>
7:34 pm - Friday October 22, 2021

ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ -''አባ መላ'' (ዘ ሚካኤል)

ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ(አባ መላ)
የአጤ ምኒሊክ የጦር ሚኒስትር የነበሩት ፊታውራሪ ሀብቴ አባ መላ በሚል ቅፅል ስምም ይታወቃሉ ። እስቲ የአባ መላን ጥቂት አስገራሚ የፍርድ ታሪኮች እንይ።
አንድ
¤¤¤¤¤
ፊታውራሪ ሀብቴ ሚስታቸው ከወታደር ጋር ስትወሰልት ትገኝና ሚስትና ወታደር እግር ተወርች ታስረው ፊታቸው ይቀርባሉ ። አባ መላም እንዲፈቱ ካዘዙ በኋላ ሁለቱንም ለየብቻ ያናግሩና ሚስትና ወታደር በፍቅር እንደወደቁ አውቀው ደግሰው ሚስታቸውን ለወታደራቸው ይድራሉ። አጤ ሚኒሊክ ታሪኩን ሰምተው ኖሮ አባ መላ ጋር ሲገናኙ” እንዲያው ቆይ በሚስትህስ አልጨክን ብለህ ነው ልበል፣ ያን ባለጌ ወታደር አለመግደልህ ሲገርመኝ እንዲያው በግርፋት አትመልጠውም ኖሯል?!” ሲሉ በአግራሞት ጠየቋቸው። ” አየ ጃንሆይ!! እንዲያው ለዚህ ሳያጥቡት ለሚገማ፣ ሳይወጉት ለሚደማ ጎደሎ ብዬ የሰው ነፍስ ላጥፋ?!” አሉ በሳቅ ታጅበው!!

¤¤¤¤
ሁለት
ሴትዮዋ መልከ ቀና ኮማሪት ነበረች ።ታዲያ በተደራቢ ለከደንበኞቿ ጋር ገንዘብ እየተቀበለች ታድራለች ( ያው በወሲብ ንግድ መተዳደር እንበለው በዘመነኛው) ። አንድ ደንበኛዋ ታዲያ በፍቅሯ ይወድቅና አብረው መኖር ይጀምራሉ ። በኋላ ኑሯቸው እየደረጀ ጎጇቸው በሀብት እየተሞላ ይመጣል። አመታት እያለፉ ሲመጡ የሰውዬው ዘመዶችእንዴት እንዳንት ያለ የከበረ ጌታ ከኮማሪት ጋር ይኖራል ብለው ይመክሩትና እንፋታ ይላታል ። ሀብቱ ሁላ በስሩ ነበርና እሷ ሜዳ ላይ ልትቀር ሆነ ። በየደረጃው በክስ ብትሄድም መላ የሚላት እያጣች ፍርድ ሁሉ ለሱ እየሆነ በመጨረሻ ” ይግባኝ ለጃንሆይ !!”ትላለች። ጃንሆይም ሊያስማሟቸው ቢሞክሩ ባል ወይ ፍንክች የአባ ቢለዋ ልጅ!! በመጨረሻ አጤ ምኒሊክም እያዘኑ ለባል ይፈርዳሉ።
” ይግባኝ ለፊታውራሪ ሀብተ ገከዮርጊስ!!” ትላለች ሰማይ የተደፋባት ከሳሽ። ” ወግጂ ይቺ ከጃንሆይ ወዲያ!!” ብሎ በዙፋን ዙሪያ ያለ ሲፎገላ ” ቆይ ቆይ !!”አሉ ጃንሆይ ተረጋግተው ። ” አባ መላ መፍትሄ ካገኘላት ምናለ ይይላት!!” አባ መላ ግራ ቀኙን ከሰሙ ወዲያ ባልን በዚህ ቢሉ በዚያ አልበገር ይላል!! በመጨረሻ እንዲህ ሲሉ ሴትዮይትን ጠየቋት። ” ለመሆኑ መጀመሪያ ቀን አብራችሁ ስታድሩ ስንት ብር ከፈለሽ?” ” አምስት ብር!” ሴትዮይት መለሰች። ” አብራችሁ መኖር ከጀመራችሁ ስንት ጊዜ ሆነ?!” ” አምስት አመታችን ሰኔ ሚካኤል ላይ አለፈ!” “በጄ!” አሉ አባ መላ ” በጄ በል እንግዲህ መጀመሪያ ቀን የከፈልካትን ብር በአምስት አመቱ ቀናት አባዝተህ ሙሉ ሂሳቧን ክፈላትና ፍቺውን መፈፀም ትችላለህ!” ባል ፊቱ ሳምባ መሰለ !! ወዲያው ሚስቱ እግር ስር ተደፋና ” ይቅር በይኝ እናቴ መካር አሳስቶኝ ነው!!”
ሶስት
¤¤¤¤¤¤
እንግሊዞች አጤ ሚኒሊክ ዘንድ ይቀርቡና በመቅደላ ጦርነት ወቅት የኛ ወታደሮች የሞቱበት መሬት ይሰጠን! ! ወገኖቻችን ተቀብረውበታልና ይላሉ። አጤ ሚኒሊክም ጉዳዩን ወደ አባ መላ ይመሩታል። አባ መላም ነገራቸውን ከሰሙ በኋላ ” በጄ ይሁን ብለናል! ! ፈቅደናል! !” አሉ። እንግሊዞችም ቂጣቸውን በካልቾ እየመቱ እየፈነጠዙ ሊወጡ ሲሉ “ቆይማ!” አሉ አባ መላ ። ” እንግዲህ የአጤ ቴዎድሮስ ልጅ ልኡል አለማየሁ የተቀበረባት ሎንዶን ለኛ የምትገባ መሆኗንም አትርሱ!!” እንግሊዞች እንደድመት ዱካቸው ሳይሰማ ሹልክ!!
አራት(እና የመጠረሻ!)
¤¤¤¤¤¤¤
ከውጭ የመጡ ሰዎች ከፊታውራሪ ጋር ሊወያዩ ብለው ማይንድ ጌም ፈልገው ኖሮ ” እንግሊዝኛ ቋንቋ  ችላሉ?”” አልችልም!”
“ፈረንሳይኛስ?!”
” አልችልም!”
” ፖርቹጊዝ!”
” እሱንም አላውቅም!!”
” ታዲያ እንዴት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆኑ??!!”
” ቆይማ ልጠይቅህ አማርኛ ቋንቋ ትችላለህ?!”
” አልችልም!”
” ኦሮምኛስ!?”
” አልችልም!”
” ጉራጌኛስ?!”
” እሱንም አላውቅም!”
” ኋላ እንዴት ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ትወያይ ዘንድ ተመደብክ??!”
እሾህን በሾህ!!

Filed in: Amharic