>
1:34 pm - Saturday October 23, 2021

ዘመነ ተሐድሶ ወይስ ዘመነ ጽልመት (ከይኄይስ እውነቱ)

ዘመነ ተሐድሶ ወይም ዳግም ልደት (Renaissance) የሚባለው ጊዜ ጠቅለል ባለ አገላለጽ በአውሮጳ ክፍለ ዓለም ለፈጠራ፣ ለአዳዲስ ግኝቶች፣ ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለፍልስምና፣ ለታሪክ፣ ለሥነ ጽሑፍ፣ ለሥነ ጥበብ፣ ለኪነ ጥበብ ባጠቃላይ ለጥበብ/ለእውቀትና ብልጽግና የተደረገ የሃሳብ ልዕልና፣ የመንፈስ መነቃቃትን የሚያመለክት በአውሮጳ ታሪክ ውስጥ መካከለኛው ክፍል ዘመን ተብሎ የሚታወቀው ጊዜ (እ.አ.አ. ከ14ኛው እስከ 16ኛው ክ/ዘመን) እንደተጠናቀቀ ተከትሎ የመጣውን ጊዜና ቀጣይነት ያለውን የሥልጣኔ ሂደት የሚያመለክት ክስተት ነው፡፡
የዚህ አስተያየት ዓላማ ስለ አውሮጳው ዘመነ ተሐድሶ ለማውሳት አይደለም፡፡

ይልቁንም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አስጨንቆና አስጠብቦ ሕዝባችንን ከሰውነት ጎዳና፣ አገራችንን ከአገር ተርታ አስወጥቶና አዋርዶ፤ ይህም አልበቃ ብሎት አጥፍቶ ለመጥፋት የሚንደፋደፈው ሽብርተኛው የወያኔ አገዛዝ ለቅጥፈቱና በዚህም ዕድሜውን ለማርዘም የሚጠቀምበት ቃል ሕዳሴ (ተሐድሶ) በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም አስተያየቱ ተሐድሶ በጨረፍታ እንኳ የነካው የአገራችን ሕይወት አለ ወይ የሚለውን የአደባባይ ምሥጢር ከየሕይወት ዘርፉ ለአብነት ያህል ለማንሳት ይሞክራል፡፡

እኩይ ተግባርን በመልካም ስም ማደስ አይቻልም፡፡ ወያኔ በአገሩ ሁሉ ሕዳሴ ሕዳሴ ይላል፡፡ እበላ ባይ ኹሉ ሣር ቅጠሉን በሕዳሴ ሰይሟል፡፡ መኩሪያችን የሆነው የአባይ ወንዝ (የቃሉ ትርጉም ታላቅ ማለት ነው) ላይ በጅምር የቀረውን ግድብ እንኳን በስሙ አባይ ብሎ ላለመጥራት ሕዳሴ በማለት የባዕድ አስመስለውታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድንቁርና ነው የወያኔ ተሐድሶ፡፡

1/ የመንግሥት አስተዳደር

ኢትዮጵያ በታሪኳ ከአገዛዝ በቀር ሕግን መሠረት ያደረገ አስተዳዳርና መሪ ገጥሟት ባያውቅም፣ ከሠለጠነ የፖለቲካ ባህል ጋር ሆድና ጀርባ ብትሆንም፤ መንግሥት እኔ ነኝ፣ አገር እኔ ነኝ፣ ሕዝብ እኔ ነኝ፣ ሕግ እኔ ነኝ የሚሉ ፈላጭ ቆራጮች እና አምባገነኖች ቢፈራረቁባትም፤ እገዛዋለኹ የሚለውን አገርና ሕዝብ (በአፍ፣ በመጣፍና በተግባር) በጠላትነት ፈርጆ በጥላቻ ላይ መሠረቱን ያቆመ አገዛዝ ግን ገጥሟት አያውቅም፡፡ ከወያኔ በቀር፡፡ ርእዮተ ዓለሙ፣ፖሊሲው፣ ሕጉ፣ ስልቱ፣ ዘዴው፣ ወዘተ. ሸፍጥና ተንኮል ሲሆን፣ ግቡም ዝርፊያን ማደላደልና ሥልጣን ላይ መቆየት ነው፡፡ ለዚህም ሲባል የአገርና የሕዝብ ያልሆነ፣ ሕዝብ የማያከብረው፣ የኔ ነው የማይለው፣ ለመብቴ ÷ ለነፃነቴ÷ ለደኅንነቴ ዋስትና ነው ብሎ የማይመካበት፣ ይልቁንም በጭካኔው እና በማስፈራሪያነት የሚታወቅ፣ ታማኝነቱና ታዛዥነቱ ለአገዛዙ ብቻ የሆነ የወያኔ የግል ‹ደኅንነትና ሠራዊት› አቁሟል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የወያኔ ለውጥ፣ መሻሻል ወይም ሕዳሴ፡፡
ኢትዮጵያ እንኳን ለራሷ የውጭውን ዓለም እያከበሩ ያሉ ልጆች እያሏት ታላቂቷ አገር በአእምሮ ድንክዬዎች መገዛቷ በየትኛውም መለኪያ ዘመነ ወያኔን የድንቁርና እንጂ የተሐድሶ ሊያደርገው አይችልም፡፡

2/ ምጣኔ ሀብት

እልፍ አእላፋት ኢትዮጵያውያን በቋሚነት ለረሃብና ለችጋር በተጋለጡባት፣ ጥቂቶች በቁንጣን ሚጨነቁባት÷ብዙኃኑ በጠኔ በሚያልቅባት የወያኔ ኢትዮጵያ ያለው የብሔራዊ ሀብት ክፍፍል በሁለት የማይገናኙ ጽንፎች የተወጠረ ነው፡፡በዝርፊያ ኢትዮጵያን ያራቆቱ ወያኔና ሎሌዎቹ ባንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እያለ ጭቆናን ተሸክሞ የዘለቀውና አሁን በቃኝ ያለው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፡፡ ንቅዘት ዋነኛ መገለጫው የሆነው የወያኔ ኢኮኖሚ በድቡሽት ላይ የተዋቀረ መሆኑን የሐሰት ስታቲስቲክስ ሊሠውረው አልቻለም፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አሳዳሪዎቻቸው ነጮች ፊታቸውን ማዞር ሲጀምሩ አገራዊው ግምጃ ቤት ኦና እየሆነ ነው፡፡ አሁን የቀራቸው እንደ አንዳንድ መሰሎቻቸው የአፍሪቃ ደም መጣጮች ካሸሹት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ላበድራችሁ ይሉን ይሆን? ለከት የሌለው ስግብግብነታቸው ይኽንንም የሚፈቅድላቸው አይመስለኝም፡፡ ወዲህም ቀናቸው እየተቆጠረ በመሆኑ ለክፉ ቀን ካስቀመጡት ጥሪት አይነኩም፡፡
ሌላው የወያኔ አገዛዝ ዕድገት መለኪያ ነዋሪውን አግለው በወረራ መልክ በተቆጣጠሩት፣ እንደ እንግዳ ደራሽ በመጡና በጥላቻ ፈረስ በሚጋልቡ ጸጉረ ልውጦች አማካይነት ቀበሌ በሚባል ፀረ-ሕዝብ ተቋም አገሬውን በሙሉ ከቤት ንብረቱ ማፈናቀል፣ ይኸው ተፈናቃይ እና መጪው ትውልድ በሚከፍለው ብድር (ተቋራጭ ተብዬዎች ጋር የሚፈጸመው ዝርፊያ እንደተጠበቀ ሆኖ) ወደሚሠራው መንገድ ክቡሩን የሰው ልጅ እየወረወሩ አገር አልባ ማድረጉን ነው፡፡ ሕንፃ እግዚአብሔርን (ሰውን) ዕለት ዕለት እያፈረሱ በዝርፊያ ጥቅመ ሰናዖርን (የባቢሎን ግንብ) መገንባት እውቀትም ዕድገትም አይደለም፡፡ ድንቁርና እንጂ፡፡ ድንቄም ሕዳሴ፡፡

3/ ትምህርት

የወያኔ አገዛዝ ዓይነተኛ መለያው ከጥበብ/እውቀት በአጠቃላይ ከትምህርት ጋር ዓይንና አፈር መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ወያኔ ተሐድሶ ከሚባለው የሃሳብ ልዕልና፣ ምጥቀትና ርቀት ባይተዋር መሆኑን አስመስክሯል፡፡
ወያኔ ትውልድና አገርን እየገደለበት እና አገራዊ ድንቁርና እንዲሠለጥን እያደረገበት ያለው ትልቁ መሣሪያ በተግባር የሚታየው የተበላሸ የትምህርት ሥርዓት ነው፡፡ ትምህርት፣ ብርሃን እውቀትን ገልጾ ነፃ የሚያወጣ መሆኑ ቀርቶ፤ በጨለማ ድንቁርና ጋርዶ ባርነት የሚያሰፍን መሆኑ የዘመኑ ታላቅ እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ ድንቁርና ሞልቶ ሲፈስ እንዲህ ለአገር ኹሉ ይተርፋል፡፡ አንዳንድ የዋሀን እና የወያኔ ሎሌዎች ለታሪክ ሽሚያና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ያለጥናትና ዕቅድ የተቋቋሙትን ሠላሳ ‹‹ዩኒቨርስቲዎች›› ወያኔ በትምህርቱ ዘርፍ ያስመዘገበው ‹ዕድገት› አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ሌላው ድንቁርና፡፡ እውነታው ሠላሳውም ተጨምቀው አንድ ደረጃውን የጠበቀ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት (በተለይ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበሩትን) አይወጣቸውም፡፡ የእውቀት አድባራት (ዩኒቨርስቲዎች) የሎሌ ‹ምሁራን›፣የካድሬዎችና ደጓዕሌዎች መፈንጫ መሆኑ የወረድንበትን አዘቅት አመልካች ነው፡፡ ‹ግሩም የሕዳሴ ትሩፋት›፡፡
አገር የሚያድገው የሕዝብ ሕይወት የሚሻሻለው በጎ ሰዎች በሚያፈልቁት ለፈጠራ፣ ለሥራ፣ ለለውጥ በሚያነሳሳ አሳብ አማካይነት ነው፡፡ የአእምሮ ውጤት የሆነው አሳብ በትምህርት በልምድ ይበለጽጋል፡፡ ማሰብ ከምንም በላይ ነፃነትን ይፈልጋል፡፡ ወያኔ በማስመሰያ ሕገመንግሥቱ (façade constitution) ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቀ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ፣ ሃሳቡን የመግለጽ ነፃነት እንዳለው ካስቀመጠ በኋላ ይህንን ነፃነት ለመጠቀም የተንቀሳቀሱ ዜጎችን በሙሉ ሰብስቦ በወህኒ ቤት አጉሯቸዋል፡፡ ጋሼ መስፍን በቅርቡ ባሳተሙትና ማንነታችንን ዕርቃኑን አውጥቶ ባሳየው መጽሐፋቸው (እንዘጭ እምቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ) በወያኔ አገዛዝ ማሰብ የግል ተግባር መሆኑ ቀርቶ ከአገዛዙ እንደ ወራጅ ውኃ ከላይ ወደታች የሚፈስ፣ አንድ ወይም ጥቂቶች ያሰቡለትን ሌላው ተቀብሎ ሳይጠይቅ የሚፈጸምበት ሂደት መሆኑን ፍንትው አድርገው አሳይተውናል፡፡ በዚህም የሰብአዊ ፍጡር ዋነኛ መለያ የሆነውን የማሰብ ችሎታ በማምከን፣ ኢትዮጵያን በአሳብ ድርቅ ክፉኛ የተመታች አገር አድርጓታል፡፡ እንደ ወያኔ ለመንጋው ላስብላችኹ የሚሉ የጎሣ ድርጅቶችም የድንቁርናው ተካፋዮች መሆናቸውን መካድ አይቻልም፡፡ በመሆኑም ወያኔ የሃሳብ ልዕልና መገለጫው ከሆነው ተሐድሶ ጋር እስከ ወዲያኛው ላይገናኝ ተለያይቷል፡፡

4/ የጎሠኝነት ጣዖት

በአርዓያ ሥላሴ የመፈጠር ሰውነት፣ የአገር ባለቤት የሚያደርግ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ጠፍቶ፣ ለማይታይ÷ለማይጨበጥ÷ ለማይዳሰስ (ጎሣ ለተባለ) ‹ጣዖት› እውቅና ሰጥቶ አገርን ማመስ ሕዝብን (በፈጠራ ልዩነት) ማተራመስ ነው የወያኔ ሕዳሴ፡፡ ሕዝብን እንደ ከብት ‹ክልል በሚባል ጋጣ አጉሮ ለዘመናት በውልደትና በጋብቻ፣ በንግድና በፍልሰት፣ በሃይማኖትና በባህል፣ በፍቅርና በጠብ ወ.ዘ.ተ. የተመሠረተ አብሮነትን በማጥፋት የዘረኝነትን ሥርዓት ማንገሥ ከድንቁርና በስተቀር እንዴት የሃሳብ ልዕልና ይሆናል፡፡ ዛሬ ራሳችንን ችለን መቆመ ያቃተንና ለጎሣ ጣዖት የምንሰግድ ኹሉ ወደድንም ጠላንም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነን፡፡ ራሳችንን ሳናድስ ለሌሎች ብርሃን ለመሆን መነሳት እብለት ነው፡፡ ድንቄም ሕዳሴ፡፡

5/ ስደት እስከነ ጓዝ መዘዙ (ውርደት፣ባርነትና ሞት)

ሀገረ መንግሥትን በመመሥረት ከቀደምቶቹ መካከል የነበረ÷ በሕግ አምላክ በሚለው ፍልስምናው ልማዳዊ የሕግ የበላይነትን ያወቀ÷ የራሱ የጽሑፍ ቋንቋ ያለው÷ ለስደት ለባርነት ሳይሆን ጥበብ/እውቀትን ለመሻት ጠቢብን ፍለጋ የተጓዘ÷ 3ቱ ታላላቅ ሃይማኖቶችን በቀደምትነት ተቀብሎ በአብሮነት በመኖር ለሥልጣኔ ተምሳሌት የሆነ÷ እንደዛሬው ውርደት ገንዘቡ ሆኖ በየቆሻሻውና በየጥሻው ላስቲክ ወጥሮ የመንገድ አዳሪ ከመሆኑ በፊት ድንቅ ኪነ ሕንፃዎችን በመሥራት የተጠበበ÷ አውሮጳውያንን አሳፍሮ ለጥቁር ሕዝቦች ኹሉ የነፃነት ቀንዲል የሆነ ሕዝብና አገር ወዘተ.ባለንበት 21ኛው ክ/ዘመን የተነሳው ሀገር-በቀል ወንበዴ ዜጎቹ ላይ ባፀናው አፈናና ቀንበር ምክንያት በገፍ መሰደዱ ሳያንስ፣ በተለይም በተሰደዱበት አረብ አገራት የሚደርስባቸው ግፍና በደል ሳያንስ፣ በስደቱ ሂደት በባሕር ሰጥሞ መቅረቱና በአሸባሪዎች ሰይፍም መቀላቱ ሳያንስ፣አሁን ደግሞ ዜጎቹ እንደ ሸቀጥ ለባርነት ሲሸጡ አንዳች ኃላፊነት የማይሰማው አገዛዝ በዜግነትም በሰብአዊነትም መለኪያዎች የዘቀጠ ብቻ ሳይሆን ስለ ተሐድሶ ለመተፈንስ ምንም የሞራል ብቃት የለውም፡፡
ለማጠቃለል መዳኛ በሌለው የዝርፊያና የሥልጣን ሱስ ተጠምዶ፣ ነባር ድንቁርናን በአዳዲስ ድንቁርና እያደሰ ኢትዮጵያን ለጨለማ ዘመን የዳረገ የጥቂት መንደርተኞች አገዛዝ በዚያው በሠለጠነበት የድንቁርና መሥፈርት ካልሆነ በቀር መለወጥ፣ መሻሻልና መታደስ ፀሩ የሆነ የወንበዴዎች ጥርቅም ሕዳሴ እያለ ሲያደነቁረን መክረሙ የንቀቱን ጥግ የሚያሳይ ነው፡፡ መራሩ እውነት ደግሞ ይህ ድንቁርና የነገሠው በአገዛዙና በሎሌዎቹ ብቻ ሳይሆን፤ አንዳንድ ፊደል ቆጥሬአለኹ በሚለው እና የከፋው ደግሞ አንዳንድ ‹‹ምሁራን›› ነን በሚሉ ወገኖች (በሎሌነት ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንዶች በሚያስደነግጥ ዝምታቸው፣ ሌሎች በፍርሃትና በአድርባይነት፣የተቀሩት ደግሞ ጥበብ/እውቀት የምትጠይቀውን እውነት ባለመያዝ ወ.ዘ.ተ.) ጭምር መሆኑ ነው፡፡
እስከ መቼ በአእምሮ ሕፃን ሆነን (ቅርብ አዳሪ በመሆንና ውጤቱንም እያወቅን) የአውሮጳንና የአሜሪካን ሞግዚትነት እንሻለን፡፡ መቼ ይሆን በሆደ ሰፊነት እርስ በርሳችን ተነጋግረን፣ ተወያይተን፣ ተደማምጠን፣ የሃሳብ ልዩነቶቻችን ተቀብለን፣ በጋራ የተስማማንባቸውን ጉዳዮች ይዘን፣ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ የሚበጅ እኩልነትና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት÷ መንግሥተ ሕዝብ ለመትከል የምንነሳው፡፡ ነፃነትን የሚናፍቀው ኢትዮጵያዊ ባጠቃላይ፣ በውስጥም በውጭም የምትገኙ ምሁራን በተለይ ይህ ወቅት አሁንም ጋሼ መሥፍን እንዳሉት መንቀልን ብቻ ሳይሆን መትከልን አጥብቀን የምናስብበትና ወደ ተግባር የምንለውጥበት ነው፡፡
የሕዝብ አጀንዳ ባልሆነ የወያኔ መግለጫ ጋጋታ ሳንዘናጋና ሳንወናበድ ማኔ ቴቄል ፋሬስ የታወጀበትን የወያኔ አገዛዝ ከምድረ ኢትዮጵያ በማስወገድ ቅድሚያ ነፃነታችንን ቀጥሎም በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ የተመሠረተ መንግሥተ ሕዝብ ለመመሥረት የአመለካከት ልዩነታችን እንቅፋት ሳይሆንብን ተግተን በኅብረት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

የኢትዮጵያ አምላክ ከዚህ ዘመነ ጽልመት አውጥቶ ወደ ዘመነ ትንሣኤ ዘመነ ተሐድሶ በሰላም ለመድረስ ያብቃን፡፡

Filed in: Amharic