>
7:37 pm - Wednesday February 8, 2023

“ የመርህ አልባው ግንኙነት ሰምና ወርቅ ? ” (አዜብ ጌታቸው)

የኦቦ ለማ መገርሳን ጋዜጣዊ መግለጫ ከማድመጤ በፊት “መርህ አልባ ግንኙነት” በሚል በኢህአዴግ መግለጫ
የተጠቀሰው ድክመት፡ በአማራና በኦሮሞው ህዝብ መካከል እየጎለበተ የመጣውን የመቀራረብ፤ የመተሳሰብና
የአንድነት ስሜት ለማጠልሸት የተቋጠረ ነው መስሎኝ ነበር ።
የለማ መገርሳን ጋዜጣዊ መግለጫ ሳደምጥ ግን “መርህ አልባ ግንኙነት” የተባለው የህወሃት ባለስልጣናት ከራሳቸው ድርጅት ውጭ በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ኔት-ወርክ በመዘርጋት የሚያደርጉትን ዘረፋና ምዝበራን አላማ ያደረገ ቡድናዊ እንቅስቃሴ መሆኑን ተረድቻለሁ። ለግዜው ግልጽ ትርጉሙ (ሰሙ) ይሄው ነው። ወርቁስ? …. አብረን እንጠርጥር።
ከጥቂት ወራት በፊት አቶ ለማ በኦሮሚያ የሚገኘውን የንግድ ማህበረሰብ ሰብስበው ሲያነጋግሩ ፤ “ካሁን በኋላ በኔ ስልጣን የምወስነው እኔና እኔ ብቻ ነኝ፡፤ “በጎድ ፋዘሮች” በግልባጭ የሚደርሰኝን ደብዳቤ ቀድጄ ቅርጫት ውስጥ ነው የምከተው። …” በማለት የህወሃት ባለስልጣናት በሌሎች ክልሎች ውስጥ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በግልጽ መቃወማቸውን ለሚያስታውስ ፦ አቶ ለማ “መርህ አልባ ግንኙነት” ሲሉ ይህንኑ የህወሃት ጣልቃ ገብነት መሆኑ አይጠፋውም። ዛሬም ከህወሃቱ ሊቀመንበር ከደብረ ጺዎን ጎን ቁጭ ብለው ደገሙት።
ስለዚህ የህወሃትን ትርጉም ባናውቅም፤ በኦቦ ለማ ትንታኔ መርህ አልባ ግንኙነት ማለት፦ የህወሃት ባለስልጣናት
በየክልሉ የሚያደርጉትን ዘረፋ፤ በሌሎች ክልል ባለስልጣናት ላይ የሚፈጽሙትን ሹም ሽር፤ ጠቅልሎ የያዘና ድምር ውጤቱም የህወሃት ፍጹም የበላይነት ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ኢህአዴግ በመግለጫው የህወሃትን የበላይነት በተዘዋዋሪ አምኖ መቀበሉን በጭላንጭልም ቢሆን ያሳየ ይመስለኛል።
ይህንን ጉዳዩ ስጋ አልብሰን፤ በሰውኛ ስንገልጸው፦ አዜብ መስፍን ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ፈረስ ጋልቦ የማይጨርሰው መሬት የወሰደቺው ከአስቴር ማሞ ጋር በነበራት “መርህ አልባ ግንኙነት” ነው ማለት ይሆናል። በኢንቨስተር ስም የጋንቤላን ለም መሬት የተቀራመቱት በሙሉ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር በተፈጠረ መርህ አልባ ግንኙነት መሆኑ ይታየናል። ሌላም ሌላም …. ከየክልሉመዘዘር ይቻላል።
ባጠቃላይ የህወሃት ባለስልጣናት (ከተራው ባለስልጣን ጀምሮ) በኦሮሚያ ፤በአማራ ፤ በጋንቤላ፤በቤናሻጉንና ….በሌሎቹም የሃገሪቷ ክፍሎች ጥንብ እንዳየ አሞራ እያንዣበቡ መሬትና፤ ሃብት የሚያጋብሱት ከየክልሉ ባልስልጣናት ጋር በመሰረቱት በዚሁ መርህ የለሽ ግንኙነት ነው። የፍትህ አልባው ሃብት ሽግግር ሃዲድ መርህ አልባው ግንኙነት መሆኑ ነው።
በነገራችን ላይ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ “መርህ አልባ ግንኙነት” ነው በሚል የጠቀሰው የድክመት መገለጫ አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው፤ መርህ አልባው ግንኙነት በማና በማን መካከል? ለሚለው ጥያቄ በቂ ማብራሪያ ስላልነበረው ይመስለኛል። ከአቶ ለማ መግለጫ በኋላ ግን ግንኙነቱ በማና በማን መካከል እንደሆነ ግልጽ ሆኗል። የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ደግሞ በስነ-ቃሉ ላይ መሻሻያ ማድረግ ጥሩ ይመስለኛል። “መርህ አልባ የባለስልጣናት ግንኙነት” ቢባል አሻሚነቱ ይወገዳል። ቢያንስ ቢያንስ መርህ አልባ የሚለው በህዝብ መሃል የሚኖረውን ግንኙነት እንዳልሆነ ግልጽ ያደርገዋል።
በመሰረቱ በህዝብ መሃል የሚኖር ግንኙነት በመርህ የሚታሰር አይደለም። በህዝብ መሃል የሚኖርን ግንኙነት በመርህ ለማሰር የሚደነግገው “የጎሳ ፖለቲካ” ነው። የህወሃትም መሰረታዊ ችግር ይኽው ነው። በህዝብ መሃል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት የመገደብና የማደፍረስ አባዜ ። በኦሮሞና በአማራ ህዝብ መሃል እየጎለበተ ያለው ግንኙነት ትልቅ ድንጋጤ የፈጠረባቸውም ይህን አባዜያቸውን አርክሶና በጣጥሶ በመውጣቱ ነው።
በህዝብ መሃል የሚኖር ግንኙነት ባህል፤ ታሪክ፤ መልክዓምድር ፤ ስነ ልቦና ….የመሳሰሉትን ነባራዊ መስተጋብሮችን መሰረት የሚያደርግ እንጂ የፖለቲካ ድርጅቶች በመርህነት በሚቋጥሩት አንቀጾች የሚገደብ ወይም የሚታሰር አይደለም። በሌላ አገላለጽ ኢህአዴግ በውስጡ ያካተታቸውን ድርጅቶች ግንኙነት እንጂ ድርጅቶቹ እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ መስተጋብር በውስጠ ደምብ ሆነ በመርህ ሊያስር አይችልም ማለት ነው።
ወደ ቆየው ነገሬ ስመለስ፡ በአቶ ለማ ጋዜጣዊ መግለጫ ግልጽ ሆኖ እንደተቀመጠው መርህ አልባው ግንኙነት
ከድርጅቱ(ኢህአዴግ) መርህ ውጭ በህውሃት ባለስልጣናትና በሌሎች ክልል ባለስልጣናት መሃል የተዘረጋ ግንኙነት (ኔት ወርክ) ነው።
ከዚህ በመነሳት እስካሁን ያለንን መረጃ ስንመረምር ደግሞ የምናገኘው እውነት፡ ኔት ወርኩ ወይም “መርህ አልባው የባለስልጣናቱ ግንኙነት” የተዘረጋው ከህወሃት ጓዳ ወደ ተለያዩ ክልሎች ብቻ ነው (One-to- Many Relationship)። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እውነተኛው የሃይል ምንጭ (Power) ያለው በህወሃት ጓዳ መሆኑ ነው።
በህወሃት በኩል ያላለፈ የኔት ወርክ መስመር ቢዘረጋም ሃይል ስለማያገኝ አይሰራም። ላለፉት 26 አመታት ሌሎች ክልሎች እርስ በእርስ የግንኙነት መስመር ሊዘረጉ ያልቻሉትም ለዚህ ነው ። ህወሃት ይህን አይቀበልም።

በቅርቡ ግን ይህን ለ26 ዓመታት የቆየ እውነት የሻረ ድንገቴ ተከስቷል። የህወሃትን ጓዳ bypass ያደረገ ኔት ወርክ ተዘርግቷል። በኦሮሞና በአማራ ክልል እየተዘረጋ ያለው ግንኙነት የህወሃትን ጓዳ በኃይል(Power) ምንጭነት መጠቀም ግድ ሳይለው እየተቀጣጠለ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የለማ መገርሳና የገዱ አንዳርጋቸው ግንኙነት በአዜብ መስፍንና በአስቴር ማሞ መካከል እንደነበረው መርህ አልባ የባለስልጣናት ግንኙነት ሳይሆን የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመሆኑና የሃይል ምንጩም ህዝብ መሆኑ ነው። ዓላማውም ሰላምና ፍቅር ነው።
በተቃራኒው የህወሃት ባለስልጣናት ከሌሎች ክልል ባለስልጣናት ጋር የዘረጉት ኔት ወርክ (መርህ አልባ ግንኙነት) የኃይል ምንጩ ጠመንጃ ሲሆን አላማውም ዘረፋ።
እንግዲህ ከላይ በዝርዝ እንደተመለከትነው ተነጥሎ ሊወገዝ የሚገባውም የህወሃት ባለስልጣናት ከክልል ባለስልጣናት ጋር የዘረጉት “መርህ አልባ የባለስልጣኖች ግንኙነት” ነው። ነገር ግን በህወሃት ጓዳ “መርህ አልባ ግንኙነት” የሚለው ሥነ-ቃል ድብቅ ትርጉሙ (ወርቁ) በህዝብ መሃል (ለምሳሌ በኦሮሞና በአማራ…) የተጀመረውን አይነት ግንኙነት ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር አይከፋም። ያምሆነ ይህ በህዝብ መሃል የሚኖር ግንኙነት በመርህ ሊታሰር ስለማይችል የሚያሳስብ አይሆንም።
ህወሃት በባህሪው የማይቆጣጠርው ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዲኖር የማይፈልግና ጥላውን የሚጠራጠር በመሆኑ፤ “የኦሮሞ ደም ደሜ ነው” የሚለው የጎንድሬው መፈክር ሁሌም ያቃዠዋል። “አባይ ኬኛ!” የሚለው የኦሮሞው ድምጽ ዘወትር ያባንነዋል። ይህን አልፎም በሁለቱ ታላላቅ ብሄሮች ፍቅር ኢትዮጵያዊነት ሲደምቅና ሲወደስ ማየትና መስማት ያመዋል። መፍትሄው ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን የበለጠ በማድመቅ ህመሙን አባብሶ ወደ መቃብር የሚያደርገውን ጉዞ ማፋጠን ነው።

አዜብ ጌታቸው
azebgeta@gmail.com

Filed in: Amharic