>
2:14 pm - Saturday October 23, 2021

38ቱ ተከሳሾች ተሰቅለዉ መገረፋቸዉን፣ጥፍራቸዉ በፒንሳ መነቀሉን፣ በሚስማር ውስጥ እግራቸዉ እና ጀርባቸዉ መበሳሳቱን በመግለጽ የድረሱልኝ ጥሪ አቀረቡ

                                                                            ብርሃኑ አየለ
ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ 38ቱ ተከሳሾች ያቀረቡት የድረሱልን ጥሪ ደብዳቤ አስቀድሞ ተከሰዉ በነበረበት ክስ የዋስትና መብታቸዉን ተከልክለዉ እንደማንኛውም እስረኛ ክሳቸዉን በቀጠሮ እየተከታተሉ እያሉ ነሃሴ 28/ 2008 ዓ•ም ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ የእሳት ቃጠሎ ይነሳል። በዚህ ቃጠሎ ምክንያት “ሊያመልጡ ሞክረዋል!” በሚል ሰበብ፣ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የመብት ጥያቄ የሚጠይቁ ወንድሞቻቸዉን እና ጓደኞቻቸዉን እፊታቸዉ በጥይት ገድለው እሳት ውስጥ ጨምረው እንዳቃጠሉዋቸዉ ይህ የጥሪ ደብዳቤ ይገልፃል።

እንዲህ ያለ አረመኔያዊ ድርጊት ከፈፀሙ በኋላ ገና ለገና ይህንን እውነት ያጋልጡብናል ብለው በመስጋት ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት በመውሰድ ለ3ወራት ከቤተሰቦቻችን ጋር እንዳይንገናኝ ተደርገን ለምርመራ በሚል ሰበብ በዋና ኢንስፔክተር አለማየሁ በሚመራው ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ አይደገምም ተብሎ ሰማዕታት ሙዝዬም ውስጥ ሀውልት የተሰራለት የቶርች ገረፋ ተፈፅሞብናል ሲሉ በጥሪዉ ገልፀዋል።


በካቴና መታሰራቸዉን፣ ተሰቅለዉ መገረፋቸዉን፣ ጥፍራቸዉ በፒንሳ መነቀሉን ፣ በኤሌክትሪክ ሾክ መደረጋቸዉን፣ በሚስማር ውስጥ እግራቸዉ እና ጀርባቸዉ መበሳሳቱን ፣ ጭንቅላታቸዉ በሰደፍ መፈነካከቱን፣ የተወሰኑ ታራሚዎች ተለይተዉ ብልታቸዉ ላይ ሁለት ሊትር ሀይላንድ ውሃ እናዳንጠለጠሉባቸዉ እና ሌሎችም ተዘርዝረው የማያልቁ ብዙ በደሎች እንደተፈፀመባቸዉ አሳዉቀዋል።

እንዲሁም የደረሰባቸዉን ኢሰብአዊ ድርጊት ታህሳስ 14/2009 ዓ•ም ለፍርድ ቤት በማሳየትና በማስረዳት ፎቶ ለመነሳት ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም ጥያቄያቸዉን ፍርድ ቤቱ አለመቀበሉን ጠቅሰዉ፤ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲመለሱ “ፍርድ ቤት ሄዳችሁ ብትለፈልፉ ምንም አታመጡም!” በማለት እስከ መጋቢት 12/2009 ዓ•ም ድረሰ ለ3 ወራት ጨለማ ቤት ውስጥ ተከተው እና የቤተሰብ ግንኙነት ተከልክለዉ፤ በፀሀይ ብርሃን እጦት መልካቸዉ ቢጫ እስኪሆንና አይናቸዉ ብርሃን ማየት እስኪያቅተው ድረስ ተቆልፎባቸዉ መሰቃየታቸዉንም አትተዋል።

ወደ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደዉ የተፈፀመባቸዉን ኢሰብአዊ ድርጊት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን መርማሪዎች ከ10 ወራት ቆይታ በኋላም ቢሆን በአይናቸው ያዩትን እውነት በዝርዝር በሪፖርት ለፍርድ ቤት ማቅረባቸዉን በማስታወስ ፍርድ ቤቱ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ሪፖርት ላይ ብይን ለመስጠት ለህዳር 29/ 2010 ዓ•ም ቀጠሮ መያዙንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን የተፈፀመባቸዉን ኢሰብአዊ ድርጊት ሙሉ ለሙሉ አለማካተቱንም በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል።

ሰብአዊ መብት ኮምሽን ሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙባቸዉን አካላት በሕግ እንዲጠየቁ በማለት ቁርጥ ያለ ሪፖርት ማቅረብ ሲገባው እና የኮምሽን መስርያ ቤቱ ጉዳዩን ተከታትሎ በዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያደረሱ አካላትን በሕግ ማስቀጣት ሲገባው ምክረ ሀሳብ በማለት የተለሳለሰ የፍራቻ የሚመስልን ሪፖርት በማቅረቡ ቅር መሰኘታቸዉን ጠቅሰዉ መስርያ ቤቱ እውነቱን እያወቀ እንዲህ ያለ ሪፖርት በማቅረቡ ምን ያህል የደህንነት ቢሮ ተፅዕኖ እንዳለበት እና በራስ መተናመን የጎደለው መስርያ ቤት መሆኑን የሚያሳይ ነው በማለትም በኮምሽኑ ላይ ያላቸዉን አስተያየት ገልፀዋል።

ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን በተጨማሪ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እና በፌደራል ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም በ19ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች ላይ ያለቸዉን ቅሬታ በማተት ግልባጭ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአሜሪካ፣ ለብሪታንያ፣ ለስዊድን፣ ለካናዳ ፣ለኖርዌ ኢንባሲዎች አና ለማህበራዊ ሚድያ ለኤፍ ኤም ራዲዮች፣ ኢቢሲ እና ለሌሎች ሚዲያዎች ይድረስ በማለት እና እንዲሁም በእንግሊዘኛ ተተርጉሞ ለአለም ህዝብ እንዲደርስ በመጠየቅ ጥሪዉን ቋጭተዋል።
Filed in: Amharic