>

ሼህ መሃመድ አላሙዲንን ጨምሮ 60 ያህል እስረኞች ከሆቴል ወደ ወህኒ ቤት ተሸጋገሩ

ኢሳት

የሳውዳረቢያ መንግስት በድርድር እንዲፈቱ የጣለባቸውን የገንዘብ መጠን ለመክፈል ያልፈቀዱት እስረኞች በወህኒ ሆነው የሙስና ክስ እንደሚመሰረትባቸውም ተመልክቷል። ምግብን ሳይጨምር ለመኝታ ብቻ በቀን 800 ዶላር እየተከፈለላቸው በዘመናዊው ሪትዝ ካርልተን ሆቴል ውስጥ የነበሩት ልኡላንና ባለጸጎች አልሔር ወደ ተባለው ወህኒ ቤት የተዛወሩት ከሶስት ቀናት በፊት መሆኑን ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል። 800 ቢሊየን ዶላር ያህል የባንክ ተቀማጭ ገንዘብ የታገደ ሲሆን ታሳሪዎቹ በድርድር የሃብታቸውን 70 በመቶ ከፍለው እንዲወጡ አማራጭ ተሰጥቷቸው እንደነበር አይዘነጋም። ከሶስት ቀናት በፊት ከሪትዝ ካልተን ሆቴል አልሔር ወደ ተባለው ወህኒ ቤት የተሸጋገሩት እስረኞች 60 ያህል መሆናቸው ታውቋል። በአረቡ አለም ቁጥር አንድ ባለሃብት የሆኑት ልኡል አልዋሲድ ቢን ታላልን ጨምሮ በአረቡ አለም ሁለተኛ ባለጸጋ የሆኑትን ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ሼህ መሀመድ አላሙዲንን አክሎ በወህኒ ቤት የሚገኙት እስረኞች ክስ ሳይመሰረትባቸው በድርድር እንዲፈቱ የሳውዲ መንግስት አማራጭ እንዳቀረበላቸው ሲገለጽ ቆይቷል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሕዳር 4/2017 በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎም በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ 1 ሺ 200 የባንክ ተቀማጮች ታግደዋል። የዚህም ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 800 ቢሊየን ዶላር እንደሆነም ታውቋል። ልኡላኑንና ባላሀብቶቹን በሙስና የወነጀለው የሳውዳረቢያ መንግስት ከተከሳሾቹ ከአንድ መቶ እስከ 3 መቶ ቢሊየን ዶላር ለማስመለስ ማቀዱንም ይፋ አድርጓል። ጉዳዩ ወደ ክስ ከማምራቱ በፊት ተከሳሾቹ በሳውዲ ከሚገኘው ሃብታቸው እስከ 70 በመቶ ለሳውዳረቢያ መንግስት ለመመለስ ወይንም ለመስጠት ከተስማሙ ክስ ሳይመሰረትባቸው በነጻ እንደሚለቀቁ ቃል ተገብቶላቸዋል። የተወሰኑት እስረኞች የተጠየቁትን በማሟላታቸው ከእስራት ነጻ ወጥተዋል። ሌሎቹም ይህንን ከፈጸሙ ከአዲሱ የፈረንጆቹ አመት በፊት እንደሚለቀቁ ቃል የተገባ ቢሆንም ለመክፈል ባለመፍቀዳቸው ከሆቴል ወደ ወህኒ መሻገራቸው ታውቋል። ለአምስቱ ሮያል ስዊት ለተባሉት ክፍሎች ለእያንዳንዳቸው በቀን የሚከፈለውን 7ሺ ዶላር ጨምሮ ምግብን ሳያካትት በየቀኑ ወደ 425 ሺ ዶላር የሳውዲ መንግስት ወጪ ሲያደርግ ቆይቷል። ሚድል ኢስት ሞኒተር እንደዘገበው ታሳሪዎቹ የተዛወሩበት አልሔር የተባለው ወህኒ ቤት አሸባሪዎችና በሳውዳረቢያ ለውጥ ፈላጊዎች የሚታሰሩበትና ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ወህኒ ቤት ነው።

Filed in: Amharic