ለምን አወዳደቃችሁን አታሳምሩም?
ኧረ በልጆቻችሁ ይሁንባችሁ – የኢትዮጵያን ህዝብ ተፋቱት? ህዝቡ ካሰራችኋቸው ሰዎችና ከናንተ ምረጥ ቢባል ምርጫው ምን ሊሆን እንደሚችል በደንብ ታውቃላችሁ። ግድየለም እሱንም ተውት። የህዝብ ፍላጎትና ስሜት ለናንተ ምናችሁም አይደል። በናንተ ቤት ህዝብን መውደድ ወንጀል ነው። እነለማን ባቆሰላችሁበት እልህ አስጨራሽ ግገማችሁ “ህዝባዊነት” የምትል አዲስ የፍረጃ/መወንጀያ ቋንቋ ፈጥራችኋል።
በናንተ አስተሳሰብ ህዝብን መውደድና በህዝብ መወደድ ወንጀል ነው። ያሰራችኋቸው ሰዎች በህዝብና በሀገር ፍቅር ከመናወዝና አፋኝ ሥርዓትን ከመታገል ውጭ ሌላ ወንጀል እንዳልፈፀሙ አሳምራችሁ ታውቃላችሁ። ህዝቡ እናንተን እንደማይፈልግና ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ከገባችሁ ቆይቷል።
ታዲያ ምን ዓይነት ቁማር ነው የምትጫወቱት? እባካችሁ በገባችሁት ቃል መሠረት ያሰራችኋቸውን ንፁሃን ዜጎች ቶሎ ፍቷቸው። በቃላችሁ መሠረት ለመፈፀም በዘገያችሁ ቁጥር ራሳችሁን በፍጥነት ወደ ውድቀት አፋፍ እየገፋችሁ ነው። መውደቃችሁ ባይቀርም አወዳደቃችሁን ማሳመር ትችላላችሁ።
