>

ኮካ በያይነቱ! (መስከረም አበራ)

ኮካ ፀባዩ ተመሳሳይ ቢሆንም አይነቱ ብዙ ነው- ዘር ከልጓም የሳበው፣ ሆድ ከጭንቅላት የሳበው እና ሁለቱም የሳበው፡፡ ዘር ከልጓም የሳበው ህወሃታዊ ካድሬዎችን ሲሆን ከዛ ውጭ ያለው የእህት(አጋር) ድርጅት ኮካ ደግሞ ሆድ/ስልጣን ከጭንቅላት የሳበው ቀላማጅ ሎሌ ነው፡፡ ሁለተኛው አይነት ካድሬ የበለጠ የሚያበላ ከተገኘ ህወሃትን ሊሸጥ አያስማማም ማለት አይቻልም፡፡ ዘር ከልጓም የሳበው ግን ኮካነቱ ከደም ስሩ ጋር አብሮ የሚዞር፣ ህወሃትን ከሚከዳ ምላሱ ከትናጋው ብትጣበቅ የሚመርጥ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ኮካ ድሬዳዋ ሊወለድ ይችላልነገር ግን ዘር ከልጓም ስቦት ላዕላይ አዲያቦ ከተወለደው እኩል የ “ውድብ” ህወሃት ነገር ይወዘውዘዋል!፣ነፃ ጋዜጠኛ ነኝ ሲል የኖረ ሊሆንል ይችላል፣በተቃውሞው ጎራ ተሰልፎ ዘጥ ዘጥ ሲል አይተነው የምናውቅ ሊሆን ይችላል ፣ከህወሃት ተሰንጥቄ ወጣሁ ብሎ አትሮኑስ የማይበቃው ዝባዝንኬ ፅፎ ሊያስነብብ ይችላል፡፡ ግን ግን ውድብ ህወሃት ያዳለጣት የመሰለው ዕለት ምድር ይጠበዋል፣ሳያስበው ክንብንቡን ያወልቃል፣ፍርድ ሲገመድል ትዝብት ላይ መውደቁን ያስብ ዘንድ አቅል ከወዴት ይመጣል? ኮካነት በውልደት ሲገኝ ካድሬ ለመሆን ፎርም መሙላት ላያስፈልግ ይችላል፣ የአባልነት ክፍያም መታወቂያም አያስፈልግም -ሁሉ የተፃፈው በልብ ፅላት ላይ ነው!

ነፃ ጋዜጠኛ እንደሆነ ሲወሻክት የኖረው ዳንኤል ብርሃኔ (ትውልደ ኮካ) እና የዋዜማው አርጋው አሽኔ (ጎበዝ ተንታኝ) ትናንት በቪኦኤ ቀርበው ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ የተራራቀውን የግንዛቤ ልዩነታቸውን ያስተጋባ ክርክር አድርገዋል፡፡ ዳንኤል ብዙ ቢያወራም አንድ የገባኝ ነገር ሳይኖር ብዙ ደቂቃዎች አለፉ፡፡ አወያዩ አሉላ ከሚያነሳው የክርክር ነጥብም ሆነ አርጋው ከሚያመጣው ጥሩ ትንታኔ ጋር በምንም የማይገናኝ ዘባሪኮም ይቀበጣጥራል – አይተ ዳንኤል፡፡እውነት የሌለው ሰው ትርጉም ያለው አረፍተነገር መስራት እንኳን እንደማይችል አስረጅ ነው የአይተ ዳንኤል ቅብጠራ! አርጋውን ማዳመጥ ስለፈለኩ ብቻ ዳንኤልን ማዳመጥ ነበረብኝ፤ አመት ያወራ የሚመስለኝ ዳኤል በመሃል አንድ አስደንጋጭ ነገር ተናገረ “የኢትዮጵያ ህዝብ ፖለቲካ አይጨንቀውም ቤቱን ካልተቀማ በቀር” ብሎ ቁጭ አለ! ምን ማለቱ ነው ???????አይምሮ የጎደለው መሰለኝ! አሁን ከኢትዮጵያ ዳር እስከዳር “ዳውን ዳውን ወያኔ” እያለ ያለው የሳኦቶሜ ህዝብ ኢትዮጵያውስጥ ጎራ ብሎነው ተብሎ ነው እንዴ በትውልደ ኮካዎች የሚታመነው? ወይስ ይሄ ሁሉ ህዝብ ቤቱን ተቀምቶ ነው በአፈሙዝ ላንቃ ሥር ቆሞ አምባገነንን እየተጋፈጠ ያለው ?!

ሆድ/ስልጣን ከጭንቅላት ስቦት አሽከርነትን ጌጥ አስመስሎ የሚያሳየው ኮካ በማጠራቀም የማይታማው ደግሞ ዝነኛው ብዓዴን ነው፡፡ አለምነው መኮንን፣ይናገር ደሴ፣ተፈራ ደርበው፣ንጉሱ ጥላሁን፣ገዱ አንዳርጋቸውን የመሰሉ ወዶገቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከነዚህ አንዱ ንጉሱ ጥላሁን በትናንቱ የሁለት ሰዓት ዜና ብቅ ብሎ “በወልዲያ እና አጎራባች ከተሞች የሚደረገው ድርጊት የአካባቢውን እውነታ አይወክልም” ሲል እውነታውን የሚወክለው የእሱ ወዶገባነት፣ዛሬ ሌላ ነገ ሌላ የመዘባጠር ወናፍነት፣ እውነትን ሸምጥጦ ክዶ እንደዘርዛራ ወንፊት ሃሰት ማፍሰስ ነው ማለት ነው! እውነት ለመናገር እውነታውን የማይወክለው የውርጃው ብአዴን ውሽከታ እንጅ የህዝብ ብሶት አይደለም፡፡ በጌቶቹ ዘንድ ከዓለምነው መኮንን በልጦ ለመገኘት እንደዝንጀሮ እግር እየለካ ያለው ንጉሱ ጥላሁን የሚባል ጉድ ተኩሰው ከሚገድሉት እኩል ሰውን እያቆሰለ ያለ መርዘኛ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እጅግ በሚያበግነው የትናንቱ ንግግሩ የአማራ ህዝብ በዘር ብቻ ትግሬዎችን እያጠቃ እንደሆነ በገደምዳሜ ተናገረ፡፡ይህን ሲል በቆመለት ህዝብ የፖለቲካ ኪሳራ የአሽከርነቱን ልቀት ለጌቶቹ ማስመዝገቡን እንጅ የጎሳ ጭትን ዘር መበተኑን የካድሬ ግንዛቤው የሚነግረው አይመስለኝም፡፡ ለመሆኑ በመላው ወሎ የሚኖር ትግሬ ስንት ነዉና ስንቱ በትግሬነቱ ብቻ ተጠቃና ነው ይህን የሚያወራው? እንዴት ያለ ራስን መናቅ ነው እንዲህ ባለው የአሽከርነት ትቢያ የሚያንፏቅቅ????!!!!!

Filed in: Amharic