ቤተክርስቲያን እንዳስተማረችን ወደ እግዚአብሔር ለሄደው፣ ክብር ላገኘው አይደለም የምናዝነው ህሊናው ታውሮ እንደ ቃኤል የወንድሙን ደም ለሚያፈሰው እንጅ። በተለያየ ምክንያት ክርስቲያኖችን የምትገድሉ ወዮላችሁ። ነገር ግን ምናልባት በመግደላችሁ እነሱን የጎዳችሁ ከመሰላችሁ አሁንም እላለሁ ለእናንተ በብዙ አዝናለሁ ወዮላችሁ። ክብር እንጅ የምታጎድሉባቸው ነገር የለም። ሰይጣን ዲያቢሎስ አዳምን ለሞት የሚያበቃ ተንኮል ቢሰራበት በኋለኛው ዘመን አምላክ ሰው ሆኖ ሰው አምላክ እንዲሆን ነው ያደረገው። የምድሩን ክብር ለማሳጣት ተንኮል ቢሰራበት ሰማያዊ ክብር እንዲጨመርለት ነው ያደረገው። ክርስቲያን በሥጋ ከሚኖረው ይልቅ ከሞተ በኋላ የሚያገኘው ክብር ። ይበልጣል። እኛ አባታችን በሰማይ ነው።”፤ እግዚአብሔር በተቀደሰው መቅደሱ ነው፤ እግዚአብሔር፥ ዙፋኑ በሰማይ ነው፤ ዓይኖቹ ወደ ድሃ ይመለከታሉ፥ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ። ” (መዝ 11: 4) “፤ እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ ( ፊልጵ3:፥20)።” ስለዚህ እናንተ ገዳዮች የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እየሞታችሁ ያላችሁ እናንተ ናችሁ። ክርስቲያን ቢሞት ወደ ተሻለ ቦታ፣ ወደሚወደው ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር ፣ ወደ ዘላለም መኖሪያ ሀገሩ መንግስተ ሰማያት ነው የሚሄደው ። ብትገድሉትም ብትተውትም የሥጋ ሞት አይቀርም።የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል። ” ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን ሮሜ 14፥7 ” ዛሬ ህሊናችሁ ታውሮ ማየት ቢሳናችሁ የፍጥረታት ባለቤት ለፍጥረቱ የሚፈርድበት ጊዜ አለና ንስሃ ግቡ። ” ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ። ” (1ኛ ቆሮ 3: 17) ተብሎ እንደተጻፈ ዛሬ እንደቀላል የምታፈሱት ደም ነገ ብዙ ዋጋ ያስከፍላልና ቆም ብላችሁ አስቡ። “፤ እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ” (ሉቃ 6: 25) ።
በሥጋ እየሞትን በመንፈስ እየኖርን እግዚአብሔርን እናመልካለን (ቀሲስ ዘላለም ጽጌ)
Filed in: Amharic