>

አዲስ አበባ ላይ የምናደርገው ፍልሚያ የፍፃሚው ፍልሚያ መሆን አለበት! (ዶ/ር ታደሰ ብሩ)

በአዲስ አበባ ጉዳይ ባዘጋጀሁት ፕሮግራም ላይ አንዳንድ ወገኖቼ ቅር ተሰኝተዋል። በዚህም ምክንያት ይህችን አጭር ማብራሪያ እሰጣለሁ።

ሰለ አዲስ አበባ ፕሮግራም ያዘጋጀሁት ሁለት ዓላማዎችን ይዤ ነው፡ (1) የአዲስ አበባን ልዩ cosmopolitan ባህርይ ለመረዳት። እና (2) አዲስ አበባን ለሕዝባዊ እምቢተኝነት ማዘጋጀት። የህወሓት ካድሬዎች የአዲስ አበባን ማኅበረሰብ ስለበታተነው አመጽ እንዳይነሳ አድርገናል ብለው በግልጽ ይናገራሉ። እኔ ይህ እውነት አለመሆኑ ማሳያ ጊዜ ደርሷል ብዬ አምናለሁ። ለዚህ እንዲረዳ ተከታታይ ፕሮግራሞችን አዘጋጅቻለሁ።

ስጀምር ሁለት ጉዳዮችን እንድናልፋቸው ፈልጌዓለሁ – የስያሜ ጉዳይና የባለቤትነት ጉዳይ። ሁለቱም የወያኔ ሀመንግሥት የፈጠራቸው ችግሮች ናቸው። አሁን እነሱ ላይ ጊዜ ማጥፋት የለብንም፤ እነዚህ ላይ ከገባን ዋናውን ጉዳይ እንዳናይ ያደርጉናል በሚል የችግሮቹ መኖርን ብቻ እውቅና ሰጥቼ ልዘላቸው ነበር የወሰንኩት።

በአዲስ አበባ ከተማ ስያሜ ጉዳይ መከራከር ለሕዝባዊ እምቢተኝነት አይጠቅመንም። የስያሜ ችግር ያለባቸው ከተሞች ብዙ ናቸው። ደብረዘይት/ቢሾፍቱ፣ ናዝሬትአዳማ፣ ግዮን/ወሊሶ፣ አዋሳ/ሀዋሳ፣ ጅጅጋ/ጅግጅጋ …. እዚህ ክርክር ውስጥ ገብተን ጊዜና ጉልበት ማባከን የለብንም።

የአዲስ አበባ ማኅበረሰብን የዘውግ ጥንቅርን በሚመለከት አወዛጊ ቢሆንም የስታትስቲክስ ጽ/ቤት መረጃን ነው ያነሳሁት “በስታትስቲክስ ጽ/ቤት መሠረት ከነዋሪዎቿ 56.04% አማራ፣ 19.00% ኦሮሞ፣ 16.34% ጉራጌ፣ 5.18% ትግሬ፣ 2.94% ስልጤ፣ 1.68% ጋሞ በማለት ራሳቸውን ይገልፃሉ” የሚለውን ነበር ለማንበብ የፈለግሁት። ይህ የሚለው የስታትስቲክስ ጽ/ቤት እንጂ እኔ አይደለሁም፤ ተቀባይነት ያለው መረጃ ነውምም አላልኩም። “56.04% አማራ ናቸው“ ብዬ እንደተፃፈው በማንበብ ፋንታ ”56.04% ከአማራ የመጡ ናቸው ይባላል” ማለቴ በአገላለጽ የተፈጠረ ስህተት እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እጠይቃለሁ። እኔ እንዲህ ዓይነት እምነትም የለኝም፤ ኖሮኝም አያውቅም። በገለፃዎች ወቅት እንዲህ ዓይነት ስህተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ በእንዲህ ዓይነት ወቅት አድማጮች በገለፃው ውስጥ ያለ አንድ ቃል ወይም ዓረፍተ ነገር ሳይሆን ሙሉ መልዕክት እንዲያጤኑልኝ በአክሮብት እጠይቃለሁ። “ራስን “ኢትዮጵያዊ” ብቻ ብሎ የመግለጽ እድል ቢኖር ኖሮ በርካታ የአዲስ አበባ ሕዝብ ራሱን እንደዚያ በገለፀ ነበር” በሚለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ ነው የኔ እምነት ያለው።

በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ጠንክረን መሥራት አለብን። አዲስ አበባ ላይ የምናደርገው ፍልሚያ የፍፃሚው ፍልሚያ መሆን አለበት። ትኩረታችን ሕዝባዊ እምቢተኝነት አዲስ አበባ ውስጥ እንዴት ይነሳ የሚለው ላይ ይሁን። ከዚህ ዋነኛ ሃሳብ የሚያናጥቡንን ነገሮች ወደ ጎን እንበላቸው። የህወሓት ህገመንግሥት ብዙ ችግሮችን ፈጥሮልናል። መቅደም ያለበት ህወሓትን ማስወገድና የተሰበሩና የተጣመሙ ነገሮች ማቃናት ነው።

Filed in: Amharic