>
4:17 am - Tuesday January 31, 2023

የጋሽ ለማ ድራማ ...(ዮናስ ሃጎስ)

የጋሽ ለማ ድራማ «አግዐዚ ወደ ኦሮሚያ ክልል ገብቶ ንፁሃንን እንዴት እንደጨፈጨፈ የምናውቀው ነገር የለም..» ሃሃሃሃሃ…

ብልጦች አይደለንም።

•°•
ብልጣብልጦች ግን አያታልሉንም…
•°•
ጋሽ ለማ በድራማቸው ቀጥለውበታል። እኚህ የሐገር ፍቅር ትያትር ቤትን እያስጎመጁ ያሉት ተዋናይ ዛሬ ደሞ «አግዐዚ ወደ ኦሮሚያ ክልል ገብቶ ንፁሃንን እንዴት እንደጨፈጨፈ የምናውቀው ነገር የለም። ጨፍጫፊዎቹ እንዳለ በሕግ ይጠየቃሉ» የምትል ሲንግል ለቅቀው ሕዝባቸውን ባንድ እግሩ አቁመውታል።
•°•
ለማያውቅሽ ታጠኝ!
•°•
እስቲ ከመጀመሪያው አንስቶ ነገሩን በጥሞና እንየው…
•°•
አቶ ለማ የኦህዴድ መሪ ናቸው። ኦህዴድ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ነው። ኦህዴድ ኢህአዴግ ያስቀመጠውን ሕገ መንግስት በፅኑ የሚያከብርና የሚያስከብር ድርጅት ነው።
•°•
ዋሸው እንዴ?
•°•
ኦህደድ በሚደግፈውና በሚያስከብረው ሕገ መንግስቱ ላይ መንግስት ማርሻል ሎው (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚደነግግበት የሕግ መሰረት በግልፅ ቋንቋ ሰፍሯል። በኦሮሚያ ውስጥ የመንግስት ደህንነቶች እና ፅንፈኛ ብሔርተኞች በጋራ ሆነው የፈጠሩት ምስቅልቅል ሁኔታ ከሐገሪቷ መንግስት አቅም በላይ መሆኑን የሐገሪቷ መሪ ጠቅላይ ሚንስትር ሐይልሽ ለሕዝብ በተሰራጨ ንግግር በቀጥታ አምነው ይህን ችግር ለመፍታት ራሱ ኦህዴድ (ለማ) ጭምር የተወከለበት የብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት ምክር ቤት እንዲቋቋም መደረጉን አስረድተዋል።
•°•
አይደለም እንዴ?
•°•
ይህ ምክር ቤት ሲቋቋም በዚህ ምክር ቤት ስር ታዝዘው ወዴትም የሚዘምቱ ወታደሮች ወደሚዘምቱበት ቦታ እቅፍ አበባ ይዘው እንደማይዘምቱ አቶ ለማ አያውቁም ማለት ይሄ ዓለም እየመሰከረላቸው ያለውን ዝነኛ ብቃታቸውን ማሳነስ ነው የሚሆንብኝ። ይህ ምክር ቤት ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ወደ ተግባር ለመግባት አስፈላጊውን እንቅስቃሴ ሲያደርግ፤ ሎጂስቲኩን ሲያሟላና ጠመንጃውን ሲወለውል እንደ ምክር ቤት አባልነታቸው በሚቀርብላቸው ሪፖርት ሳያውቁ ይቀራሉ አይባልም። ከዚያ ውጭ ራሳቸው አቶ ለማ አባል የሆኑበት መንግስታችን መጀመሪያውኑም ይህን ምክር ቤት ያዘጋጀው ሕዝቡን ለማሸበር የሚፈፅማቸው ግድያዎችን «ሕጋዊነት» ለማላበስ መሆኑን አቶ ለማ በደንብ ጠንቅቀው ያውቃሉ።
እጅግ ዴሞክራት በምትባለው አሜሪካ ውስጥ ማርሻል ሎው ሲታወጅ ወደዛ የሚዘምቱ ወታደሮች ማንኛውንም ነገር ፈፅመው የአብዛኛውን ሕዝብ ደህንነት መጠበቅ እንዲችሉ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ በዚህ ወቅት ለሚወስዷቸው እርምጃዎች በሕግ እንዳይጠየቁ በቂ የሕግ ከለላ አላቸው። መጀመሪያውኑም ማርሻል ሎው የሚታወጀው ሌላው ዴሞክራት የሆነ አማራጭ ሁሉ ተሞኩሮ ሲያበቃ ነውና በማርሻል ሎው ሕግ የሚዘምቱ ወታደሮች ከሰማይ በታች ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ የመውሰድ አና አብዛኛውን ሕዝብ የመታደግ ተልዕኮ አንግበው ነው ጉዞ የሚጀምሩት።
በኛ ሐገርም ያው መንግስታት ማርሻል ሎውን ሕዝብን ለመጠበቅ ሳይሆን ሕዝብን በግድያ አስፈራርቶ ጨቁኖ ለመግዛት እንደሚጠቀሙበት የታወቀ ቢሆንም በሐገሪቷ ሕገ መንግስት ላይ የሚሰፍረው ግን እዚያ አሜሪካ ከሰፈረው የተለየ አይደለም። ስለዚህ እነዚህ ወታደሮች አቶ ለማ እንዳይናድ ሊጠብቁት በማሉለት ሕገ መንግስት በቂ የሕግ ጥበቃና ከለላ አላቸው።
•°•
አጠፋሁ? ካጠፋሁ ልጥፋ!
•°•
የዚህንም ምክር ቤት ምስረታ ከጥንስሱ የሚያውቁት፣ ከተመሰረተ በኋላም በአባልነት የሚሳተፉበት ሰውዬ ዛሬ በድንገት ብቅ ብለው ዓይናቸውን በጨው አጥበው (በነገራችን ላይ እኔ በቪድዮ አላየሁም። አሉ ተብሎ ግን በደጋፊዎቻቸው እየተሸለላቸው መሆኑን በግልፅ እያየን ነው) «ወደ ኦሮምያ ክልል የገባው ወታደር በማን ትዕዛዝ እንደገባ አናውቅም! ወታደሮቹ ለፈፀሙት ግድያም በሕግ ይጠየቃሉ!» የሚል ኢትዮጵያ ሱሴ የሚሸት ነገር ሲየላዝኑ መስማት በእውነት አንጀት ከመብላት በቀር ማንንም ሊያታልል አይገባም ነበረ። ምፅ!
•°•
ጭራሽ ዛሬ ከመሸ የሰማሁት ወሬ ደግሞ የበለጠ ግራ አጋብቶኛል። እነዚህ «ተላላኪ» የሚል ቅፅል ታፔላ የተለጠፈላቸው ኦህዴድና ብዓዴን፤ እነዚህ «ሕወሐት ነው አውሬው እንጂ እነርሱኮ ምስኪን በግ ናቸው…» የተባለላቸው ኦህዴድና ብዓዴን የኢህአዴግን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ «ስብሰባ ረግጠው ወጡ…» የሚል የ«ጀግንነት» ወሬ ሰምቼ ምን ብል ጥሩ ነው?
«ተመስገን በየነ ነው እንዴ ዜናውን ያነበበው?»
•°•
አዎና… ስብሰባ ረግጦ መውጣት እኮ በሰለጠነው በዴሞክራሲያዊ መንግስት በሚተዳደር ሕዝብ መሐከል የተቃውሞ ምልክት ነው። አንድ ጊዜ መንግስቱ ኃይለማርያም እውነት ይሁን ውሸት ባላውቅም በስብሰባ ላይ አላስፈላጊ የመሰለውን ጥያቄ የጠየቀ የኢሰፓ አባልን እዚያው እርምጃ አስወስዶበታል ይባላል። ጥያቄ ብቻ የጠየቀ አባል ይህ ከገጠመው ስብሰባ ረግጦ የወጣ አባል ምን እንደሚገጥመው አለማሰብ ነው። ታድያ «ኢህአዴግ አምባገነን ነው። ሕወሐት በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ የበላይነት አላት!» ምናምን እያሉ ሲያደነቁሩን የሚውሉ «ተቃዋሚዎቻችን» እንደገና ሕወሐቶች አምባገነን ካለመሆናቸው የተነሳ ስብሰባ ረግጠው የወጡ አባላቶቻቸው ላይ ምንም እርምጃ እንዳልወሰዱ ሊነግሩን ሲዳዳቸው የቱን አምነን የቱን እንደምንተወው ግራ ተጋባን እኮ?
•°•
አምባገነን ናቸው? እንግዲያውስ ስብሰባ ረግጦ የሚወጣ «ተላላኪያቸው»ን በምህረት ሊያልፉት አይገባም።
ዴሞክራት ስለሆኑ ስብሰባውን ረግጠው የወጡ አባላቶቻቸውን «አይ የሐሳብ ልዩነት ቢኖረን ይሆናል…» ብለው ዝም አሏቸው?
•°•
እነ አቶ ለማ በኢህአዴግ ውስጥ ያላመኑበት ውሳኔ ሲወሰን እንደ ተላላኪነታቸው ውሳኔውን ለማስፈፀም ቶሎ ከመሯሯጥ ይልቅ «በዚህ ጉዳይ ላይ ስለማናምንበት የዚህ ጉባዔ አባል ልንሆን አይገባም…» ብለው ስብሰባ ረግጠው በመውጣት የሚልኳቸውን ጌቶቻቸውን እስከ ማበሳጨት የመድረስ ዓቅም ካላቸው ምኑ ላይ ነው ተላላኪነታቸው? ኧረ በአንድ ቋንቋ እያወራን እንደ ባቤል ግንብ አንሁን?
•°•
ተወደደም ተጠላም የብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት ምክር ቤት ስራውን መጀመሩን በጨለንቆ በገደላቸው 15 ንፁሃን በተግባር አሳይቶናል።
ተወደደም ተጠላም አቶ ለማና አቶ ገዱ እዚህ ምክር ቤት ውስጥ ውክልና አላቸው።
ተወደደም ተጠላም አቶ ለማና አቶ ገዱ ወደ ጨለንቆ የዘመቱት ወታደሮች በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ መሰረት በሕግ ያለመጠየቅ ሙሉ መብት እንዳላቸው አሳምረው ያውቃሉ።
ተወደደም ተጠላም የጨለንቆ ገዳዮችን ያሰማራው ምክር ቤት አባል የሆኑት ብዓዴንና ኦህዴድ በጨለንቆ ለጠፉት ነፍሳትም ሆነ ነገ ከነገ ወዲያ ለሚጠፉ ሌሎች ነፍሳቶች ከሕወሐት ባልተናነሰ 100% ተጠያቂ ናቸው። (ተጠያቂ ስንል በሕሊና ፍርድ እንጂ ሕገ መንግስቱማ ነፃ እንዳወጣቸው ከላይ በደንብ አብጠርጠሬ አሳይቻለሁኝ።
•°•
ስለዚህ ይህቺ በOBN የተሰራችው ድራማ የለማን ደጋፊዎች ጮቤ ታስረግጥ እንጂ ለኛ ብልጣብልጥ ባንሆንም ብልጣብልጦች ለማያታልሉን ነቄዎች ግን ምናልባት አቶ ለማ በሐገር ፍቅር ቲያትር ቤት ወደፊት ሲቀጠሩ ሲቪያቸውን ሟሟያ ሊያደርጓት ከመቻላቸው ውጭ ቅንጣት ትርጉም የሌላት መሆኗን እንገነዘባለን።
•°•
ምን ተሻለ?
•°•
ኦህዴድና ብዓዴን እውነት ሪፎርም ላይ ከሆኑ ማድረግ የሚገባቸው ተፈጥሯዊው ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ሊያደርገው ከማይችለው ዲሞክራሲን በስሙ ውስጥ በማካተቱ ብቻ ዴሞክራሲያዊ መሆን እንደማይችል ከማይገባው (ገ ትላላለች) ከኢህአዴግ ራሳቸውን በፍጥነት ማግለል ብቻ ነው።
•°•
አንዳንድ ሰዎች ኦህዴድ ራሱን ከኢህአዴግ ካገለለ ኦሮሚያን ያጣልና ትግሉን ማጠናከር አይችልም የሚል መላ ምት ያቀርባሉ… ይሄም ሕገ መንግስቱን ካለማወቅ የመነጨ ነው። ኦህዴድ የኢህአዴግ አባል ሆነ አልሆነ በባለፈው ምርጫ ኦሮሚያን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የመግዛት መብቱን 100% ተጎናፅፏል። ይህንን በጠመንጃ ካልሆነ በቀር ሊቀማው የሚችል አንድም ኃይል የለም። ስለዚህ ኦህዴድ ከኢህአዴግ አባልነት ቢወጣ በነፃነት ኦሮሚያን እስከሚቀጥለው ምርጫ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣኑ በሕገ መንግስት የተረጋገጠ ነው።
•°•
እዚህ ላይ አንድ አናንያ የሚባል ወዳጄ «ባክህ አስሬ ሕገ መንግስት ሕገ መንግስት አትበልብን!» ብሎ እንደሚጮህብኝ አውቃለሁኝ። እሺ ሕወሐት ሕገ መንግስቱን እንደማያከብር እኔም አምናለሁኝ። ታድያ ምንድነው መፍትሄው? አሁንም እኮ መከላከያው ኦሮምያን ከነለማ እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት ጠመንጃውን ወልውሎ ዘምቷል። በቲዎሪ ስናየው አንደኛው አዝማችም እነርሱ ናቸው። ታድያ አዘማችም ሆነው እንደገና ወቃሽም ሆነው ግራ ያጋቡን ወይንስ በዚያው ድራማ በሚሰሩበት ቴሌቭዥናቸው በይፋ ቀርበው «ኢህአዴግ የሚባለው ነገር ውሸት ነው! ኢህአዴግ የሚባለው ሕወሐት ሐገሪቷን ጠቅልሎ ለመግዛትና የትግራይ የበላይነት ለማስፈን ሲል የፈጠረው ድሪቶ ነው። ስለዚህ ኢህአዴግን ከውስጥ ሆነን ልንቀይረው ስላልቻልን ራሳችንን ሕገ መንግስቱ በሚፈቅድልን አሰራር መሰረት ከኢህአዴግ አግልለናል። ከዚህ በኋላ በኦሮምያ የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ ከኢህአዴግ ጋር አንዳችም ንኪኪ በማይኖረው ሪፎርምድ የኦህዴድ አመራር ብቻ የሚመሩ ይሆናሉ!» ብሎ ጉዱን አፍረጥርጦ ከዚያ በኋላ የሚመጣውን ማናቸውም ነገር ከሕዝባቸው ጋር ሆነው ቢቀበሉ ይሻላቸዋል?
•°•
ኦህዴድ የኛንም ሆነ ወጥ በሆነ መልኩ የኦሮምያን ሕዝብ ድጋፍ ከፈለገ ራሱን ከዚህ ኢህአዴግ ከተባለ ቫይረስ ያላቅቅ። ጀለሴ ሌላ የማርያም መንገድ የለም።
•°•
አጠፋሁ እንዴ? ዋሸሁ አንዴ? አይደለም እንዴ?

Filed in: Amharic