•°•
አቶ ለማና ካቢኔያቸው በቃን ያሉት ነገር በውል ለይቶ አልታወቀም። በቃን ያሉት በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን የሕወሐት የበላይነትን ይሁን ተቃዋሚዎች አለ ብለው የሚያስቡትን የትግራይ የበላይነት ይሁን የኢህአዴግን ስርዓት አልበኝነትን ከማቆምና ሕገ መንግስቱ በራሱ ኢህአዴግ እንዲከበር ከማድረግ ይሁን ለሕዝብ የሚጠቅም ዴሞክራሲያዊ መንግስት ከመመስረት አንፃር ይሁን እስካሁን የተረጋገጠ ነገር የለም። ነገር ግን የእያንዳንዱን ጥያቄ ሁኔታ ለየብቻው በማየት የሚፈጠረውን ነገር አስቀድሞ መገመት የሚከብድ ነገር አይሆንም።
•°•
1) የሕወሐት የበላይነትን በቃን ካሉ…
ኢህአዴግ ውስጥ ያለውን የሕወሐት የበላይነት እዚያው ኢህአዴግ ውስጥ ሆነው ለመታገል ከወሰኑ በኢህአዴግ አሰራር መሰረት ከብዓዴን በተጨማሪ የደኢህዴግን ድጋፍም ሊያገኙ ግድ ይላል። ምክንያቱም የኢህአዴግን በወረቀት ላይ የሰፈረ አካሄድ ከተከተልን ስራ አስፈፃሚው 36 የምክር ቤት አባላት ሲኖሩት ብዓዴንና ኦህዴድ 18 ሕወሐትና ደኢህዴግ ደግሞ 18 ድምፅ ይኖራቸዋል። ሕወሐት ብዓዴን ውስጥም የራሷን ታማኞች አስቀምጣለችና ሚዛኑ ወደርሷ ማጋደሉ አይቀርም። ኦህዴድ ኢትዮጵያ ሱሴን ነጠላ ዜማውን ወደ ደቡብ ክልል መውሰድ የቻለ አይመስልም። ስለዚህ ኦህዴድ በኢህአዴግ ስርዓት ውስጥ ታቅፎ ይህን ሊቀይር የሚችልበት አንዳችም እድል የለውም።
•°•
2) ተቃዋሚዎች አለ የሚሉትን የትግራይ የበላይነት ከሆነ በቃን ያሉት…
•°•
ይሄን ነገር በቲዎሪ እንኳን አንስቶ ለመወያየት ይከብዳል። ምክንያቱም ሁሉም ክልል የሚያስተዳድረው ራሱን ነው። በእርግጥ ፌደራሉን ባመዛኙ የምትቆጣጠረው ሕወሐት ደህንነቷና መከላከያዋ በፈለገችው ክልል እንደፈለገች እንድትፈነጭ መንገድ የከፈቱላት ቢሆንም ቅሉ ይሄ የሚወስደን በአንደኛ ተራ ቁጥር ወደተጠቀሰው የሕወሐት የበላይነት እንጂ የትግራይ የበላይነትን አያሳይም። ያም ሆነ ይህ የትግራይ የበላይነቱ ካለ እንኳ ለማስወገድ መጀመሪያ የሕወሐት የበላይነትን ማስወገድ ግድ ይለዋል።
•°•
3) የኢህአዴግ ስርዓት አልበኝነትን ከማስቆምና ሕገ መንግስቱ እንዲከበር ከማድረግ አንፃር ከሆነ በቃን ያለው…
•°•
ከላይ እንደተጠቀሰው ይህ ኢህአዴግ ከተመሰረተበት ስረ መሰረቱ ጋር የሚጋጭና ከራሱ ከኦህዴድ ጀምሮ የብዙ ኢህአዴግ አባላትን ጥቅም የሚፃረር አካሄድ ነው። የኢህአዴግ አባላት ኢህአዴግ ስርዓት አልበኛ አካሄዱን ካስተካከለና ሕገ መንግስቱን ማክበር ከጀመረ እስካሁን የሸቀሉት በሙሉ ተጠራርጎ ተወስዶባቸው መጨረሻቸው ቃሊቲ እንደሚሆን አያጠራጥርም። የእስካሁኑን ቢማሩ እንኳን ከዚህ በኋላ እንደፈለጉ ኃብት የሚመሰርቱበት የፈለጉትን የሚያሳስሩበትና የሚያፈናቅሉበት አሰራር አይኖርም ማለት ነው። ታድያ ይሄ የትኛውን የኢህአዴግ አባል ሊያስደስት ይችላል? በዚህኛው መስመር በኢህአዴግ የወረቀት ላይ መስመር እንጓዝ ካሉ አይደለምና ከሌሎች ድርጅቶች ቀርቶ ከራሳቸው ድርጅት እንኳን የተሟላ ድምፅ ስለማግኘታቸው እጠራጠራለሁኝ።
•°•
4) በቃን ያሉት ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት ከሆነ…
ዌል እንግዲክ… እንዲል ኃይሌ ገ/ስላሴ ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የሚመሰረተው በኢህአዴግ መቃብር ላይ ብቻ ነው። ኢህአዴግም ሆነ አባል ድርጅቶቹ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ አድርገው በምርጫ ስልጣናቸውን ለሕዝባዊ መንግስት ያስረክባሉ ብሎ መጠበቅ ከሰማይ ላይ አሳ እንዲዘንብ የመጠበቅ ያህል ነው። (ኧረ እሱ አንዳንዴ እንኳ ይዘንባል) ጋሽ ለማ የኢህአዴግ መቃብር የሚባለው ቦታ የርሳቸውም መቃብር እንደሚሆን ያጡታል ማለት ዘበት ነው። ኦህዴድ ተወደደም ተጠላም ኢህአዴግ ነውና።
•°•
እንግዲህ የ«በቃን» ምክንያታቸው የቱም ሆነ የቱ… ኢህአዴግ ውስጥ እያሉ አንዱንም ሊያሳኩ እንደማይችሉ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። ኢህአዴግ ውስጥ እያሉ ሪፎርም መመኘት አሊያም ዴሞክራሲን ለሕዝብ ለማምጣት መታገል አሊያም በድምፅ የሚበልጣቸውን ሕወሐት ለማሸነፍ መታገል መጨረሻቸው እንዳያምር ከመሆኑ ውጭ ለነ ጋሽ ለማ ጠብ የሚያደርግላቸው አንዳችም ውጤት የለም።
•°•
እና ምን ተሻለ?
•°•
እደግመዋለሁኝ!
አቶ ለማና ካቢኔያቸው ከላይ ለተጠቀሱ ለማናቸውም ምክንያት ለውጥ ፈላጊ ሆነው ከተገኙ ኢህአዴግን አውግዘው ከመሰናበት ውጭ ምንም አማራጭ የላቸውም። እስካሁን በኢህአዴግ ውስጥ ሆነው የፈፀሟቸው ሐጥያቶች ሁሉ ሊሰረይላቸው የሚችለውና ለትግላቸው ጥሪም ፈጣን የሕዝብ ምላሽ ከሁሉም አቅጣጫ ሊያገኙ የሚችሉት መጀመሪያ ይህን የኢህአዴግ ድርጅት በይፋ ጥለው የመውጣት ወንድነቱ ሲኖራቸው ብቻ ነው። «ኢህአዴግ ኢህአዴግ አትበልብን… ኢህአዴግ የሚባል ነገር የለም። ያለው ሕወሐትና በአምሳሉ ጠፍጥፎ የሰራቸው ድርጅቶች ብቻ ናቸው» የምትሉ ወዳጆቼ የኔም ጥያቄ ኢህአዴግ የሚባል ነገር እንደሌለና ሁሉንም ነገር ሕወሐት ከላይ እስከታች እንደተቆጣጠረችው የሚታወቅ ከሆነ አቶ ለማ በዚህ ውትብትብ ውስጥ ሆነው «የምትፈልጉትን ለውጥ» ማምጣት ስለማይችሉ ከጎኔ ሆናችሁ ኢህአዴግን ለቅቀው እንዲወጡ ትመክሯቸው ዘንድ እጠይቃለሁኝ።
•°•
ከዚያ ውጭ ራሳቸው የመንግስት አንድ አካል ሆነው ሳሉ «መንግስት ወታደር አዘመተብን! መከላከያ ክልሌን ለቅቆ ይውጣ…» ዓይነት ድራማ መጫወት እኛ ብልጣብልጦቹን አያታልለንም። በፕሮፖጋንዳ የናወዘ ቅልጥ ያለ ደጋፊያቸውን ግን ለጊዜው ሊያስፈነድቀው ይችላል…
እነ ለማ በቃን ያሉት… (ዮናስ ሃጎስ)
Filed in: Amharic