>

ህወሀት እንዳበደ ውሻ ተቅበዝብዟል-ያሳደጋቸው ባሪያዎቹ ፈንግለውታል። በረቱን ሰብረው ወጥተዋል!!

መሳይ መኮንን

የትግራይ የበላይነት’ በኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች የሰሞኑ ስብሰባ የፍጥጫ አጀንዳ ሆኗል። ኦህዴዶች ”የበላይነቱ” እስከመቼ ሲሉ ወጠረው ይዘዋል። ብአዴኖች አጉረምርመዋል። ህወሀት ይህ ጥያቄ እንዴት ይነሳል ሲል እየፎከረ ነው። በቅርቡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ‘የትግራይ የበላይነት የለም ብለን ከስምምነት ደርሰናል’ ያሉት መግለጫ ውሃ ብልቶታል። በተቃዋሚው መንደር ለዘመናት ሲነገር የነበረው፡ የነጻነትና የዲሞክራሲ ሃይሎች ሲወተውቱ የከረሙት፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አደጋ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ በስጋት ሲገለጽ የዘለቀው፡ ‘የበላይነት’ ዛሬ በኢህአዴግ ሰፈር ፈንድቶ ወጥቷል። ጊዜ ደግ ነው። ገና ብዙ ያሳየናል።

ሰሞኑን እየተካሄደ ያለው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ከፍተኛ ፍጥጫ የታየበት እንደሆነ ይነገራል። ህወሀት ‘ውስጤን አጽድቼአለሁ። ተራው የእናንተ ነው’ ብሎ የኦህዴድንና የብአዴንን ጉሮሮ አንቆ ይዟል። ሁለቱ ድርጅቶች አፍንጫህን ላስ ዓይነት ምላሽ እየሰጡት ናቸው። ህወሀት የለማንናን የገዱን ቡድኖች ጠራርጎ ለማስወገድ እንቅልፍ አጥቶ አድሯል። በሁለቱ ክልሎች ለተባባሰው ቀውስ ተጠያቂ አድርጎ እየጠዘጠዛቸው ሲሆን እነሱም የሚበገሩ አልሆኑም። በጸጥታና ደህንነት መስሪያ ቤቱ ውክልናችን አንሷል የሚል ጥያቄ በድፍረት ማንሳታቸው ይነገራል። ህወሀት ለሩብ ክፍለዘመን የዘለቀበት የጌታና ሎሌ ጨዋታ እያበቃ መሆኑ አስደንግጦታል። እንዳሻው የሚፈነጭበት፡ እንደፈለገ የሚፈነጥዝበት ዘመን ማክተሙን የሚያሳዩ ፍንጮችን ማየቱ ብርክ አሲዞታል።

የኢህአዴግ ሰሞንኛው ስብሰባ የህወሀትን ቀጣይ ህልውና የሚወስን ይመስላል። ከወዲሁ ስብስቡን ለማፍረስ የደህንነት(ሰቆቃ) ሚኒስትሩ ጌታቸው አሰፋ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሀገሪቱን መምራት ስላልቻለ እንዲበተን ሀሳብ ማቅረቡ ተሰምቷል። በስብሰባው ኦህዴዶች ከአባይ ጸሀዬ ጋር ዱላ ቀረሽ የቃላት ልውውጥ ውስጥ ገብተው እንደነበርም ታውቋል። የጨለንቆው ጭፍጨፋ ለኦህዴዶች ጥሩ የማጥቂያ ዱላ ሆኗቸዋል። በመከላከያ ሰራዊት የተፈጸመው ዘግናኝ ግድያ ያስቆጣቸው ኦህዴዶች እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ሰብሰባውን እያካሂዱት ነው።

ህወሀትም ከዚህ ማምለጫ ሴራ መጎንጎን ጀምሯል። እነለማን ለማስደንበር በኦህዴድ ስም በሶማሌ ክልል ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ማካሄዱ እየተነገረ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በርካታ የሶማሌ ክልል ተወላጆች ከትላንት በስቲያ ተገድለዋል። የኦህዴድ ታጣቂዎች ፈጽመውታል የሚል ወሬ በህወሀት በኩል እየተራገበ ነው። እነለማን አፍ ለማሲያዝ ብሎም በወንጀል አሸማቆ ወደ እስር ቤት ለመወርወር የተጎነጎነች ጊዜ ያለፈባት ሴራ እንደሆነች መጠራጠር ሞኝነት ነው።

ህወሀት እነኩማ ደመቅሳን ከአውሮፓ አስመጥቶ፡ ግርማ ብሩንና ወርቅነህ ገበየሁን ከፊት አሰልፎ የነለማን ቡድን ለመምታት ተዘጋጅቷል። በአማራ ህዝብ ዘንድ ታሪካዊ ጠላት ሆኖ ከአሳፋሪ ተግባሩ ጋር በጥቁር መዝገብ ላይ የሰፈረው አለምነው መኮንን ገዱንና በገዱ ዙሪያ ያሉትን ለመመንጠር ከህወሀት ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። የለማና ገዱ ሰመራ ላይ የታየው ፍቅር በህወሀት መንደር አጥንት ድረስ የዘለቀ ስጋት ፈጥሯል። ይህ ስብሰባ ይህን ፍቅር ለመበጣጠስ የታቀደ ነው። የኦሮሞና የአማራ ህዝብን አንድነት ማፈራረስ ግቡ ያደረገ ነው። በኦህዴድና ብአዴን መሀል የሚታየውን የትብብር መንፈስ ለማጥፋት ያለመ ነው።

ህወሀት እንዳበደ ውሻ ተቅበዝብዟል። ያሳደጋቸው ባሪያዎቹ ፈንግለውታል። በረቱን ሰብረው ወጥተዋል። ለዘመናት እጃቸው ላይ የታሰረውን ሰንሰለት በጥሰዋል። ኦህዴዶችና ብአዴኖች ከዚህ በኋላ ካፈገፈጉ አደጋው ከባድ ነው። ህዝብ ከዳር እሰከዳር በተነሳበት፡ የህወሀትን ዕድሜ የሚያሳጥር ትግል በተፋፋመበት በዚህን ወቅት የህወሀትን ዱላ ፈርተው እጅ ይሰጣሉ የሚል እምነት የለኝም። ከዚህ የኢህአዴግ ስብሰባ የሚጠብቁት ውጤት እንደሌለ ማወቅ አለባቸው። ይህኛው ስብሰባ የህወሀትን የበላይነት ለማጽናት፡ ዳግም ለማረጋገጥ የተዘጋጀ ነው። በመቀሌ የተቀመመውን መርዝ የሚረጭበት መድረክ እንደሆነ ለአፍታም መጠራጠር አይገባም። እነዚህ ሃይሎች በትንሹ ማድረግ የሚገባቸው ነገር ቢኖር የሰሞኑን ስብሰባ ረግጠው መውጣት ነው።

የእነለማ ልብ ከህዝብ ጋር ሆኖ መዝለቁ ይጠቅመዋል። ተስፋ ከሰጡት ወገናቸው ጋር እስከመጨረሻው መቆም አለባቸው። ለህውሀት ጀርባቸውን ሰጥተው ህዝባቸውን ማዳመጣቸው የህልውና ጉዳይ መሆኑ አይጠፋቸውም። ከህውሀት ጋር ሆነው ለሰሩት ሃጢያት ህዝብ ከውስጡ ይቅር እንዲላቸው በጀመሩት ጎዳና መቀጠል ምርጫ የሌለው አማራጭ ነው። ደግሞም ብቻቸውን አይደሉም። የህወሀት ጌቶች የሆኑት ምዕራባውያንም ስለለውጥ አብዝተው እየመከሩ ነው። ከህወሀት ውጭ እያሰቡ ነው። ለእነ ለማ ይህ ጥሩ ዜና ነው።

አዎን! አውሮፓውያኑ ተቃዋሚዎችን እያነጋገሩ ነው። የህወሀት አገዛዝ የቀውስ እንጂ የመፍትሄ አካል እንዳልሆነ ተገልጦላቸዋል። በተለይ መሳሪያ ያነሱትንም ጭምር ጠርተው ፍኖተ ካርታችሁን አሳዩን ማለታቸው በአገዛዙ ተስፋ መቁረጣቸውን የሚያመላክት ነው። አሜሪካውያኑም ውስጥ ውስጡን እየመከሩበት እንደሆነ ይነገራል። ህወሀትንና ሻዕቢያን አዝለው ለቤተመንግስት ያበቁት የአሜሪካን ዲፕሎማቶች ሰሞኑን የሚናገሩት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በወቅቱ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት የነበሩትና ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማሪያምን በጓሮ በር አስወጥተው፡ ህወሀትን በፊት ለፊት ያስገቡት ሀርማን ኮህን ”ህግና ስርዓት ከመፋለሱ በፊት ሁሉንም ያሳተፈ ጉባዔ” እንዲካሄድ ጥሪ አድርገዋል። ሌላው ዲፕሎማት ዶናልድ ያማማቶም አዲስ አበባ ከርመዋል። አንዳች የሽግግር መንግስት የሚመስል ንግግር ሳይጀምሩ አይቀርም የሚል መረጃ ሾልኮ ወጥቷል።

ኢትዮጵያ በጣም አደገኛ በሆነ መስመር ላይ ናት። በአንጻሩም ተስፋ በሚሰጥ ጎዳና ላይ ወጥታለች። የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሉን በጋራ አድርጎ ከያለበት ተመሳሳይ ድምጽ ማሰማቱ ተስፋ የሚሰጥ ሲሆን የህወሀት አገዛዝ ከጠፋሁ ብቻዬን አልጠፋም በሚል እያካሄደ ያለው የዘርና ጎሳ ግጭት ደግሞ ስጋትን የሚፈጥር ነው። ተስፋውና ስጋቱ እኩል ቆመዋል። ሁለቱም ከኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ተደቅነዋል። ተስፋውን የማለምለም፡ ስጋቱን የመቀነስና ብሎም የማጥፋት የወቅቱ አንገብጋቢ የቤት ስራ ነው።

Filed in: Amharic