>

ዲፕሎማሲ ቀረ ቢሉ፣ ጥገኝነት ቀረ! ( በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

(No Diplomacy, No Dependency: https://t.co/ydKhIqA7g5?amp=1)

ሁሉም ለውጦች ከአገር ውስጥ መፍለቅ አለባቸው ብዬ አምናለሁ። የመጨረሻው ውሳኔ የኛው መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ኃያላኑ አገራት በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም ማለት አይደለም። እንዲያውም ያልተመጣጠነ የውሳኔ ድርሻ አላቸው። የሚያሳዝነው ግን ላሸናፊው (ሥልጣን እና መሣሪያ ለያዘው) ነው የሚወግኑት። ዓለምዐቀፍ ቃልኪዳኖች፣ ስምምነቶች፣ የወዳጅነት እሴቶች እና ሌሎችም ተስፋ ያጣውን ብዙኃን በከንቱ ተስፋ እያባበሉ አምባገነኖቹ ሥልጣናቸውን እንዲያደላድሉ መርጃ መሣሪያዎች ሆነዋል።

ከምርጫ 97 በኋላ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ኢሕአዴግ ያመለጠው በኃያላኑ መንግሥታት እርዳታ ነው። ዛሬም እንደያኔው ኃያላኑ መንግሥታት እና ዲፕሎማቶቻቸው አገዛዙ እንዲቀጥል እየጣሩ ነው። ይህን የሚያደርጉበት ዋነኛ ምክንያት የሚከተሉት ናቸው፦

1. የማያውቁት መልአክ

አፍሪካ ቀንድ የቀውስ መዲና ናት። ሶማሊያ ላለፉት ዓሥርት ዓመታት መንግሥት አልባ ናት፣ ደቡብ ሱዳን በግጭት እየታመሰች ነው፣ ኤርትራ እና ሱዳን ለምዕራቡ ዓለም ታዛዥ አይደሉም። ኬንያ ጠንካራ ሠራዊት የላትም፣ የጅቡቲ ወዳጅነት ደግሞ በጣም ትንሽ ፋይዳ ነው ያለው። መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ላይ ማንም ለውጥ የሚያመጣውን ያልታወቀ ነገር ለመሞከር አይደፍርም። በዚያ ላይ የኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ እልፍ ስደተኞችን ተቀባይ አገር ነች። እሷ ራሷ ተጨማሪ የስደተኞች ምንጭ እንድትሆን አይፈለግም። (በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ እነዚህን ስደተኞች በስደተኛ ካምፖቿ ለማኖር የምትቀበለው እርዳታ ወደ ደኅንነት ቢሮ ነው የሚሔደው። ደኅንነቱ ደግሞ ገንዘቡን ዜጎች ይሰልልበታል።)

የሆነው ሆኖ፣ ኃያላኑ አገራት በኢትዮጵያ “አትነካኳት” ዓይነት ስልት እየተከተሉ ነው። አካባቢው ላይ ተጨማሪ ቀውስ ለማስወገድ የሚደረግ ጥረት መሆኑ ነው። ነገር ግን ጭቆና ባለበት ሕዝባዊ ቁጣ የማይቀር በመሆኑ የነርሱ ፀጥታ ተኮር መረጋጋት አዋጭ ስልት አይደለም። ስለሆነም አማራጭ ኃይሎችን መደገፍ እና ማጠናከር ላይ ቢሠሩ ከሚፈሩት ትርምስ የተሻለ ውጤት የሚያስገኝ ስልት በመሆኑ የታክስ ከፋይ ዜጎቻቸውን ገንዘብ ቁም ነገር ላይ ማዋል ይችሉ ነበር።

2. ወታደራዊ ተረት

ኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ቡድን በየቦታው ትልካለች። ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ኢትዮጵያ የሠላም አስከባሪ ቡድኗን የላከችባቸው የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የሠላም ተልዕኮዎች አካል ናቸው። እነዚህ ተልዕኮዎች ለኢትዮጵያ ወታደሮች ምንም እውነተኛ አደጋ የሌለባቸው ጥሩ የገቢ ምንጭ ናቸው። እንዲያውም፣ የሠላም አስከባሪ ቡድኖቹ አባል ሆኖ ለመሔድ ያለው ሽሚያ የሙስና ምንጭ ሆኗል። ነገር ግን ዓለምዐቀፉ ማኅበረሰብ በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያን (በተለይ መንግሥቷን) የሠላም አጋር አድርጎ ነው የሚመለከተው። በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ከሶማሊያው አል ሸባብ ጋር የምትዋጋው “የውክልና ጦርነት” አለ። ለዚህም፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ አምባገነኑን የኢትዮጵያ መንግሥት “በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ” ብለው አወድሰውታል። እግረ መንገዳቸውንም፣ አሜሪካ እዚህ ድረስ ሠራዊት መላክ አላስፈለጋትም ምክንያቱም የኢትዮጵያ ወታደሮች ለዚህ አያንሱም ብለዋል።

ኃያላኑ መንግሥታት ኢትዮጵያ “የውክልና ውጊያውን” ለመዋጋት ፈቃደኛ እስከሆነች ድረስ መደጋፋቸውን አያቆሙም። ነገር ግን ወታደራዊ ተልዕኮዎቹ የኢኮኖሚ ጥቅም እስካላቸው ድረስ አገዛዙ ቢቀየርም አይቋረጥም። ይህንን ድጋፍ አድራጊዎቹ የተረዱት አይመስልም።

3. የልማት አጋርነት እቃቃ

አጋርነት ሁለትዮሽ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ግን “የልማት እርዳታ” የሚለውን ቃል በይፋ ሰርዞ “የልማት አጋርነት” እያለ መጥራት ጀምሯል። የልማት እርዳታው ግን የሚፈሰው ወዳንድ አቅጣጫ ብቻ ነው። በፊት በፊት፣ ሟቹ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች በሠላም ሥም ፀጥታ የሚፈልጉትን ኃያላኑን አገሮች ካልረዳችሁን እንበጣበጥና ሠላማችሁን እናደፈርሳለን እያሉ ያስፈራሩዋቸው ነበር። አሁን ይሔ ትርክታቸው ተቀባይነት አግኝቶ ‘ቀዝቃዛው ጦርነት’ ሲያበቃ የገቡትን ቃል አሰርዟቸዋል። ያኔ የገቡት ቃል የዜጎቻቸውን መብት የማያከብሩ መንግሥታትን አለመርዳት የሚል ነበር።

ሲቪል ማኅበራት ዜጎች ስለመብቶቻቸው ከማሳወቅም ባሻገር መንግሥት እንዲያከብርላቸው ነው የሚሠሩት። ይህን ለማድረግ ከውጭ የመብቶች ተቆርቋሪ አካላት የገቢ ምንጮችን ያፈላልጋሉ። እንደኛ ችጋር የደቆሰው ሕዝብ ሲቪል ማኅበራትን የመደገፍ አቅም የለውም። ሟቹ መለስ “በውጭ እርዳታ የበለፀገ የለም” ብለው ነበር። ነገር ግን የልማት እርዳታ ተከልክሎ አያውቅም። የተከለከለው የሲቪል ማኅበራት እርዳታ ነው። በዚህ መንገድ፣ በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት እንዴት እንደሚያጠፋው የሚጠይቀው ሳይኖር የልማት እርዳታውን ይቀበላል። የተለያዩ ሪፖርች የልማት እርዳታ ዜጎችን ለመጨቆን እንደዋለ ቢያጋልጡም፣ የበለፀጉት አገራት “የልማት አጋርነታቸውን” ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል።

ሲቪል ማኅበራትን በማሳደድ እና በማዳከም፣ መንግሥት ብቸኛው የስታትስቲክስ አምራች ሆኗል። ለአምባገነናዊ አገዛዙ የሚፈስሰው እርዳታም እንደቀጠለ ነው። ማንም የዕድገቱ ቁጥር ከየት እንደመጣ ለማወቅ አይገድደውም። ማንም የሀብት ፍሰቱ ወዴት እንደሆነ አይጠይቅም።

4. የቻይና ምፅአት

ቻይና አምባገነናዊነትን የምታበረታታ የአምባገነኖች አገር ነች። ቻይና ትንሽ ዕርዳታ እና ብዙ ብድር በቢዝነስ አጋርነት መርሕ ያለምንም ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታ የምታበረክት አገር ነች። በአገሮች የውስጥ ጉዳይ አያገባኝም ትላለች። ኢትዮጵያን ደግሞ ለአፍሪካ ገበያዋ ምርቷን እንደማሳያ ሱቅ ነው የምትመለከታት። ይህ ምዕራባውያኑን ስላስደነገጣችው እርሷኑ እየመሰሉ ነው። ሒደቱ ለአፍሪካውያን አምባገነኖች የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል። የአፍሪካ አገሮችን ለአጋርነት የመቀራመቱ ሒደት በቻይናውያን እና በምዕራቡ ዓለም በጦፈ ቁጥር፣ የአፍሪካ አምባገነኖች መረን እየወጡ ነው።

የጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የሚል ውንጀላም አለ። አፍሪካውያን አምባገነኖች የልማት ዕርዳታ መቀበል ይፈልጋሉ፣ ነገር ግን ገንዘቡን እንዴት እንደሚያጠፉት መናገር አይፈልጉም። የቅኝ አገዛዝን ታሪክ እያስታወሱ ማሸማቀቅን እንደስልት ይዘውታል። ቻይና ደግሞ በዚህ አትታማም። ስለዚህ አምባገነኖቹ ቻይናን ለምዕራባውያን እንደ መልካም የአጋርነት አርአያ ያውለበልቧታል።

መደምደሚያ፣ ለኛ ከኛ ወዲያ!

ምዕራባውያን እና ብዙዎቹ ዲፕሎማቶቻቸው አገዛዙ ጉዞውን እንዲቀጥል ከማገዝ ወዲያ ፋይዳ እንደሌላቸው እያሳዩ ነው። የኃያላኑ መንግሥታት የማይተገበሩ የተስፋ ቃላትን ተስፋ እያደረጉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ቆም ብለው ወደውስጣቸው የሚመለከቱበት ግዜ አሁን ነው። ለእነርሱ፣ እኛ በደጉ ግዜ ገበያቸው፣ በክፉው ግዜ ደግሞ ስደተኛ ማምረቻቸው ነን። አገራችንን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በምናደርገው መስዋዕትነት ውስጥ የሚገባንን ድጋፍ አያደርጉልንም። ኃያላኑ አገራት መደገፍ የሚፈልጉት ብዙኃኑን ፀጥ የሚያስብል ኃይል ያለውን አካል ነው። ሕዝባዊ ቁጣዎች ለኛ የጭቆና እምቢ ባይነት ነው፤ ለነርሱ፣ የአንድ የገበያ ቦታ መረበሽ ወይም የስደተኛ ማፍለቂያ መንስዔ ነው።

በኔ አተያይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊዎች ዕርዳታዎቻቸውን በቅድመ ሁኔታ እንዲያደርጉት ለማድረግ በቂ ጉልበት ባክኗል። ነገር ግን መጀመሪያ አሸንፎ መደራደር ነው የሚያዋጣው። የኛን አምባገነኖች እኛው ራሳችን መዋጋት አለብን። እንደራጅ፣ እንነቃነቅ እና ለክብራችን እንቁም። ያኔ ሁሉም ከኛ ጋር ይቆማል።

Filed in: Amharic