>
5:13 pm - Thursday April 19, 5240

የሁለት ዓለም ሰዎች በአንድ ሀገር ኢትዮጵያውያን በወዲህ ህወሀት በወዲያ (መሳይ መኮንን)

                                                                   ከወዲህ

ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ሰዓት አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለቀናት ከቆየበት ውጥረት አልተላቀቀም። ከሁለት በላይ ተማሪዎች ተገድለዋል። በርካቶች ቆስለዋል። በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአማራና ኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች በስጋት ከማደሪያቸው መውጣት አልቻሉም። ከግቢ ውስጥ የታዩ ተማሪዎች ይደበደባሉ። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ ስጋት አንዣቧል። በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች በአጋዚ ሰራዊት ጥበቃ ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ቢወጡም በከተማው አቋርጠው ወደ ”ክልላቸው” መሄድ አልቻሉም። ግጭት ተቀስቅሶ ለጊዜው ቁጥሩ ያልተገለጸ ሞት ተመዝግቧል። የዩኒቨርሲቲው አንድ አዳራሽ ተቃጥሏል።

በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ውጥረት ተከስቷል። ህንጻ እየተቃጠለ ነው። የአጋዚ ሰራዊት ግቢውን ወሮታል። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብሄር ላይ ባነጣጠረ መልኩ ግጭት መፈጠሩንም መረጃዎች ያመለክታሉ። የጎንደር ተማሪዎች የህወሀት አገዛዝ ያበቃ ዘንድ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ ውለዋል።በዚያም የትግራይ ተወላጆች ሆቴል ተይዞላቸው በጥበቃ ስር እንደሚገኙ ታውቋል።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ሳምንት የተነሳው ተቃውሞ ቀጥሏል። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር የጋራ ድምጽ እያሰሙ ነው። መቱ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቆሟል። በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ከ35ሺህ በላይ ተማሪ ግቢውን ለቀው ወጥተዋል። በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ሶስት ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን መቀጠል እንዳልቻሉ በይፋ አስታውቀዋል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ አዝማሚያው ተመሳሳይ የሆነ ውጥረት እያንዣዣበበ እንደሆነ ዛሬ በጠዋቱ ሰምቼአለሁ።

በከተሞችና መንደሮችም ተቃውሞው ግድያው ቀጥሏል። በሀረር ጨለንቆ ከ10በላይ ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት ተገድለዋል። በወሎ ሰቆጣ በተነሳ ተቃውሞ ለጊዜው ቁጥሩ ያልታወቀ ሰው ተጎድቷል። በደቡብ ኦሞ የ13 ሰዎች ህይወት የቀጠፈ ጥቃት ተፈጽሟል። እዚህም እዚያም ያለው ነገር አያምርም። ነገሮች ጦዘዋል። ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ ናት። የጭንቀት ምጥ።

ከወዲያ

ከህወሀት መንደር ፌሽታው ለጉድ ነው። የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በሚል ሰመራ ላይ ከቀለጠው ድግስ በተጨማሪ በየሀገራቱ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፡ በየመስሪያ ቤቱ፡ በየቀበሌው፡ በሴል፡ ፎረምና ሊግ ደረጃ ቸበርቻቻው ደምቋል። የ1997ቱ የምርጫ ሃንጎቨር ለኢትዮጵያ ያመጣላት ነገር ቢኖር የበዓልና የድግስ ሱናሚ ነው። የህወሀት አገዛዝ በኢትዮጵያ ህዝብ በቀይ ካርድ እንዲሰናበት የተደረገበትን ምርጫ በጠራራ ጸሀይ ኮሮጆ ገልብጦ፡ የአሸናፊነት አክሊሉን ለራሱ ደፍቶ፡ የማሰመሰያ ዲሞክራሲ ጭምብሉን አውልቆ የወታደራዊ ቆብ ደፍቶ በስልጣን ለመቆየት ከወሰነ በኋላ ኢትዮጵያን በድግስና በዓል ማጥለቅለቅን እንደመንግስታዊ ተግባር በዘመቻ ገብቶበታል። የምርጫ ሽንፈት የፈጠረው ድንጋጤ ኢትዮጵያ ላይ ያወረደው መዓት ቢኖር የፌሽታና የቸበርቻቻ ናዳ ሆኗል።

ከግማሽ ሚሊየን በላይ የኦሮሞ ልጆች ተፈናቅለው ከፍተኛ ችግር ውስጥ በገቡበት፡ ከ400ሺህ በላይ የሶማሌ ክልል ተወላጆች በረሃብና ጠኔ ምክንያት በካምፕ ውስጥ በሰፈሩበት፡ ከ8ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን የሚላስ የሚቀመስ አጥተው የረሃብ ጉንፋ እያሳሉ ባሉበት፡ ድርቅና ረሃብ ገጠሬውን ኢትዮጵያዊ ሞፈረና ማረሻ አስጥሎ ለልመናና ስደት በዳረገበት፡ የከተማ ውስጥ ድህነት ስር ሰዶ በየትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በረሃብ ተዝለፍለፈው መውደቃቸው በተበራከተበት፡ ሌላም ሌላም….አፋር ሰመራ ላይ በቢሊየን ገንዘብ የብሄር ብሄረሰቦች ድግስ ተሰናድቷል።

የአፋር ክልል መንግስት ከተራበው ህዝብ ጉሮሮ በመንጠቅና ከፌደራል መንግስት በመበደር ቸብርቻቻውን እንዳዘጋጀው ሀፍረት ሳይኖራቸው በይፋ ገልጸዋል። በሴፍትኔት ቀለብ ከሚሰፈርላቸው ተረጂዎች ሳይቀር ተነጥቆ በዓሉ መዘጋጀቱንም ሰምተናል። የባለፈውን ዓመት በዓል ያከበረው የጋምቤላ ክልል ለበዓሉ የተበደረውን ለመክፈል ከዓመታዊ በጀቱ መቀነሱንም አውቀናል። የዚህ ውጤትም የጋምቤላ የመንግስት ሰራተኛ ደምወዝ ሳይከፈለው ከሁለት ወራት በላይ መቆየቱን ባለፈው ሳምንት ተገልጿል። ይህ ሁሉ የበዓልና የድግስ ጋጋታ ማንን ለመጥቀም እንደሆነ ይታወቃል። ይሄን በሌላ ጊዜ ማንሳቱ ይሻላል።
እንግዲህ የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በደመቀበት ሰሞን ነው በመላ ሀገሪቱ ብሄርን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች የበረከቱት። ኢትዮጵያውያን በየመንደሩ፡ በየዩኒቨርሲቲው፡ በኳስ ሜዳ በዘር ተቧድነው ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ የገቡትም ከሰመራ እስከ ለንደን ኤምባሲ፡ የብሄረሰቦች ድግስ በቀለጠበት በዚሁ ሰሞን ነው።

የሁለት ዓለም ሰዎች በአንድ ሀገር። ኢትዮጵያውያን በወዲህ፡ ህወሀት በወዲያ

ሃይለማያም ደሳለኝ ከሰሞኑ

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት ቃለመጠይቅ የተናገሩት የህወሀትን አገዛዝ ይሉኝታ ያጣ፡ ቅጥፈት የበዛበት፡ ሞራል የጎደለው አካሄድ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ጅራፍ ራሱ ገርፎ እንደሚጮሀው ህወሀትም በሃይለማርያም አፍ የነገረን የብሄር ፖለቲካን እንደሚጠየፍ ነው። ቃል በቃል ሃይለማርያም ያለው ” የድሮ ተማሪዎች በሀሳብና በርዕዮት ዓለም ፖለቲካ እንጂ የሚፋጩት በብሄር አይደለም። የአሁኑ ተማሪ በብሄር መጋጨቱ ተገቢ አይደለም።”

ለ40ዓመታት የዘር ፖለቲካን የጋለበ፡ ለ26 ዓመታት ኢትዮጵያን በዘርና ጎሳ ሸንሽኖ ያጋደለ፡ ያባላ፡ ከሁለት ትወልድ በላይ በዘር ፖለቲካ ጠምቆ ኮትኩቶ ያሳደገ፡ ከዘር ፖለቲካ ውጭ ህልውና የሌለው የህወሀት አገዛዝ የወረወረው ሰይፍ ተመዘግዝጎ ወደራሱ ሲመጣ፡ ያሳደገው ልጅ በአደገበት ቋንቋ ሊያናግረው ከፊቱ ሲደቀን ”የለሁበትም” ዓይነት ጨዋታ ጀምሯል። የብሄር ፖለቲካ የህውሀት ደምና አጥንት ነው። በአስተሳሰብ ድህነት የሚሰቃዩ፡ ስድብ እንጂ ሀሳብ ያልፈጠረባቸው አቅምም አቋምም የሌላቸው የህወሀት መሪዎች የጫሩት እሳት አጠገባቸው ደርሶ ሲለበልባቸው መወራጨት መጀመራቸውን እያየን ነው።

ህወሀቶች የዘር ፖለቲካን ያራገቡት በዋናነት በከፍተኛ የትምህር ተቋማት ውስጥ ነው። በፓርቲው መዋቅር ዩኒቨርስቲዎች በዘርና ጎሳ እንዲደራጁ በግልጽ የተቀመጠ አሰራር አለ። በኦሪገን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የዶክተሬት ተማሪ እንዳልካቸው ሃይለሚካዔል እንደሚለው በኢትዮጵያ ተማሪዎች በሀሳብ እንዲደራጁ አይፈቀድም። የብሄር ፖለቲካ ድርጅቶች ቅርጽ እንዳለ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው በህወሀት መንግስት ታቅዶና በጀት ተመድቦለት ነው። በዚህም ተማሪዎች በብሄር ማንነታቸው እንጂ በክህሎታቸው፡ በእውቀታቸው እንዲደራጁ፡ እንዲያስቡ አይደረግም። አንድ ለአምስት በተባለው አደረጃጀት ተጠርንፈው ከብሄራቸው ውጪ ስለሌላ እንዳያስቡ ማድረግ የህወሀት የፖለቲካ ግብ ሆኖ ተቀምጧል።

ሃይለማርያም በአይዶሎጂ መደራጀት ድሮ ቀረ እያለ ሲያላዝን፡ የአማራ ቴሌቪዥን ስለአዲግራቱ ግጭት ያናገረው ተማሪ ”በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የብአዴን አስተባባሪ” በሚል የስራ ድርሻ መሆኑ ጉዳዩን አስቂኝም፡ አሳዛኝም ያደርገዋል። ዛሬ ደርሶ ተማሪዎች ላይ ጣት የሚጠነቁለው ህወሀት ወይ የብሄር ፖለቲካው ተሸንፏል፡ አልያም ጊዜያዊ ማስተንፈሻ ስልት ነው ይላል እንዳልካቸው ሃይለሚዔል።

የህወሀት አደገኛና መርዛማ የዘር ፖለቲካ የተተከለው በትምህርት ስርዓት ውስጥ ነው። በኦሮሚያ ክልል አጼ ምኒሊክን ጡት ቆራጭ አድርጎ የሚያስተምር ስርዓተ ትምህርት ይቀርጻል። በአማራ ክልል አጼ ሚኒሊክን የስልጣኔ አባት አድርጎ ያስተምራል። በእነዚህ ጫፍና ጫፍ በቆሙ ሁለት ፍጹም ተቃራኒ ስርዓተ ትምህርቶች ተኮትኩቶ ያደገ ተማሪ በዩኒቨርስቲ ሲገናኝ የሚፈጠረውን ማሰብ የሚከብድ አይደለም። ህወሀትም ይህንን ነበር የፈለገው። እንደፈለገው ግን አልሆነለትም።

ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ዩኒቨርስቲዎች ዘር ፖለቲካ ማራገቢያ ሲሆኑ ይህንን የሚያስፈጽሙ የትግራይ ተወላጅ አሉ። በደህንነት(ሰቆቃ) መስሪያ ቤቱ ደምወዝ የሚከፈላቸው፡ የማይመረቁ ተማሪዎች መኖራቸው ጸሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። እነዚህ ሰላይ ተማሪዎች የህወሀትን አገዛዝ ህልውና የሚፈታተኑ እንቅስቃሴዎች በዩኒቨርስቲ ውስጥ እንዳይከሰት ሌት ተቀን ተግተው የሚሰሩ እንደሆኑም ግልጽ ነው። ዛሬ በየዩኒቨርስቲው ለፈነዳው የዘር ግጭት የእነዚህ ሰላይ ተማሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል።

የአድዋ ስረወ መንግስት

ትንሽ ስለአድዋ ስረወ መንግስት እናውራ። የህወሀትን መንግስት ስለሚመራው ስረወ መንግስት። ለሁለት ወራት ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ድረስ የዘለቀው የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የአድዋን ስረወ መንግስት ተክሎ መጠናቀቁ ይታወሳል። ከዘጠኙ የፖሊት ቢሮ አባልት መሀል ስድስቱ የአድዋ አፈር ያበቀላቸው ናቸው። በጥቅሉ ከ75 በመቶ በላይ የህወሀት አስኳል አመራር እትብቱ የተቀበረው ከአድዋ መሬት ውስጥ ነው። በአጭር አነጋገር መቀሌ የአድዋ ስረወ መንግስትን ቀብታ ሰይማለች። የኢትዮጵያውያን ኩራት፡የአፍሪካውያን ዓርማ፡ የመላው ጥቁር ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት የሆነው የአድዋ መሬት እነዚህን እንጉዳዮች፡የዘመን ኩሶች፡ የትውልድ አበሳዎች፡ የሀገር ማፈሪያዎችን ማብቀሉ አስገራሚ ነው።

የህወሀት አመራር የዘር ግንድ በአድዋነት ብቻ ተወስኖ አልቀረም ሲሉም የሚሟገቱ አሉ። ከዚያም ወርዶ የአንድ ቤተሰብ ጎጆ ውስጥ ገብቷል በማለት የሚገልጹትንም ሰምተናቸዋል። በዚህም ተባለ በዚያ ህሊና የሚባለውን ትንሹን እግዚያብሄር የተጠየፉ፡ ተከዜን ሲሻገሩ በእንዶድ አጥበው የጣሉ፡
አእምሮ የሚባለውን ማመዛዘኛ ክፍል ቆርጠው ያስወገዱ፡ ማስተዋል የተሰኘውን የብርሃን መንገድ ጥርቅም አድርገው የዘጉ፡ ይሉኝታ የተባለውን የጨዋዎች መገለጫ ከመሬት አርቀው የቀበሩ፡ ውሸትን ስንቅና ትጥቃቸው ያደረጉ፡ የአንድ ሰፈር ልጆች የስልጣን ኮርቻው ላይ ተፈናጠዋል። የአድዋን ስረወ መንግስትን አጽንተው፡ ቃል ገብተው ተማምለው ተለያይተዋል።

መቀሌ ዝም ብላለች። አዲግራት አላጉረመረመችም። ተምቤኖች ድምጻቸው አልተሰማም። የአክሱም ተጋሩዎች አልተቃወሙም። ስለሽሬ እንደስላሴዎችም የታወቀ ነገር የለም። ኩናማ፡ ኢሮብ፡ ቀድሞውኑም በህወሀት ሰፈር የሚታሰቡ አይደሉምና ከእነሱ የሚጠበቅ ነገር አይኖርም። ዝምታው መስማማት ነው። የአድዋ ስርወ መንግስትን ተቀብለውታል።

የአድዋ ስረወ መንግስት ምስረታ ያረጋገጠው ለውጥ እንደማይኖር ነው። የባሰ እንጂ የተሻለ እንደማይመጣ ህወሀቶች በግልጽ ነግረውናል።
የአድዋ ስረወ መንግስት እንኳን የኢትዮጵያን በአስተሳሰብ መሻገር ላቃተው የትግራይ ክልልም መፍትሄ የሚያመጣ መንግስት አይደለም። አሁን የደረሰበት ቁመና ከመፍትሄ አካልነት ይልቅ የችግሩ ተዋናይ ከመሆን ያለፈ ሚና እንዳይኖረው አድርጓል። የፌደራል አወቃቀሩ የዚህ ሁሉ መከራ ምንጭ መሆኑን ዓለም እያወቀው በሌላ እንጭፍጫፊ ሰበቦች ድርደራ ላይ የተጠመደ አገዛዝ ሆኗል።

የሃይለማርያም የሰሞኑ ቃለመጠይቅ በግልጽ እንደሚያሳየው የአድዋ ስረወ መንግስት ኢትዮጵያን ከገባችበት ቅርቃር ለማውጣት ፍላጎትም፡ አቅምም የለውም። የአገዛዙ ”ምሁራን” ደም እያፋሰሰ ያለው ግጭት በፌደራል ስርዓቱ ምክንያት የተጫረ አይደለም የሚል መፈከር ይዘው በሲምፖዚየምና ወርክሾፕ ሊያደነቁሩ መዘጋጀታቸው እየተነገረ ነው። ይህም ከአድዋ ስርወ መንግስት መፍትሄ አትጠብቁ የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው።

እኛና እነሱ?

ከወልዲያ የተሰማው ጥሩ አይደለም። ጎንደር ላይ እየሆነ ያለውም አዝማሚያው ያስፈራል። ባለፈው ሰሞን በጋሞጎፋ ሳውላ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የንግድ ቤቶች ቃጠሎ መልዕክቱ ግልጽ ነው። በደቡብ ኦሞ ከወራት በፊት በትግራይ ተወላጅ ሹፌር ላይ የተፈጸመው ግድያም የሚያሳየው ነገር አለ። በመቱ በቅርቡ የትግራይ ልጆች ላይ የተነሳው ተቃውሞ፡ በሀሮማያ ተማሪዎች የትግራይ ”ፎረም” ሰላዮች እንዲወጡላቸው ያቀረቡት ጥያቄ፡ እዚህ እዚያም የሚታየው ስሜት ለትግራይ ህዝብ ጥሩ መልዕክት ያለው አይደለም።

በህወሀት ዘረኛ አገዛዝ የተንገሸገሸው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ወገኑ ላይ አኩርፏል። እኛና እነሱ የሚል መስመር አበጅቷል። የእነ ጌታቸው ረዳን ”የትግራይ ህዝብ የበላይነት የለም” ቀረርቶ የሚሰማበት ትዕግስቱ ተሟጦ አልቋል። የትግራይ ህዝብ በተደጋጋሚ ጥሪ እየተደረገለት ነው። ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ሆኖ የአድዋን ስረወ መንግስት ይገረስስ ዘንድ ከልመና ያልተናነሰ ጥያቄ ሲቀርብለት ቆይቷል። ላለፉት 26 ዓመታት የትግራይ ህዝብ መስመሩን እንዲያስተካክል በተለያየ መልኩ ተጠይቋል። ነገር ግን ከዝምታና በአብዛኛውም ለህወሀት ጥብቅና ከመቆም ባለፈ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ ተግቢውን ምላሽ ሊሰጥ አልፈቀደም።

አሁን ነገሮች መልካቸውን ቀይረዋል። በየትኛውም የኢትዮጵያ መሬት ላይ ሳር ቅጠሉ ሳይቀር የትግራይን የበላይነት እየመሰከሩ ነው። የትግራይ ህዝብ መንቃት አለበት። ሆን ብሎም ከሆነ እየመጣ ያለው አደጋ ከማንም በላይ የትግራይ ወገናችንን የሚጎዳ ነው። ይህ ማስፈራሪያ አይደለም። መሬት ላይ የሚታይ እውነት ነው። ነገን እንደመስታወት የሚያሳይ የዛሬ እውነት።
የጄኖሳይድ ዎች ፕሬዝዳንት ግሪጎሪ ስታንተን ከዓመታት በፊት የተነበዩት በእርግጥም ያስፈራል። ስለትግራይ ህዝብ ትላንት ላይ ሆነው ስለነገው የተናገሩት ግሪጎሪ ስታንተን እኛና እነሱ የሚል መስመር ከተሰመረ አዝማሚያ መጥፎ ነው- የትግራይ ህዝብ አደጋ ላይ ነው- ሲሉ ቀድመው አስጠንቅቀዋል። የሚሰማቸው የትግራይ ተወላጅ አልነበረም። ይልቅስ ሰውዬውን መራገምና ጭቃ መቀባት የትግራይ ኢሊቶች ምላሽ ሆኖ አረፈው።

ይሀው የተፈራው እያንዣበበ ነው። እኛና እነሱ በግልጽ ተሰምሯል። ለኢትዮጵያችን ህልውና አደገኛ የሆነ የመጠፋፋት ፖለቲካ በየቀጠናው እየተደለቀ ነው። እናም የትግራይ ህዝብ ከብዥታ ውስጥ መውጣት ይጠበቅበታል። ድብን ካለበት የሰመመን እንቅልፍ መነሳት አለበት። ከትከሻው ላይ ተፈናጦ የሚጋልበውን ዘረኛ ቡድን ለማውገዝና ፡ ለመገዝገዝና ለመገነዝ በቶሎ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጎን ይሰለፍ ዘንድ አማራጭ የሌለው ምርጫ ቀርቦለታል። ጸሀይ እየጠለቀች ነው። ኢትዮጵያን ለማዳን የትግራይ ህዝብ ከምንጊዜውም በላይ ሃላፊነት ወድቆበታል።

አንድ ለመንገድ

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተቀምጧል። ከሌሎች ጊዜያት የተለየ ጠንካራ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል። ምን እንደሆነ አልታወቀም። የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውሶች የሚንጠው ስርዓቱ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገብቶታል። ምን አልባት የስፖርታዊ ውድድሮችን ላልተወሰነ ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ ሊያግድ ይችላል። ለዚህም ባለፈው ሳምንት ምልክት አሳይቷል። ዩኒቨርሲቲዎችን ለአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ ሊዘጋቸው እንደሚችልም ይገመታል። ኢትዮጵያን በተቆጣጠረ በሁለተኛው ዓመቱ አድርጎታል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዳግም ሊደነግግ ይችል ይሆናል። በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ዋጋ የሚያስከፍለው ቢሆንም ከመጣበት አደጋ የሚብስበት የለም። እናም የአድዋው ስረወ መንግስትን ውሳኔ በስሙ ለማሳለፍ የኢህአዴግ ኮሚቴ ተሰብስቧል።

ነገ የሚሆነው አይታወቅም። ዩኒቨርሲቲዎች አዳራቸውን በጭንቀት ውስጥ እንዳሉ እየሰማን ነው። ከሰሞኑ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ይቀላቀላሉ ተብሏል። የአማራ ክልል ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞ ይንጣቸዋል ተብሎም ከወዲሁ እየተገለጸ ነው። በየቦታው ወረቀቶች በመበተን ላይ ናቸው።
በእርግጥም ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ናት። የሚያስጨንቅ ምጥ ላይ ናት። በስልጣንና በዘር ፖለቲካ የሰከሩ ሳይሆን በፍቅር የሰከኑ ልጆቿ ሊነሱ ይገባል።

Filed in: Amharic