>

ሕወሓት ከሁሉም የሚያሳስበዉ የትግራይ ሕዝብ በአድዋው የቤተሰብ መንግስት ላይ ይነሳብኛል የሚለው ስጋቱ ነው

ኤርሚያስ ቶኩማ

አይናችን የወገኖቻችንን አስከሬን ለመደ ?

ኦህዴድ ሳይቀር ያልጠራናቸው እና ያልጋበዝናቸው ታጣቂዎች እንዴት ወደ ክልሉ እንደመጡ እንደማያውቁ እና አለመጋበዛቸውን መግለፁ የይስሙላውም የኢህአዴግ ማዘዣ ጣብያ ሙሉ በሙሉ መፍረሱን ያሳያል።
ኢትዮጵያ ለህወሓት ስልጣን እና ለአድዋ መንደር እና የቤተሰብ ትስስር ሐብት የማጋበስ ሰይጣናዊ ተግባር ሲባል እንድትበታተን ብቻ ሳይሆን አለ የተባለ የህዝቧ ቁስል እየተፈለገ በህወሓት የተንኮል ስለት እየተከፈተ ለዘመናት አብሮ የኖረ ሕዝብ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም የልጅ ልጆቹ አብረው እንዳይኖሩ  እለት እለት በቢሮ ውስጥ ቁጭ ብለው ተንኮል በሚያደሩ ባለሙያዎች እልቂት እንደተደገሰለት ይታያል።

ስለ ህወሓት አሁን እዚህ አጭር ማስታወሻ ላይ እንደ አዲስ ለመተረክ የማስታወሻዬ አላማ አይደለም።ምክንያት ብዙዎች በሚገባ ተንትነውታል። አሁን የሰሞኑ የህወሓት ድርጊት (ከእዚህ በፊት የነበረ ተግባሩ ቢሆንም)  ገና ከሃያ ሁለት ዓመት ያልዘለሉ ለጋ ወጣቶችን በሀገሪቱ ከአስራ አምስት ዩንቨርስቲዎች በላይ በሚገኙ ካምፓሶች መኝታ ቤት ድረስ ቦንብ እና ክላሽ የታጠቁ የአጋዚ ሰራዊት እያሰማራ፣ የመኝታ ቤታቸውን በር እየሰበረ ከተማሪ ደብተር እና እርሳስ ሌላ በእጃቸው አንዳች የማያውቁ የኢትዮጵያ የነገ ተስፋዎችን በእየሜዳው ላይ አስከሬናቸውን አነጠፈው፣ደማቸው እንደ ውሃ ፈሰሰ።ከወልዲያ እስከ ነቀምት ያሉ ዩንቨርስቲዎች በሽብር ተወጥረው፣ የእናት የአባታቸውን ፊት ሳያዩ ለማደር የሚደነግጡ ታዳጊ ወጣቶችን በቂም እና በዘረኝነት ጥላቻ በተሞላ ስሜት ቁጥራቸው ያልታወቁ ኢትዮጵያውያውን ሕይወት ተቀጥፏል።

በጉዳዩ ዙርያ ወላጆች ስለልጆቻቸው መረጃ እንዳያገኙ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች ወደ ቤተሰብ ቀርቶ ወደ አካባቢው አብያተ ክርስቲያናት እንዳይሄዱ እና እንዳይጠለሉ አስከሬን በወጣበት ግቢ ውስጥ ተማሪዎች በግድ አርፋችሁ ተማሩ  መውጣት አትችሉም ተብለው ዙርያውን በወታደር እያጠረ የቤተሰብ ሰቀቀን ሳምንት ሆነው ሳምንታቱ አልፈዋል። ይህ ብቻ አይደለም። ተማሪዎቹ ለወላጆቻቸው ደውለው ወይንም በማህበራዊ ሚድያ ደህንነታቸውን እንዳይናገሩ ወይንም በግቢው ውስጥ እየተፈፀመ ስላለው ጉዳይ ለተቀረው ዓለም እንዳይገልጡ የኢንተርኔት እና ስልክ አገልግሎት ቆርጦ ወጣቶቹን ሲያሰቃያቸው ነው የከረመው።

የሰሞኑ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች አዲስ  የሚያደርገው አንዱ እና አይነተኛ ምክንያት በመላው ሀገሪቱ ውስጥ ትግራይን ጨምሮ ግጭቶች መፈጠራቸው እና ይህንን ተከትሎም ቀደም ብለው የተጀመሩ ሕዝባዊ አመፆች በአዲስ መልክ መነሳታቸው ነው።ከእዚህ በተለየ የስርዓቱ ታጣቂዎች አድሏዊ ተግባር በሕዝቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ አባል ድርጅት በሚባለው በኦህዴድ ሳይቀር ያልጠራናቸው እና ያልጋበዝናቸው ታጣቂዎች እንዴት ወደ ክልሉ እንደመጡ እንደማያውቁ እና አለመጋበዛቸውን እንዲሁም በመንግስት ደረጃ የጨለንቆ እልቂትን አለማውገዝ ከመተባበር እኩል መሆኑን የገለጡት  የኦሮምያ ፕሬዝዳንት እና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መሆናቸው አድዋ መሩ የህወሓት አካል ከአባል ድርጅቶች ከሚላቸው ጋር የተፋጣበት እርቀትን  ነው። እዚህ ላይ የኦህዴድ  ያልጠራናቸው እና ያልጋበዝናቸው ታጣቂዎች እንዴት ወደ ክልሉ እንደመጡ እንደማያውቁ እና አለመጋበዛቸውን መግለፁ የኢህአዴግ የይስሙላውም ማዘዣ ጣብያ ሙሉ በሙሉ መፍረሱን ያሳያል።

የሰሞኑ የኢትዮጵያ ከራሞት ኢትዮጵያ በቀጥታ በአድዋ የፖለቲካ ስርወ መንግስት እና በቀረው የኢትዮጵያ ክፍል መካከል ቀጥተኛ የጎሳ ግጭት እንዳይፈጠር ያሰጋል።ይህ ግጭት ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ላይ  የሆነ ቦታ በቀን ሰራተኞች መካከል በተነሳ ጠብ ቢጫር በቀጥታ የአድዋ መንግስት ደጋፊዎች በሕዝቡ ላይ የሚያደርሱት እልቂትም ሆነ በበደል የተማረረው እንዲሁም ልጆቹን ለከፍተኛ ትምህርት ልኮ እንደወጡ የቀሩበት በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በቀጥታ ወደ ከፍተኛ የቁጣ መገንፈል እንደሚሸጋገር ምንም ጥርጥር የለውም። ይህንን ሁኔታ ደግሞ እያባባሱ ያሉ የአድዋ መንግስት አድናቂዎች እና የጥቅም ተጋሪዎች  በማኅበራዊ ሚድያ በምስኪኑ ኢትዮጵያዊ ላይ የሚያሳዩት ንቀት እና ስድብ እንዲስተካከል የሚመክር አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን በሕግ የሚጠይቅ የሕግ አካል አለመኖሩ ነው ጉዳዩን የከፋ የሚያደርገው።

ይህ በእንዲህ እያለ ግን ሁለት  አደገኛ ሁኔታዎች በሕዝብ ዘንድ እየታየ ነው። ይሄውም የወገኖቻችን መገደል በእየለቱ በመስማት፣አስከሬን በማየት እና የሚፈሰው ደም በተገቢው ደረጃ የማይሰቀጥጠው ሰው የመኖሩ አደጋ እና ስሜቱ የተነካውም በተገቢ የቁጣ ደረጃ ለመብቱ የመነሳት ፍጥነት በተለይ በአዲስ አበባ እየታየ መሆኑ ነው።ይህ ማለት ከንፈሩን ከመምጠጥ ባለፈ ቁጣውን በተገቢው የማይገልጥ ወይንም እንዳላየ የሚያልፍ ሕዝብ በተለይ በአዲስ አበባ ነዋሪ ዘንድ መታየቱ የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚከፍለው ዋጋ እንዳይንር ያሰጋል።ይህ ወቅት  የአድዋ የቤተሰብ መንግስት ስልጣኑን እንዲለቅ፣ ሕዝብ በጎሳ እንዳይተላለቅ የማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩ የሚሰራበት ጊዜ እንጂ እንዳላዩ የሚያልፉበት ጊዜ አይደለም።ምሁሩ፣ወታደሩ፣ፖሊሱ፣ተማሪው፣ገበሬው እና የከተማ ነዋሪው በአንድነት በኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚነሳበት እና በአድዋ መንደር ስር በመጡ ስብስቦች የሚንቀሳቀሰው የህወሓት ድርጅት በተቻለ መጠን የበለጠ ጥፋት ሳያደርስ የሚንቀሳቀሱበት እንጂ በእየለቱ በማኅበራዊ ሚድያ እና በቴሌቭዥን መስኮቶች ለጋ ወጣቶች አስከሬን እያየን አይናችን ተመልክቶ ከማዘን፣ከመበሳጨት እና ከመቆጨት ባነሰ መልኩ አስከሬን እያየን የመልመድ በሽታ እየተጠናወተን እንደሆነ መመልከት ይቻላል።የወጣቶቹ ሞት የኢትዮጵያ ሞት ብቻ ሳይሆን ነገ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ የተደገሰ የጥፋት ድግስ መሆኑን  ተረድቶ በኅብረት ለሃገር ማዳን ተግባር መነሳት ይገባል።

ህውሓት በመላ ሀገሪቱ ላይ አንድ ዓመት ፈጅቶ የፈፀመው እና ብዙዎች ያለቁበት  አዋጅ ለውጥ ያላመጣለት መሆኑን ከተረዳ በኃላ በእያነሳውም በተግባር ግን አዋጁ ወትሮም ኢትዮጵያ ስትገዝበት የነበረው የበደል አይነት ሁሉ እየተፈፀመ እየተተገበረ ነው።የግፍ አገዛዙን  የስልጣን መጠበቂያ አጥር አድርጎ የሚመለከተው የአድዋ ዘመዳሞች መንግስትሬም ኢትዮጵያን በደም እየነከረ  አዲስ አበባን በቅርቡ በአመፅ የምትፈነዳ ከተማ አድርጎ የአመፅ ቀለበት ውስጥ ገብታለች።አዲስ አበባ ትንሽ ምክንያት የሚሆን ኮሽታ ብቻ የምትጠብቅ ከተማ እንደሆነች ለማንም ግልፅ ሆኗል።ይህንን የተረዱ ዓለም አቀፍ ድርጅት ሰራተኛ ኃላፊዎች በሰበብ አስባቡ ከሀገር እየወጡ የምከርሙበት አንዱ ምክንያት ይሄው በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ እንደሚችል የሚነገረው ሕዝባዊ አመፅ ፍራቻ እንደሆነ ጉዳዩን በእገባ የሚያውቁ የቡና ላይ ወሬ ካደረጉት ሰንብተዋል። ምናልባትም በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የአዲስ አበባ ድምፅ አይሰማም ማለት አይቻልም። እዚህ ላይ አስገራሚው ጉዳይ ህወሓት ችግሩ የአድዋ ስርወ መንግስት የጎሳ ፖለቲካ መሆኑን የረሳ እየመሰለ ችግሩ ከአቶ ሃይለማርያም ለማስመሰል አቶ ኃይለማርያምን በመቀየር መፍትሄ ያመጣ ለመምሰል ሽር ጉድ እያለ ነው። ቀድሞም የህዝቡን ድምፅ የመጨፍለቅ ሥራ የሚሰራው  እና ትዕዛዙ ለይስሙላ በአቶ ሃይለማርያም ይምሰል እንጂ ዋና ማዘዣ ጣቢያው የሚመጣው ከህወሓት ቢሮ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው።ትልቁ ቁም ነገር ይህ ሁሉ እልቂት እየተፈፀመ ያለው የህወሓት መንግስት ስልጣን ለሕዝብ አላስረክብም በቀደድኩላችሁ ቦይ ብቻ ፍሰሱ  የሚል የእብሪት ተግባር ምክንያት መሆኑን ሁል ጊዜ መዘንጋት የሌለበት ነው።ህወሓት ኢትዮጵያ ትጥፋ እንጂ ስልጣን አልለቅም ሂደቱ ሁላችንን ኢትዮጵያውያንን መጪውን በመፍራት አርፈን የምንገዛ አድርጎ የማሰብ የአስተሳሰብ ድህነት ብቻ ሳያሆን  የኢትዮጵያን ሕዝብን ስነ ልቦና ደረጃ ያለመረዳት ችግር ነው።

ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ከመጥፎ መጥፎ ይመረጣል።ሁሉም መጥፎ አካሄድ ቢሆንብህ የተሻለውን መጥፎ መምረጥ ብቻ አማራጭ የሚሆንበት አጋጣሚ በሀገሮች ታሪክ የሚያጋጥም እውነታ ነው።ሳይንገጫገጩ ያሰቡበት መድረስ የለም። ህወሓት በስልጣን ላይ እያለ ከሚመጣው የመከፋፈል አደጋ ይልቅ የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ሕዝብ ነፃነቱን ማወጅ እንደሚመርጥ እና አሁን እየሆነ ያለው ሁሉ ሕዝብ  ለበለጠው ትግል ከመነሳት ሌላ አማራጭ እንደሌለው  እንጂ አንዳች ወደ ኃላ እንደማይገፋው ማወቅ ተገቢ  ነው።ችግሩ እየገፋ ስመጣ እና ጉዳይ የትግራይ መሬትን እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ፍል መቆርቆር ሲጀምር የአድዋው ስርወ መንግስት በእራሱ በትግራይ ሕዝብም ጭምር አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም።ለእዚህ ነው ህወሓት አሁንም ለእውነተኛ ለውጡ ካልተነሳች መውጊያው ለእራሷ ይብስባታል የምለው። ፈተናው ሲበዛ መውጫው ይጠባል።ህወሓት ከሁሉም ስጋት ውስጥ የገባው የትግራይ ሕዝብ በአድዋው የቤተሰብ መንግስት ላይ ይነሳብኛል በሚለው ስጋት ነው።
ይህንንም  ስለሚያውቅ ነው የትግራይ ተወላጆችን ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ግጭት ውስጥ ለማስገባት አንዴ በስፖርት ሌላ ጊዜ በዩንቨርስቲ ተማሪዎች መሃከል በሚነሱ ጠቦች ሕዝቡን ለማስደንበር የምሞክረው።ለምሳሌ የወልዲያው የስፖርት ጫወታ ግጭት ላይ ህወሓት ቢያንስ በደህንነቱ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ቀድሞ ያውቃል።የአቶ ጌታቸው ቢሮ ግን ጫወታው እንዲሰረዝ አላደረገም። ይልቁንም ለግጭቱ ምክንያት እንዲሆን በከተማው ውስጥ ከትግራይ የመጡ ወጣቶች በፒክ አፕ መኪና እየተዘዋወሩ አላስፈላጊ ቃላት እንዲሰነዝሩ አደረገ።አንድ የስፖርት ጫወታ አይደለም ውጥረት መኖሩ እየታወቀ ቀርቶ ኃይለኛ ዝናብ በመኖሩም ይሰረዛል። ለህወሓት ግን የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተከላካይ መሆኑን ለመንገር ይህንን ግጭት እያወቀ ሕዝብ እንዲገባ አደረገ።በምላሹ በአዲግራት ዩንቨርስቲ እና ሌሎች ቦታዎች በፈለገው መንገድ ተቀጣጠለለት። ይህ አካሄድ ለህወሓት መውግያውን ያስለዋል እንጂ መፍትሄ አይሆንም። የመጨረሻው ብሔራዊ ተቃውሞ በመላ ሀገሪቱ አዲስ አበባን ጨምሮ የተነሳ ጊዜ ህወሓት የቀረ እንጥፍጣፊ ሃሳብ ለማስረዳት ፋታ አገኛለሁ ብሎ ካሰበ ፍፁም  ሕልም እንደሚሆን ከአሁኑ ብረዳው ጥሩ ነው።

Filed in: Amharic