>

''አምስቱ ምርጦቼ" (አበበ ገላው)

በእኔ እይታ ለነጻነት በሚደረገው ትግል ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ከፍተኛ አወንታዊ ትጽእኖ ፈጣሪዎች፣ ህዝብን በህብረት ያሰለፉ፣ ያነቁ እና የመሩ እንዲሁም ፋሽታዊው የህወሃቶች ስርአት በቀውስ እንዲወጠርና እንዲሰነጣጥቅ አስተዋኦ ያበርከቱ ሁሉ ሲሆኑ ከነርሱም መሃል የሚከተሉት ጎልተው ይታዩኛል።
1. የኢትዮጵያ ህዝብ ጩኸትና ሰቆቃን ለመላው አለም በማሳወቅ እና ፋሺስቶችን በማጋለጥ ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረከተው የኦሎምፒኩ ጀግና የአገር መኩሪያ ፈይሳ ሌሊሳ የ2016 እንቁ ነበር። ፈይሳን ባገኘሁት አጋጣሚ ህዝቡን አንድ አርጉት በጋራ አታግሉት በማለት ያቀረበልኝ ማሳሰቢያ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለለውጥ የምንታገልና የምናታግል ሁሉ ከልባችን ልንተጋበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
2. በኦሮሚያ ከዳር እስከ ዳር የተቀጣጠለውን ህዝባዊ ንቅናቄ በመምራትና በማደራጀት ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረከቱትና መስዋእትነት የከፈሉት የቄሮ ወጣቶች ናቸው። ምንም እንኳን በአቋም እና እስትራቴጂ ባንስማማም ያለጋራ ትግል አንባገነናዊ ስርአት መናድ ፈታኝ መሆኑን በመገንዘብ ወደፊት ቄሮዎች እንደገና አንሰራርተው ትግላቸውን ከሌላው ጭቁን ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጋር እንደሚያቀናጁ ተስፋ አለኝ።
3. የመከፋፈል ድባብ ትግሉ ላይ አደጋ በደቀነበት ወሳኝ ሰአት ላይ የፈሰሰው የኦሮሞ ወገናችን ደም ደማችን ነው ብለው የአንድነትን ሃይል አጉልተው የመከፋፈልን ግንብ ለደረመሱት የአማራ ታጋዮች፣ በተለይ የጎንደርና የባህር ዳር ወጣቶች፣ ክብር ይገባቸውል።
4. ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ካልሁነብኝ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በማንቃት እና መረጃን በማስታጠቅ፣ የተደበቀውን ሁሉ ጎልጉሎ በማውጣት ስርአቱን እርቃኑን በማስቀረት ህዝቡን ለትግል በማነሳሳት እና ለሚሊዮኖች አይንና ጆሮ የሆነውን ኢሳትን እንዲሁም ለዚህም ሌት ተቀን በትጋት በመስራት ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስተዋጾ ላበረከቱት የስራ ባልደረቦቼና በመላው አለም የሚገኙ የኢሳት ደጋፊዎች እና ቤተሰቦች የሚያስመስግን ስራ መስራታቸውን ስመሰክር በኩራት ነው። ይሁንና እስካሁን በሰራነው ሳንኩራራ በሚቀጥለው አመት የተሻለ ለመስራት በጋራ የበለጠ እንደምንተጋ አልጠራጠርም።
5. ትግል ያለመሪ ወደ ስኬት አያመራምና ከእኔ በላይ የህዝቤ ነጻት ብሎ ክብሩን፣ ኑሮውን ትዳሩን እና ቤተሰቡን በትኖ ሙሉ ግዜውን ትግሉን ለመምራት እሾሃማውን መንገድ መርጦ መሬት የወረደው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአሳለፍነው አመትም ተጽእኖው እጅግ የጎላ ነበር። መሪ ፈተና እና መስዋእትነትን አይፈራም። መሪ መንግዱን ያውቃል፣ መንገድ ይመራል፣ ራዕይውን ለማሳካት እራሱን ዝቅ ያደርጋል። ለእኔ ከሶስት ጊዜ በላይ ወያኔ የሞት ፍርድ ያሳለፈበት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ምርጥ መሪ ነው። በአሁኑ ጊዜ ያጋጠው ችግር የመሪ ሳይሆን የተከታይ እና የታጋይ ጥራት በመሆኑ ይሄንን ችግር ለማስተካከል በየአቅጣጫው ጥረት ሊደረግ ይገባል። ወደድንም ጠላንም ትግል ያለ መሪ ሾፌር የሌለው መኪና ማለት ነው።
“A leader is one who knows the way, goes the way, and shows the way,” as John Maxwell said.
ለማንኛውም 2018ን ቸሩ ፈጣሪያችን ነጻነታችንን የምናውጅበት አመት እንዲያደርግልን ምኞቴን እገልጻለሁ።
አሁንም በድጋሚ “ነጻነት፣ ነጻነት፣ ነጻነት…” እላለሁ።  ..>>

Filed in: Amharic