>

የኦሮማራ ህብረት ለኢትዮጵያ ጤና ለወያኔዎች ግን የማይድን ካንሰር ነው

 

ሚኒሊክ ዘ ኢትዮጵያ

፟ወያኔ የኦሮማራ ህብረት እጅግ ከሚያስፈሩት ህብረቶች አንዱ ነው። ከዚህ በፊት የመገናኛ ሚኒስትሩ «እሳትና ጭድ በአንድ ላይ መቆማቸው ስራችንን በተገቢው አለመስራታችንን ያመላክታል» ማለታቸውን ልብ ይሏል። ቃል በቃል በደንብ አላባላናቸውም ማለታቸው ነው። ይህ በእንዲህ እያለ በኢትዮጵያ ብዙ ህብረቶች አሉ። የኦሮማራ ህብረት ግን የወያኔን ግብአተ መሬት የሚያፋጥን በመሆኑ ወያኔዎችን እንቅልፍ አሳጥቷል። ለሃያ ሰባት ዓመት አማራውንና ኦሮሞውን በማጋጨት እንቅልፍ ተኝተው ነበር። በነሱ የቤት ስራ ለቀጣዮቹ 50 ዓመታት የሰላም እንቅልፍ እንተኛለን ብለው አስበው ነበር። ይህ ግን አልሆነም። ሁሉም ነገር አከተመ። አሁን ተራው የወያኔ ነው። ማን ተኝቶ ማን ሊቀር ብለው የኢትዮጵያ ልጆች እጅ ለእጅ ተያይዘው ተነስተዋል። «አማራ ኬኛ! ኦሮሞ ኬኛ!» ተባብለው ተማምለዋል።

፟የኦሮማራ ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት እጅግ መሰረታዊ ነው። ለወያኔዎች ግን የማይድን ካንሰር ነው። የኦሮማራ ህብረት ለምስራቅ አፍሪካ ሃገሮችም ሰላምንና መረጋጋትን የመፍጠር አቅም አለው። እነኚህ ህዝቦች በኢኮኖሚም ተዝቆ የማያልቅ ሃብት አላቸው። ይህ ህዝብ በጋብቻም ሆነ በሌላ መልኩ የተዋሃደ ህዝብ ነው። ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች የተዋሃዱ ቢሆኑም ቅሉ የኦሮማራው ግን አብላጫውን የያዘ ነው። የተዋሃደው በራሱ ትልቅ አቅም አለው። ለዛም ይመስላል «አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል» እንደሚባለው፡ የቁርጡ ቀን ሲመጣ ፋኖ እና ቄሮ እጅ ለእጅ ተያይዘው አንድነታቸውን ያሳዩት።ለዛም ነው ወያኔዎች የማይደፈረውን ነካክተው ለህዝባቸው ቋሚ ጠላትን የፈጠሩት። አሁን ግን ወያኔዎች ግራ ተጋብተዋል። ግራ በመጋባታቸው አዲስ ጋብቻ ፈጥረዋል። ከአብዲ አሊጋ። ጋብቻው ይሰምራል?! ወይስ አይሰምርም?! የሚለውን ወደፊት የምናየው ነው።

፟በኢሃዴግ ምክር ቤት ብአዴንና ኦፒዲኦ ያሳዩት ድፍረትም ከኦሮማራ ህብረት የተቀዳ ነው። በ27 ዓመቱ የወያኔ ታሪክ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታም የብአዴንና የኦህዴድ አባላት ለአቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል። ስለወቅቱ የኢትዮያ ሁኔታን የሚያንፀባርቅ ጥያቄ። የፓርላማ አባላቱ ለጥያቄው መልስ እስካልተሰጠን ስብሰባውን አንሳተፍምም ብለዋል። ይህ ትልቅ ለውጥ ነው። የባርነት ሰንሰለቱንም በጥሰዋል። አንጋፋዎቹ የወያኔ የጡት ልጆች ሳይቀሩ ሰንሰለቱን እየበጠሱ ነው። በምክርቤቱ ስብሰባም የትግራይ የበላይነት እንዳለም በድፍረት መናገር ጀምረዋል። ይህንንም ያለው የወያኔ የጡት ልጅ አባዱላ ገመዳ ነው። ይህን ግዜ ነው ወያኔ የምትይዘውን ያጣችው። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ያጠመቀችው የበኩር ልጇ ክዷታል። የሷ ባሪያና ሎሌ ሆኖ መቀጠሉም አንገሽግሾታል። አባዱላ ለ27 ዓመት የተጠፈነገበትን የባርነት ሰንሰለት በጣጥሷል።

፟ይህ በአባዱላ ገመዳ የተነሳው የትግራይ የበላይነት አጀንዳ ወያኔን ክፉኛ አስደንግጧታል። ብርክም አስይዟታል። በሃገሪቱ ውስጥ ስር የሰደደው የትግራይ የበላይነት፡ የኢትዮጵያን ልጆች አሰድዷል። የአውሬ ራት አስደርጓል። በጥይት አስረግፏል። በረሃብ አለንጋ እንዲጠበሱ አድርጓል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያኖች ክብራቸውን እንዲያጡ አድርጓል። ይህ የትግራይ የበላይነት አጀንዳ በሁሉም የኦህዴድ አመራሮችና በመካከለኛውና በታችኛው እርከን ባሉት የብአዴን አመራሮች ሲብላላ ለረጅም ዓመታቶች የቆየ ነገር ነው። የአቶ ገመዳ ልጅ አባዱላ በኢትዮጵያውያኖች ታምቆ የነበረውን ጉድ አፈነዳው!!!

፟የኦሮማራ መናበብ ወያኔን አቅሏን አስቶ የአሊን ጋብቻ ፈልጋዋለች። ከመፈለግም ባሻገር መሳሪያ አስታጥቃዋለች። በአማራና ኦሮሞ ላይ ጦርነት ለመክፈት። ይህ መንገዷ ግን የመጨረሻዋን እስትንፋስ የሚገታ ውሳኔ ነው። እያደረገች ያለው የአልሞት ባይ ተጋዳይነት መፍጨርጨር ነው። የኦሮማራ ሃይል ግን ሁለቱንም ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ የመቅበሪያውን ደውል ደውሏል። የሚቀረው አፈር ማልበስ ብቻ ነው።

Filed in: Amharic