>
6:28 am - Wednesday July 6, 2022

የታኅሳሱ ግርግር (የወንድማማቾቹ መፈንቅለ መንግሥት) 57ኛ ዓመት መታሰቢያ

አምደጽዮን ሚኒሊክ

የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት ለመገልበጥ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተካሄደው ከ57 ዓመታት በፊት ነበር፡፡

በወንድማማቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይና ገርማሜ ነዋይ የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለምስኪኗ ኢትዮጵያ የተሻለ የአስተዳደር ስርዓት ለማምጣት ታልሞ የተደረገ እንደነበር ይነገራል፡፡

በታኅሣስ ወር 1953 ዓ.ም ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለጉብኝት ወደ ብራዚል መሄዳቸውን ተከትሎ፣ የክብር ዘበኛ ጦር አዛዡ ብርጋዲዬር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ እና በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ከተማሩት ታናሽ ወንድማቸው ገርማሜ ነዋይ ጋር መከሩ፡፡

ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራውን ሃሳብ የጠነሰሱት ከወቅቱ የፀጥታ/ደህንነት ክፍል ኃላፊው ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ እና ከፖሊስ ኃይል አዛዡ ከብርጋዴር ጀኔራል ጽጌ ዲቡ ጋር ሆነው ነበር፡፡ ታኅሳሥ 5 ቀን 1953 ዓ.ም (ከዛሬ 57 ዓመታት በፊት) የወንድማማቾቹ ቡድን ዓላውን ለሕዝብ ይፋ አደረገ፡፡

የተሻለ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስሪት ያላትን ሀገር እውን ለማድረግ ፍላጎት/ዓላማ እንዳለው ገለፀ፡፡ ‹‹ለውጥ ፈላጊ ናቸው›› የሚባሉት ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሾማቸውንና አልጋ ወራሹን አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴንም በማስማማት (‹‹አስገድደው ነው›› የሚሉም አሉ) መንግሥት በቆረጠላቸው ደመወዝ እየተዳደሩ ለሕገ መንግሥት የሚገዙ ንጉሥ ሆነው እንደሚያገለግሉ እራሳቸው ለሕዝቡ በራዲዮ እንዲያስተላልፉ አደረገ።

በቀጣዩ ቀን በወንድማማቾቹ የተጠነሰሰውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሚቃረነው የነጄኔራል መርዕድ መንገሻ ኃይል ሙከራውን ለማክሸፍ ዝግጅቱን ጨርሶ በዓየር እና በታንክ ጭምር የተፋፋመ ውጊያ ሲጀምር ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ መምሪያ ክፍላቸውን ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት አዛወሩ።

በቀጣዮቹ ቀናት የምድር ጦሩንና የአየር ኃይሉን ያላሳተፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተዳከመ፤ በአንጻሩ ደግሞ የንጉሱ ታማኞች እያደር እየበረቱ መሄዳቸውን የተገነዘቡት እነብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ በቁጥጥራቸው ስር የነበሩትን መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሚኒስትሮችንና መኮንኖችን ወደ ሌላ ቦታ አዛውረው፣ አልጋወራሹንና አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ ለብቻቸው እንዲጠበቁ ያደርጋሉ።

ጄኔራል ጽጌ ዲቡ ወዲያው ከተቃራኒ ወገን በተተኮሰ ጥይት ሲገደሉ፣ እነ ብርጋዴር ጄነራል መንግሥቱ ደግሞ የያዟቸውን እስረኞት ረሽነው ለማምለጥ ወስነው ራስ አበበ አረጋይ፣ ሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ራስ ስዩም መንገሻ፣ አቶ መኮንን ሀብተወልድ፣ አባ ሐና ጅማና ሌሎች የንጉሰ ነገሥቱ ባለስልጣናት ተረሽነው ሞቱ። በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥም የሞቱ ባለስልጣናት ነበሩ፡፡ ከነዚህም መካከል የስመ ጥሩው አርበኛ የኃይለማርያም ማሞ ልጅ እና የንጉሠ ነገሥቱ የልጅ ልጅ የልዕልት ሶፊያ ደስታ ባል የሆኑት ሻምበል ደረጀ ኃይለ ማርያም ይጠቀሳሉ፡፡

ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴም ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ተሳትፈዋል የተባሉት ወገኖችም እየታደኑ ተገደሉ፡፡ የመንግሥት ግልበጣው መሪ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይም ተይዘው በስቅላት ተቀጡ፡፡ ወንድማቸው ገርማሜ ነዋይ ደግሞ በሽሽት ላይ ሳሉ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ተገደሉ፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውም ይችን ምስኪን አገር ብዙ ጀግኖችን አሳጥቶ ሳይሳካ በአጭሩ ተቀጨ፡፡

ምንጮች፡

፩. የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከ1847-1983 (ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ)
፪. ልዩ ልዩ ድረ-ገፆች

ምስኪን ሀገር – ኢትዮጵያ!

Filed in: Amharic