>

ህወሀቶች መቀሌ ላይ የቀመሙትን መርዝ በእጅ አዙር ሊረጩት ተሰማርተዋል (መሳይ መኮንን)

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ጆሮና አይኔ ወሎ ላይ ተተክሎ ሰንብቷል። ከወልዲያው ጭፍጨፋ፡ ከቆቦዎች አይበገሬነት እስከመርሳዎች ጀግንነት፡ ክስተቶችን እዚያው አጠገባቸው እንዳለ ሆኜ ነበር ስከታተል የቆየሁት። ስሜቴ ከወዲህ ውዲያ ሲላጋ፡ ቅጭም ሲል፡ በሀዘን ሲመታ፡ ደግሞም በጀግንነታቸው ልቤ ሲሞቅ፡ ወዲያኑም በሚደርስባቸው የግፍ በትር ውስጤ ሲደማ፡ በሞታቸው ኩምትር ስልበወርቃማ መስዋዕትነታቸው ስጽናና፡ እንዲሁ ላይ ታች ስል ሰነበትኩ። አሁንም ከዚያው ነኝ። ከወልዲያ ምድር፡ ከቆቦዎች መንደር፡ ከሮቢት ሰፈር፡ ከሀራ ገበያ፡ ከጎቢዬዎች ሀገር፡ ከመርሳዎች መንደር፡፡ የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም የሚለው አባባል አይገባኝም። ወሎን ባላውቀውም ይናፍቀኛል።

ፖለቲካው ግሏል። ሙቀቱ ጨምሯል። ህወሀቶች መቀሌ ላይ የቀመሙትን መርዝ በእጅ አዙር ሊረጩት ተሰማርተዋል። የዘርዓይ አስገዶም ያልተጠና ዲስኩር የህወሀቶችን ቀጣይ አካሄድ እርቃኑን ያጋለጠው ሆኗል። አንጻራዊ የህዝብ ድምጽ በማሰማት ቀና ማለት የጀመሩትን የኦሮሞ ብሮድካስት ኔትወርክና የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅትን ወደ ቀድሞ አገልጋይነታቸውና በቀቀንነታቸው ለመመለስ በህወሀት አማካኝነት የተዘጋጀውና እነዘርዓይ የተላኩበት ዘመቻ ድባቅ ሲመታ ለመታዘብ ችለናል። አፋቸው ተሎጉሞ የከረሙት ወይም ከህወሀት አገልጋይነት መላቀቅ አቅቷቸው ህዝባቸውን ሲያሳዝኑ የምናውቃቸው እነንጉሱ ጥላሁን እንኳን አፍ አውጥተው፡ ወኔ አግኝተው፡ ድፍረት ተላብሰው ”በዘረኝነት ትዕቢት የተወጠረውን” ዘርዓይን እሳት እንዳየ ላስቲክ ኩምሽሽ ሲያደርጉት አይተናል።

ህወሀት በደም ነፍስ የቀረ አገዛዝ ሆኗል። በደህንነቱና መከላከያው ብቻ እየተነፈሰ ነው።የእነዚህ ሁለት ተቋማትም ነገር የጊዜ ጉዳይ እንጂ የህወሀት ማጥፊያ መድሃኒት መሆናቸው አይቀርም። ህወሀት የበተናቸውን መሰብሰብ አቅቶታል። ያሰለጠናቸውን ማዘዝ ተስኖታል። ባሪያዎቹ እየፈነገሉት ነው። ቀኝ እጄ የሚላቸው እየካዱት ነው። ህዝቡ አልታዘዝ ብሏል። ለሚያወጣቸው ህጎች ጀርባውን እየሰጠ። ማስፈራራያውን ከቁብም የሚቆጥር የለም። ግድያ የማያስበረግገው፡ ጭፍጨፋ የማያስፈራው፡ የአጋዚ ጭካኔ፡ የቅልብ ፌደራል ዱላ፡ የመከላከያ አፈሙዝ የማያስደነግጠው፡ ልበ ሙሉ፡ ሞትን የማይፈራ፡ ደረቱን ለጥይት የሚሰጥ ደፋር ትውልድ እዚህም እዚያም ተፈጥሯል።

በቅርቡ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ”በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሰልፍ የተከለከለ ነው” ብሎ ካስጠነቀቀ ወዲህ ሁሉን ነገር የተቆጣጠረ መስሎት ነበር። አዋጁን ያነበበው ሲራጅ ፈርጌሳ ቃለመጠይቁ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተላልፎ ሳያልቅ በማግስቱ የህዝብ እምቢተኝነት በየቦታው ተቀስቅሷል። ወልቂጤም ተቀላቀለች። አርባምንጭ ተነሳች። ወሎ አቀጣጠለች። ከእንግዲህ የሚመልሰው አይኖርም። ነጻነት የሸሸተውን ህዝብ ማን ሊያቆመው?

ትላንት ማታ እዚህ አሜሪካ የህወሀቱ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ለ400 የህወሀት ደጋፊዎች በተዘጋጀ የቴሌ ኮንፈረንስ ላይ ተገኝቶ ያደረገው የመግቢያ ንግግር ላይ እንዲህ አለ ”ይህቺን ሀገር ያቆምናት በመርህ ነው። ምንም ማዕበል ቢመጣ፡ ወጀቡ ቢያሰፈራ ለጊዜው እንጂ ያቆምነውን መሰረት የሚንድ አይሆንም። ” ቴሌ ኮንፈረሱ በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ሱናሚ ተቋርጦ፡ ካሳ ተክለብርሃንም ስልኩን ዘግቶ ጠፋ። ኢትዮጵያውያኑ ” ብሶት የወለደው ጀግናው የኢትዮጵያ ልጅ ለዘመናት ወያኔ ሲጠቀምበት የነበረውን ቴሌኮንፍረንስ ተቆጣጥሮታል። ጉንበት…..” እያሉ በመድረኩ ቆዩበት።

ካሳ ተክለብርሃን ይህቺን ሀገር ያቆምናት በመርህ ነው አለና አረፈው። መቼም ይሉኝታ ሲከዳ፡ ሞራል ሲላሽቅ የማትደፍረው ነገር የለም። የፈጣሪን ዕይን መጠንቆልም አይቀርም። ድንቁርና ከእውቀት ጋር ቦታ በተቀያየሩበት የህወሀት ሰፈር ”መርህ” የሚለው ቃል አፋቸው ላይ ሲመላለስ መስማት ያሳፍራል። በደንቆሮዎች ስብስብ፡ በመሃይማን ጉባዔ፡ እውቀት በነጠፈችባቸው፡ ማስተዋል በራቃቸው፡ ፍጹም ደካማ በሆኑ ሰዎች እጅ ላይ የወደቀችውን ሀገር ”በመርህ ያቆምናት” ሲል አጠገቡ ብኖር መቼም በአንደበት የሚገለጽ መልስ አይኖረኝም። ጆሮ ግንዱን በጥፊ ከማላጋት ውጪ። ሰውዬው ሲበዛ ደፋር ነው። የመሃይም ደፋር። መርሳ ላይ 13 ኢትዮጵያውያን በተገደሉበት ዕለት፡ ትኩስ ሀዘን ውስጣችንን እየበላው፡ በመሳሪያ ጉልበት አፍኖ የሚመራትን ሀገር ”በመርህ” እያለ ሲያላዝን እንደመስማት የሚያም ምንም ነገር የለም። ለማንኛውም ምሱን ቀምሶ ተባሯል።

ወደ ተነሳሁበት ነጥቤ ልግባ። ህወሀት በብአዴን ውስጥ ከተከላቸዎች ሙጃና አረሞች አንዱ ካሳ ተክለብርሃን ነው። እሱና መሰሎቹ ብአዴን ውስጥ ተሰግስገው የአማራው ህዝብ በህወሀት የባርነት ቀንበር ውስጥ እንዲቆይ እስከመቃብራቸው ድረስ ቃል ገብተው እየሰሩ ነው። እነዚህ አገአልጋዮችና በጎ ፈቃደኛ ባሪያዎች ዋናው ተልዕኳቸው የህወሀትን ህልውና ማስጠበቅ ነው። ሌላው ተግባራቸው ትርፍ ነው። በአለቆቻቸው የሚመዘኑት፡ ሹመትና ስልጣን የሚደረብላቸው የህወሀትን ጥቅም ለማስጠበቅ የሄዱበት ርቀት ተለክቶና ተሰልቶ ነው። እነዚህ ሰዎች በሆድና ህሊና መሀል ልዩነቱን አያውቁም። ሲበዛ ፈሪዎች ናቸው። አደርባይነት ውስጣቸው ቤት ሰርቷል። ህወሀት ከሳቀች የሚስቁ፡ ካዘነች ብሶባቸው ለቅሶ የሚቀመጡ፡ የራሳችን የሚሉት የሌላቸው፡ እንደሰው ተፈጥረው፡ ባሪያ ሆነው አድገው፡ በአሽከርነት ጎልምሰው፡ በሎሌነት አርጅተው ሰው መሆን አቅቶአቸው ወደ መቃብራቸው የሚያመሩ፡ የትውልድ ማፈሪያ፡ የሀገር ሸክም ናቸው። ከእነዚህ አንዱ የሆነው ካሳ ነው እንግዲህ የአትላንቲክን ውቅያኖስ ተሻግሮ መጥቶ ”በመርህ ያቆምናት ሀገር” የሚለን።

ህወሀት አሽከሮቿን አዝምታለች። ስብሰባ አቋርጠው እሳት እንዲያጠፉላት በየቦታው አሰማርታለች። የወሎው ነገር አላማራትም። የእንጀራ ገመዷ ሊበጠስ ነው። ከመሃል ሀገር ጋር ያለው ግንኙነት በሰማይ ካልሆነ በየብስ የሚቻል ከማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱ አይቀርም። የወሎው መስመር ለትግራይ የህይወትና ሞት ጉዳይ ነው። ቀለብ የሚጓጓዝበት፡ ሸቀጥ የሚመላለስበት፡ ትግራይን ቀጥ አድርጎ የያዘው መስመር ነው። የህይወት መስመር። ከየትኛውም አከባቢ በላይ የወሎው ተቃውሞ ለህወሀት አደገኛ እንደሆነ ይታወቃል። በአንድ ሳምንት ተቃውሞ በተፈጠረ የመንገድ መዘጋት ትግራይ ውስጥ የተፈጠረውን ጭንቀት ሰምተናል። የዋጋ መጨመር፡ የምርቶች ከገበያ መጥፋት ተከስቶ ተጋሩዎች በስጋትና ፍርሃት ተውጠው እንደከረሙ የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል። ህወሀቶች የአፋርን መስመር በአማራጭነት ለመጠቀም እያሰቡ ነው።

በግፍ ገንዘብ የተቋቋመው የሰላም ባስ ድርጅት የወሎውን መስመር ዘግቶ በአፋር በኩል ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ተጨማሪ መንገድ መጓዝ ግድ ሆኖበታል። ተሳፋሪዎች ከ500 ብር በላይ ተጨማሪ እንዲከፍሉ ተገደዋል። አፋሮች እጃቸውን እያሟሹ ነው። እኛ ጋ ያለው ስቃይና በደል ቢብስ እንጂ የሚያንስ አይደለም ያሉት የሱልጣን ዓሊሚራህ ልጆች እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ከወዲሁ እያስጠነቀቁ ናቸው። ነገሮች እየከፉ መምጣታቸው አይቀርም። ወሎ ከተነሳ አይመለስም የሚለው ብሂል መሬት ረግጧል። ወልዲያ ጀምሮ፡ ቆቦን አዳርሶ፡ ከመርሳ የገባው እምቢተኝነት ደሴን ኮምቦልቻን ሀይቅን ዳር ዳር እያለ ነው። ህወሀቶች ብርክ ይዟቸዋል። ወሎ አምርሮባቸዋል። የየብሱ ነገር እያከተመ። የሰማዩን ይሞክሩ ይሆን?

ለህወሀት መጪው ጊዜ አስፈሪ ነው። ወሎ የተነሳው ተቃውሞ የመቃብር ጉዞውን እንደሚያፋጥነው ተረድቶታል። ሞቱን በጣም ቅርብ አድርጎበታል። እናም አሽከሮቹን አሰበ። ባሪያዎቹን ጠራ። ብአዴኖችን። እሳቱን እንዲያጠፉለት ሲል የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባቸው እንዲያቋርጡ አድርጓቸዋል። ከዚህ በላይ የሚያሳስበው ምንም ነገር የለም። ለጉባዔው ሌላ ጊዜ ይደረስበታል። ወሎን ዝም ማሰኘት፡ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ከዚህ የሚበልጥ አጀንዳ ለጊዜው የለም። ብአዴኖች ጉዛቸውን ጠቅልለው ወደየዞኑ ተሰማርተዋል። የህወሀትን ነፍስ ሊያድኑ። የአማራውን ህዝብ ስቃይ ሊያራዝሙ።

እንግዲህ ይለይለታል። ከዚህ በኋላ የብአዴን ሰዎችን ልመናም ይሁን ሽንገላ የሚሰማ ጆሮ የለም። እነዚህ ሰዎች ስለአማራ ብለው ስብሰባቸውን አላቋረጡም። ስለአማራው ብለው አልተሯሯጡም። አማራው ከቤንሻንጉል፡ ጉራፈርዳ፡ ከየቦታው ሲፈቀልና ሲገደል እንኳን ስብሰባቸውን ሊያቋርጡ፡ ለሀዘኔታ የምትሆን አንዲትም ቃል አልወጣቻቸውም። ባለፉት 27 ዓመታት የአማራው ህዝብ በህወሀቶች የበትቻኝነት ስሜት በፈጠረው ቂም በቀል ሲቀጠቀጥ ዱላ ሲያቀብሉ የነበሩት እነዚህ የብአዴን አመራሮች ናቸው። የአማራው ህዝብ ክፉ ጠላት እንጂ ወዳጅ አይደሉም። አማራው እነዚህ የትውልድ ኩሶችን ሊገላገላቸው ይገባል። ጀርባው ላይ እንደአልቅት ተጣብቀው፡ ለህወሀት የባርነት አገዛዝ መንገድ የሚጠርጉትን የብ አዴን ጉዶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊፋታቸው ጊዜው አሁን ነው።

አዎን! የህወሀትን የእሳት አደጋ ብርጌድ ማሳፈር ይገባል። የተሰማራውን የነፍስ አድን ቡድን አንገት አስደፍቶ መመለስ ግድ ይላል። ስብሰባቸውን መታደም፡ በግፍ በተገደሉት ላይ መሳለቅ ነው። ከብአዴኖች ጋር በአንድ አዳራሽ በአንድ ጉባዔ መቀመጥ፡ የእነዚያን መስዋዕትነት ማራከስ ነው። የአማራው ህዝብ አሳፍሮ ሊመልሳቸው ይገባል። የህወሀት አለቆቹን ለማስደስት የአማራውን ህዝብ በአደባባይ የዘለፈው አቶ አለምነው መኮንን ከቆቦ እጅና እግሩን ይዞ እንዳይወጣ ማድረግ ከሞራል አንጻር የሚያስጠይቅ አይደለም። ሌሎችንም እንደዚያው።

Filed in: Amharic