሳሁት ፡፡ እንዲህ ነበር ፡፡ በአንድ ወቅት ከአንድ የቡና መሸጫ ካፌ ቤት በረንዳ ላይ ከአቶ ዩሱፍ ያሲን/ ሃሰን ዑመር አብደላ ጋር የአገራችንን ፖለቲካ እያወራን ሳለ ፣ አጠገባችን አቶ ሌንጮ ለታ ይደርሳሉ ፡፡ የምናወራው በአማርኛ ስለነበር ጭውውታችንን የሰሙት አቶ ሌንጮ፣ አቶ ዩሱፍን ብቻ ሰላም ብለው ንግግራቸውን በንግሊዘኛ ቀጠሉ ፡፡ አቶ ዩሱፍ ካልዘነጋሁ የሚመልስላቸው በአማርኛ ነበር ፡፡ የሚያወሩትን ጨርሰው አቶ ሌንጮ ወደ ጉዳያቸው ሲሄዱ ፣ አቶ ዩሱፍን ሁሌ ስትገናኙ በንግሊዘኛ ነው እንዴ የምትወያዩት በማለት ጠየቅሁት ? ኧረ በፍጹም በአማርኛ ነው ይለኛል ፡፡ አይ ! እንግዲህ ክኔ ጋር በአማርኛ ስታወራ ስለሰሙህ እኔን በአማራነት ፈርጀውኝ ነው በማለት ተሳሳቅን ፡፡ መቸም ለአፋሩም ለትግሬውም ፥ ለኦሮሞውም ፥ መግባቢያው ቋንቋ በታሪክ አጋጣሚም ሆነ በሌላ ምክንያት አማርኛ ነውና ለአቶ ሌንጮ ለታ ቢጎረብጣቸውም እንደ ፖለቲከኛ ያን ማድረጋቸው ዘወትር የሚገርመኝ ጉዳይ ነው አልኩት ለወዳጄ ፡፡
በወጋችን መሀል አጋጣሚ ሆኖ ሌላ አንድ ሁለታችንም የምናውቀው ሰው በአጠገባችን ሲያልፍ ስላላየን በስሙ ጠርቼ አብሮን እንዲያወጋን ጋበዝኩት ፡፡ ወዳጄና አሁን የመጣው ሰው ደግሞ የአንድ ቦታና ቀዬ ተውላጅ በመሆናቸው ጭምር በኦነግ ፖለቲካ አባልነት ስለሚተዋወቁ በንጥልጥል ላይ የነበረውን የአቶ ሌንጮ ለታ ወግን አዲስ ከመጣው ሰው ጋር አስቀጠልነው ፡፡ ያመጣል መንገድ ይወስዳል መንገድ እንዲህ ነው ፡፡ አዲስ የተደባለቀን ሰው አሁንም ድረስ በኦነግ ፖለቲካ አመራር ውስጥ ቦታ ያለው ሰው ነው ፡፡ እሱም አቶ ለታ ሌንጮን ኮንኖ ጨዋታው ሲደራ ወደነ አቶ ለማ መገርሳ እና ዶክተር አብይ ተገባ ፡፡ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረውን ለተንታኞቹም ጭምር እንቆቅልሽ የሆነውን የነለማ መገርሳን አካሄድ ሁሉ ሁለቱ የኦነግ ሰዎች አፈር ያስበሉት ጀመር ፡፡ ቢያንስ እንደ መኤሶን ወቅት Critical supportእየሰጠን ቢታገዙ አይሻልም ወይ እንዲሁ ከምናወግዛቸው አልኩኝ ፡፡ ይኽማ እነ ሌንጮ የመጡበት አዲሱ መንገድ ነው ! ስልጣን እንደማያገኙ እነሌንጮ ሲያውቁ አሁን ማሳለጫው መንገድ እሱ ነው በሚል አሰፍስፈዋል አሉኝ ሁለቱም ፡፡
ለማ መገርሳን እናውቀዋለን የሰፈራችን እና የመንደራችን ልጅ ነው ፡፡ አንተ አታውቀውም ፡፡ በኦነግ ፖለቲካ ታስረን ስንገረፍ መጨረሻ እስር ቤት ውስጥ መጥቶ የሚያነጋግረንና የኦህዴድ አባል ከሆናችሁ ኦነግንም ካወገዛችሁ ከስር ትወጣላችሁ በማለት ከእስር ከተፈታን በኋላ በየቀኑ እሱ ቢሮ እየሄድን መኖራችንን እየፈርምን አዘናግተን ነው ከአገር ያመለጥነው አሉኝ ፡፡ ጌታቸው አሰፋ ለማ ነው ለማም ጌታቸው አሰፋ ነው ፡፡ አብይም ሆነ ለማ ከጌታቸው አሰፋ ጋር በአንድ የስለላ ተቋም የሰሩ ስለሆነ ፣ ኧንደውም እጅግ አደገኞቹ ሰዎች ለማና አብይ ናቸው ፡፡ አሁን ደግሞ የመቀሌው ጉባኤ አለቃቸውን ጌታቸው አሰፋን መርጦ ያመጣ ስለሆነ በነለማና አብይ ወርቃማ ንግግር ለሌላ ባርነት ፍጥረት እየተመቻቸ ነው ምንም ለውጥ አይመጣም ይልቅ ሰንሰለቱ ይጠብቃል ፡፡ ለማ በቅርቡ በአማራና ኦሮሞ ህዝብ መሃል ሊኖር ስለሚገባው መልካም ግንኙነት ያወራውን በመርህ ደረጃ እኛም ከልብ የምንደግፈው ነው ፣ ሆኖም ንግግሩ በወርቅ የተለበጠ የህወሃት ማስተኛ ዘዴ ናት ፡፡ እንደ ባህርዳሩ ጉባኤ እያደር ታያለህ በቅርቡ የሱማሌ ክልልና የኦሮሞ ህዝብ የሰላም ጉባኤ ተካሄደ ብለው ቲያትር ይሰራሉ ፡፡ « ሃሮምሳ » በአፋን ኦሮሞ በአማርኛ ደግሞ ውርስ ትርጉሙ ተሃድሶ የሚሉት ማስተኛ የትም እንደማይደርስ የሚያሳየው በቅርቡ የኦሮሚያ የደህንነት ምክር ቤት ብለው ባካሄዱት ስብሰባ በጸጥታው ዘርፍ የፌዴራል ክፍሉን ወክለው የመጡት ሃላፊዎች ሁሉ ትግሬዎች ነበሩ የቱ ላይ ነው የነለማ ነጻነት ? በሚል ጥያቄያዊ እንቆቅልሽ ሊያስረዱኝ ሞከሩ ፡፡
ከነኝሀ ሁለት የኦነግ ሰዎች ጋር በነበረኝ ውሎ እነ’ለማ መገርሳ የተያያዙት መንገድ አበረታታች እንደሆነና በይበልጥም የአንድነቱ ኃይል በርቱ እያለ ሂሳዊ ድጋፍ ቢያደርግላቸው የህወሃትን እድሜ ያሳጥራል የሚለውን እምነቴን ቅርቃር ውስጥ ከቶ በጥልቀት እንዳስብ አደረገኝ እስከአሁን ቁርጥ ያለ ምልከታ አላሳያችሁንም ፣ በመሆኑም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ፡፡ አሁን በነ’ አቶ ለማ መገርሳና በነ’ ዶክተር አብይ አመለካከት ላይ ያላችሁን ጥርጣሬ የኢትዮጵያ ህዝበ እንዲረዳው ያደረጋችሁት ትንታኔ በመገናኛ ብዙሀን የለም ፡፡ ቢኖርም ምናልባት በአፋን ኦሮሞ ብቻ ለኦሮሞ ህዝብ ሊሆን ይችላል ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ትግራዩንም በሉት ፥ አማራው ፥ ደቡብ በሉት ፥ አፋሩ ወዘተ, ሊሰማ በሚችለው አማርኛ ይህን መሰል ሴራ በነ’ለማ መገርሳ በኩል ካለ አለመግለጻችሁ ደካማ ጎናችሁ ነው ፡፡ ይህ እንደ ድርጅት ቅድሚያ መስጠት የሚገባችሁ ጉዳይ ነበር ላልኳቸው ሃሳብ ONN , Oromo News Network ላይ ለአድማጮቻችን እያሰማን ነው ፣ በርግጥ በአማርኛ ላይ ሰፊ ዘገባ አለማድረጋችን ስህተት ነው ፡፡ ይህ በቶሎ ይታረማል ነበር ያሉኝ ፡፡
በጨፍጋጋው የስካንዲኔቪያ ክረምትና ድብርት ጋር ፣ የኦነግ ሰዎች የሰጡኝ ትንተና ይበልጥ ወስዋስ ውስጥ እንድገባ አደረገኝ ፡፡ እንኳን እኔ አንድ ተራ ሰውና እውቅ የአገራችን የፖለቲካ ጠበብት ተንታኞችየነ አባባ ታምራትን ርዳታ በሚሹበት ወቅት እንዲህ ለያዥ ለገራዥ የነ’ ለማ ጉዞን ማወቅ ባስቸገረበት ወቅት የእሁድ ህዳር 24 2010 የሪፖርተር ጋዜጣ በመቀሌ የተደረገውን ሹም ሽር በሚያትት ዘገባው ፣ የተሿሚዎቹን ስምንት አመራሮች ፎቶ ሲለጥፍ ፣ከትግራይ ህዝብ ውጭ ሌላው እንዳያውቃቸው ፎቷቸው ያልተለጠፈውን አቶ ጌታቸው አሰፋን ፎቶ አዘልሎ ከዚህ የሚከተለውን ዘገባ አስፍሯል ፡፡ ህምምም ያሰኛል ፡፡
«የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ አቶ ጌታቸው አሰፋና ወ/ሮ ፈትለወርቅ በደኅንነት ተቋማት ውስጥበመረጃ ትንተና ልምድ ያካበቱ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ቀጣዩን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከተመሳሳይ የደኅንነት ተቋማት የመጡአመራሮች ተፅዕኖ የሚጎላበት ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ ኦሕዴድን በመወከል የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ሆነውየተወከሉት አቶ ለማ መገርሳ፣ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ርእና ዓብይ አህመድ (ዶ/) ከብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት የመጡ አመራሮችናቸው፡፡ »