>

የመቀሌው ስብሰባና የ'ፖለቲካ እስረኞች' ፍቺ (መሳይ መኮንን)

ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ሰዓት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ መግለጫ እየሰጡ ነው። የእስረኞችን መፈታት በተመለከተ ትላንት መግለጫ እንደሚሰጡ ስንሰማ መቀሌ ወሰነች ብለን ነበር። ምክንያቱም የእስረኞች መፈታት ወሬ ከሃይለማርያም አፍ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በህወሀት መንደር የፈጠረው መንጫጫት የተባለው እንደማይሆን ከምልክትም በላይ ነበርና ነው። ከጠቅላይ አቃቤ ህጉ የዛሬ መግለጫ ለመረዳት እንደተቻለው ግን የሚፈታ የፖለቲካ እስረኛ የለም።

ክሳቸው ተቋርጦ፡ የሁለት ቀናት ተሀድሶ ተሰጥቷቸው የሚለቀቁት 528 እስረኞች ህገመንግሥቱን ወይም ህገመንግሥታዊ ስርዓቱን የመናድ እንቅስቃሴ ላይ ያልተሳተፉ ወይም ያልመሩ፡ በከፍተኛ የኢኮኖሚ አውታሮች ላይ ጉዳት ለማድረስ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ያልተሳተፉ ወይም ያልመሩ፡ የሰው ህይወት ያላጠፉ ወይም በአካል ላይ ከባድ ጉዳት ያላደረሱ የሚል መስፈርት ተቀምጦ የተመረጡ ናቸው። በአጭሩ የምንፈታው የፖለቲካ እስረኛ የለም ማለት ነው። ያለወንጀላቸው፡ ወንጀል የተለጠፈባቸው፡ ያለሃጢያታቸው ሃጢያት የተከመረባቸው፡ የፖለቲካ እስረኞች ከላይ ከተቀመጡት መስፈርቶች በአንዱ ወይም በሶስቱም የተከሰሱ በመሆናቸው የመቀሌው የምህረት ውሳኔ የሚመለከታቸው አይደለም።

በቀውስ የሚናጠው ህወሀት መፍታትም አለመፍታትም ችግር ሆኖበታል። ምናልባት መቀሌ ላይ የተሰበሰቡት ህወሀቶች ከደህንነት መስሪያ ቤቱ የተሰጣቸው ስም ዝርዝር ላይ ከውሳኔ ደርሰው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ሰጥተን ነበር። ከጠቅላይ አቃቤ ህጉ የዛሬው መግለጫ መረዳት የሚቻለው የፖለቲካ እስረኞች እንዳይፈቱ የተቀጣጠለው የህወሀት ደጋፊዎች ጫጫታ አሸናፊ መሆኑን ነው። ህወሀት የመጣበትን ውጪያዊ አደጋ ለመመከት ቅድሚያ ከውስጡ እንደቋያ እሳት የሚንቀለቀለውን የደጋፊዎቹንና አባላቱን ቁጣና ተቃውሞ ለማብረድ ጓዙን ጠቅልሎ መቀሌ ገብቷል። በእርግጥ ደጋፊዎቹና አባላቱ የሚያማቸው የሌላው ኢትዮጵያዊ ህመም አይደለም። የሚያስቆጣቸው፡ የሚያንጨረጭራቸው የነጻነትና የፍትህ ረሃብ አይደለም። ሌላው ቢቀር በሚፈቱት እስረኞች ላይ ከህወሀት ደጋፊዎች መንደር የሚሰማው ትርክት ለቅሶአችን ለየቅል መሆኑን የሚሳይ ነው።

ከመቀሌ የተለየ ነገር አይጠበቅም። የስብሰባ ጋጋታ የህወሀትን ሞት የሚያስቀረው እንዳልሆነ ይታመናል። በውስጣቸው የገባውን ትርምስ በውይይት መፍታት ስላልቻሉ ለጊዜው የተወሰኑ እስረኞችን በመልቀቅ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስ የወሰኑ ይመስላል። ከፌስ ቡክ ሰራዊት እስከ ዲያስፖራ የህወሀት ክንፍ፡ ታች ወረዳ እስካለው አመራር የከተተበት የመቀሌው ግርግር የህወሀትን ዕድሜ ለማራዘም የሚቻለውን እያደረገ ቢሆንም ብዙም ውጤታማ እንዳልሆነ ሾልከው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። በሚፈቱት ሰዎች ላይ በህወህቶች መሃል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የትግራይ ሽማግሌዎች ልመና ውስጥ ገብተው እንደነበርም ይነገራል። በልመና የሚፈቱት እነማን እንደሆኑ ፍንጩን አውቀናል። የኢትዮጵያ ህዝብ በትግሉ እንጂ ደጅ በመጥናት መብቱን እንደማይጠይቅ ታሪክ ምስክር መሆኑን ህወሀቶች ዘንግተውታል።

ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እየጠበቀ ነው። የህወሀት ቀለብ ሰፋሪዎች ህወሀት ቃሉን እንዲያከብር በጓሮ በኩል ውትወታ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል። የዛሬውን የጠቅላይ አቃቤ ህጉ መግለጫ ከሰሙ በኋላ ምን ሊሉ እንደሚችሉ አናውቅም። ህወሀትን እያባበሉ እዚህ ያደረሱ በመሆናቸው አንድም እስረኛ ቢለቀቅ ”ጥሩ ጅምር ነው” በሚል ሊያሞካሹት እንደሚችሉ ይጠበቃል። ”እሱን ይዛችሁ ደግሞ ሌላውን ጠይቁ። ለውይይት በር የሚከፍት መልካም ውሳኔ ነው” ከሚል ጫና ጋር ምዕራባውያን መንግስታት ምላሽ መስጠታቸው የማይቀር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበትን መንገሽገሽ የሚመጥን እንደማይሆን ቢነገራቸው ላይገባቸው ይችላል። የእነሱ ጭንቀት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጋተው መከራና ስቃይ አይደለም። ህወሀት ተጠጋግኖ፡ አፈር ልሶ፡ እንደምንም ቆሞ በስልጣን ቢቆይላቸው ደስታቸው ወደር የለውም። ችግሩ ህወሀት ፈውስ በሌለው፡በማይድን በሽታ የሚሰቃይ ሆኖባቸው እንጂ።

Filed in: Amharic