>

ብሄር ለፖለቲካ ስብስብ ሲውል የቂም፣የጥላቻና የእኛ ብቻ አይነት ግትርነት ነው

 

ሙክታሮቪች ዑስማኖቫ

የእገሌ ብሄር ሀሳብና አስተሳሰብ የሚባል ነገር የለም። እርግጥ የአንድ ብሄር አባላት አብላጫቸው የሚደግፉት ሀሳብ ይኖራል። በአንድ ማህበርም አብላጫው የሚቀበለው ሀሳብ እንደሚኖረው። ያ ሀሳብ ገዢ ሀሳብ የሚሆነው በዴሞክራሲያዊ የድምፅ አሰጣጥ ሂደትን ተከትሎ ነው። የብሄር ፖለቲካ አራማጅ ግን አንዳቸውም የብሄራቸው ውክልና የላቸውም። የብሄር ጥቅምና ፍላጎትን ማንንም ጠይቀው፣ ምርምር አድርገው፣ የብሄር አባላትን ፍቃድና ውክልና አግኝተው አያውቁም። የዚህ ብሄር አስተሳሰብ፣ ሀሳብና ርእዮተአለም የዚያ ብሄር አስተሳሰብና ሀሳብ የሚባል የተረጋገጠ ነገር የለም። የግለሰቦች ሀሳብ ነጥሮና ተቀምሮ አብላጫው የሚደግፈው ሀሳብ ሊገኝ ይችላል። ይህም የግለሰቦች ሀሳብ ነው፣ ጊዜያዊ ነው። በጊዜ ሂደት ሊለወጥ ይችላል።

የብሄር ማንነት ግን አይለወጥም። ብሄር ለፖለቲካ ስብስብ ሲውል ቆይቶ የሀገር መፍረስ አደጋ የሚያመጣ ነው። ብሄር ላይ የሚንጠለጠል ፖለቲካ ለሰጥቶ መቀበል፣ ፍላጎቶችን ለማጣጣም አይመችም። አይዲዮሎጂው ወደፊት ለእድገት የሚያመች የመፍትሄ ሳይሆን የቂም፣ የጥላቻና የእኛብቻ አይነት ግትር ነው።

የብሄር ፖለቲካ የግለሰቦች ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሰረተ ፖለቲካ እንጂ የአንድ ብሄር/ቡድን አለመሆኑን የምታውቀው አንድ ብሄርን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲወክሉት ስትመለከት ነው። ብሄሩ አንድ ከሆነ ለምን የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ያስፈልጉታል? ግለሰቦች በጎሳ ፈረስ ላይ ተፈናጠው፣ የግል ፍላጎትና የስልጣን ምኞት ይዟቸው ስለሚጋልቡ ነው።

ዘውጌ ብሄርተኞች ባጠቃላይ ለአንድ ብሄር ብዙ ወኪሎች ያለውክልና የእንደራሴነት ሹመት ለራሳቸው የሚሰጡት ለራሳቸው የስልጣን ጥም ነው፣ በሀሳብ የሚለያዩትም ብሄር ጉኡዝ ነገር ስለሆነ ማሰቢያ አዕምሮ ስለሌለው ነው። ግለሰቡ ነው የሚያስበው፣ መብትም የግለሰብ ነው። የግለሰብ ስብስብ የሆነው ብሄር በለው ሌላ ቡድን በግለሰብ ነፃ ፍቃድ ላይ የሚመሰረት ስብስብ ከሆነ ብቻ ነው ሀሳቡ አትሊስት የማጆሪቲው ሊታወቅ የሚችለው። በብሄር ፖለቲካ ግን ከናት ማህፀን የወጣ ልጅ ገና እንደተወለደ ፖለቲከኛ ነው። እጣ ፈንታው ያርባ ቀን እድሉ ተወስኖለታል። ይህ ሃላቀር ፖለቲካ ነው። በግለሰብ ፈቃድ ስብስብ የምትመሰረተው ቡድን የግለሰቦቹ ሀሳብ ፍላጎትንና ጥቅምን መሰረት አድርጎ ሊደራጅ ይችላል። የዘውጌ ብሄርተኝነት ስብስብ ግን በአርባቀን እድልህ የሚወሰን ፀረደሞክራሲና ሰው የመሆንን ፀጋ ገፋፊ ነው።

Filed in: Amharic