>

የአብዲ ኢሌ ቀኝ እጆችና በጭፍጨፋው ተዋናይ የሆኑት በሀርጌሳ መሸሺግያ እያመቻቹ ነው (በወንድወሰን ተክሉ)

 ም/ል ፕሬዚዳንቱ፣ የልዩፖሊስ አዛዥን ጨምሮ አራት ባለስልጣናት ሀርጌሳ ገብተዋል

 

የሱማሌ ክልል መስተዳድር ባለስልጣናት በተለይም የአብዲ ኢሌ የቀኝ እጅ የሚባሉ ባለስልጣናት ለተለየ ተልእኮ ሶማሌ ላንድ ሀርጌሳ መግባታቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በሀርጌሳ ያለው ምንጫችን አህመድ አብዲ እንደገለጸው የሶማሌው ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል ዋና አዛዥ እና የአብዲ ኢሌ አጎት የሆነው አብዱራህማን ለበጎሌ፣የሶማሌ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንት አብዱከሪም ኢጋል፣በሱማሌ ክልል ስልጣን ተዋረድ ሶሰተኛ ሰው የሆነውና የአብዲ ኢሌ ሁለተኛ ሚስት ወንድም ከድር ዴሬና ሌሎች ባለስልጣናት በሀርጌሳው ም/ል ፕሬዚዳንት ሴሌህ ቤት ምክክር እያደረጉ መሆናቸውን ይገልጻል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በአፋር ሰማራ ከተማ በተከበረው በ12ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እለት ከፌዴራሉ መንግስት በተለይም አሁን ወደ ስልጣን በመጡት የህወሃት ባለስልጣናት አቶ አብዲ ኢሊ በምስራቁ ጭፍጨፋ እጃቸው አለበት የተባሉትን ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር እንዲያውል መታዘዙን ምንጫችን ይናገራል።
በምስራቅ ኦሮሚያ በተፈጸመው ጭፍጨፋ በኦሮሚያ በኩል ተጠርጣሪ የተባሉ 96ሰዎች በኦሮሚያ ክልል ፖሊስና በፌዴራሉ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር መገናኛ ቢሮ ሃላፊ መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን በሶማሌ ክልል ከሚፈለጉት ከ50በላይ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ስድስት ያህሉ ብቻ እንደተያዙ መገለጹ አይዘነጋም።

የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ኢሌ ተጠርጣሪዎችን አሳላፎ እንዲሰጠ የሚቀርብለት ተጽእኖ ከእለት ወደ እለት እየበረታ በመምጣቱ በተፈላጊነቱ ቁጥር አንድ ላይ ያለው የልዩው ፖሊስ አዛዥ አብዱራህማን ለበጎሌ ለሶስት ወር ለሚቆይ እስር እንዲታሰርለት ሊያግባባው ሞክሮ እንዳልተቀበለው ምንጫችን ይገልጻል።

አብዲ ኢሌ የልዩ ፖሊስ ሃይል አዛዡን ለበጎሌን ለሶስት ወራት ለማስመስል ታሰርልኝ ለሚለው ጥያቄ”መታሰር ካለብኝ ሁለታችንም ለመታሰር ዝግጁ ነኝ” ማለቱንና “በአንተ ትእዛዝ አብረን ሰርተን እኔ ለብቻ የምታሰርበት ምክንያት የለም” በማለት ከጂጂጋ ወጥቶ በደጋቡህር፣ቀብሪደሃርና ሺላቦ ላለፉት አራት ቀናት እንደቆየ ከምንጫችን መረጃ ማወቅ ተችሏል።

ሁኔታው ያሳሰበው አብዲ ኢሌ ትናንት ም/ል ፕሬዚዳንቱን እና የሁለተኛ ሚስቱን ወንድም ከድሬ ዴሬ የሚመራ ቡድን በበረሃ ያለውን አብዱራህማን ለበጎሌን ይዘው ወደ ወደጁ የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት ሙሳ ቢህ ወዳጆቹን በሚሸሽግበትና ብሎም ከሀርጌሳ በሚያስወጣበት ጉዳይ እንዲመክሩ ልኳቸዋል ሲል የምንጫችን መረጃ ይገልጻል።
የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት ሙሳ ቢህ በቅርቡ በህዳር ወር የተመረጡ ሲሆን አብዲ ኢሌ ከፍተኛውን የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብ በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት የረዳቸው ወዳጁም እንደሆኑ መረዳት ተችሏል።

በሃርጌሳ ያሉት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል ዋና አዛዥን ጨምሮ ሁሉም የሶማሌን ፓስፖርት የያዙ መሆናቸው ምንጫችን ገልጾ በሁለቱ ባለስልጣናት መካከል በደህንነት እና ጸጥታ ዙሪያ እንዴት እንደሚተባበሩና እንደሚረዳዱ የመከሩ ቢሆንም ዋናው አጀንዳ ግን በፌዴራሉ መንግስት ሊታሰሩ ይችላሉ ተብለው የተጠረጠሩትን የአብዲ ኢሌን ሹማምንቶች በመሸሸግና በመጠበቅ ዙሪያ ያነጣጠረ ነው ሲል ምንጫችን አህመድ ገልጾልናል።

በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መሰረት የክልል መንግስት ከማእከላዊው የፌዴራል መንግስት በኩል ከመንግስታት ጋር ይገናኛሉ ቢልም የዚህ የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት የሀርጌሳ ጉዞ በፌዴራሉ መንግስት እውቅና ስር ስለመሆኑ የተገለጸ ነገር የለም።

Filed in: Amharic