>
9:49 am - Sunday January 29, 2023

በሕጉ መሰረት “ህወሓት አሸባሪ ነው!” (ስዩም ተሾመ)

“ህወሓት እና ፍርሃት፡ ከቀበሌ እስከ መቀሌ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ፣ አህአዴግ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ያጋጠመው ሽንፈትና በተለይ ደግሞ በህወሓት ልሂቃን ዘንድ ያስከተለው ከፍተኛ ድንጋጤና ፍርሃት ፍፁም ጨቋኝና ጨካኝ የሆነ መንግስት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን በዝርዝር ተመልክተናል። በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አማካኝነት በኢትዮጲያ ሕዝብ ዘንድ ያለውን ድጋፍና ተቀባይነት ለማጠናከር ያደረገው ሙከራ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ህወሓት/ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ለመቆየት ያለው ብቸኛ አማራጭ የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ያላቸውን የፖለቲካ ኃይሎች በማስወገድ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማድረግ ነው።
ተቋማትን ማፍረስ

የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ ህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጣኑን ለማስረከብ ፍቃደኛ አልነበረም። ሆኖም ግን፣ የፖለቲካ ቡድኑ በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ከሌለው ደግሞ ሀገርና ሕዝብ ማስተዳደር አይችልም። ምክንያቱም እንደ “Jose Ortega y Gassett” አገላለፅ፣ “there can be no rule in opposition to public opinion.”” በዚህ መሰረት፣ ህወሓት/ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ለመቆየት ያለው ብቸኛ አማራጭ የብዙሃኑን አመለካከት/አስተያየት (public opinion) መቆጣጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙበትንመ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ ደግሞ ተቀባይነት ያጣበትን የዴሞክራሲ መዋቅር ማፍረስ ይኖርበታል።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሦስት ምሶሶዎች ላይ የተዋቀረ ነው። እነሱም፣ አንደኛ፡-ጠንካራ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሁለተኛ፡- ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ፣ ሦስተኛ፡- ሲቪል ማህበራት ናቸው። የህወሓት/ኢህአዴግ ሕልውና እንዲረጋገጥ እነዚህን የዴሞክራሲ ተቋማት በተለያየ መንገድ ማገድ፥ ማሽመድመድ፥ ማፍረስና ማስወገድ ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ፣ የዴሞክራሲ መዋቅሩን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት የታየው ፖለቲካዊ ንቅናቄ ተመልሶ እንዳያንሰራራ መደረግ አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ህወሓት/ኢህአዴግ በስልጣን ላይ መቆየት አይችልም።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ ህወሓት/ኢህአዴግ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ለዚህ ሁሉ አጣብቂኝ የዳረጉትን የቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ አመራሮችን ማሰርና ከፓርቲ ውስጥ ሰርጎ በመግባት ጥምረቱን ማፍረስ ነው። በተመሳሳይ መንገድ በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ሰርጎ-በመግባት፣ ብቃት ያላቸውን የፓርቲ አባላትና አመራሮችን በመደለልና በማስኮብለል፣ የተቀሩትን ደግሞ ለእስር፥ ስቃይና ስደት በመዳረግ ጠንካራ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ አጥፍቷል።

ሁለተኛ በፀረ-ሽብር ሕጉን እና የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅን በማውጣት በአራት አመታት ግዜ ውስጥ ብቻ 60 ጋዜጠኞችን ለስደት፣ 19 ጋዜጠኞችን ለእስር በመዳረግ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን አጥፍቷል። ሦስተኛ ላይ የተጠቀሱትን ሲቪል ማህበራት ደግሞ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሕብረት መመሪያን በማውጣት አጥፍቷቸዋል። ከሕግ አዋጆች በተጨማሪ፣ የኢህአዴግ መንግስት በመረጃና ግንኙነት ዘርፉ ላይ ጥብቅ ስለላና ክትትል ያደርጋል።

የዓለም የቴሌኮምዩኒኬሽን ማህበር (ITU) በ2015 የፈረንጆች አመት ባወጣው ሪፖርት መሰረት ኢትዮጲያ በመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT) መሰረተ ልማት ከ167 የዓለም ሀገራት 165ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ሆኖም ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎትን በማስተጓጎል፣ ይዘቶቹን በመቆጣጠርና የተጠቃሚዎቹን የግለሰብ መብት በመጣስ 82/100 ነጥብ አስመዝግቧል።

ፍፁም አምባገነንነት

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ ባለፉት አስር አመታት ህወሓት/ኢህአዴግ ዜጎችን በፀረ-ሽብር አዋጁ የሚያሸብረው፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን፥ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾችን፥ የሲቭልና ሙያ ማህበራትን፥… በአጠቃላይ የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ለእስር፥ ስደት፥ እንግልት፥ ለአካል ጉዳትና ሞት የዳረገበት መሰረታዊ ምክንያት የብዙሃኑን አመለካከትና አስተያየት በብቸኝነት በመቆጣጠር በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ነው። ይህ ጨቋኝ ስርዓት የፖለቲካ ስልጣኑን የሚቆጣጠርበት ስልት እንደሆነ “Jose Ortega y Gassett” ይገልፃል፡-

“Rule is the normal exercise of authority, and is always based on public opinion, to-day as a thousand years ago, amongst the English as amongst the bushmen. Never has anyone ruled on this earth by basing his rule essentially on any other thing than public opinion. The Revolt of the Masses, Ch. XIV: Who Rules the World?, Page 73.

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ የ1997ቱ ምርጫ በህወሓት የፖለቲካ ልሂቃን ላይ የፈጠረው ድንጋጤና ፍርሃት የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስትን ጨቋኝና አምባገነን እንዲሆን አድርጎታል። ነገር ግን፣ ከጨቋኝነትና አምባገነንነት በተጨማሪ፣ ፍርሃት በፖለቲካ ልሂቃኑ ላይ የበታችነት (inferiority) ስሜት ይፈጥራል።

ምክንያቱም የ1997ቱ ምርጫ በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተው ፖለቲካዊ ስርዓት በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው አረጋግጧል። በዚህ ምክንያት የህወሓት ልሂቃን በኢትዮጲያ ሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት የሌላቸው እና በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ የረባ ተፅዕኖ መፍጠር የማይችሉ ደካሞች መሆናቸውን አስገንዝቧቸዋል። በዚህ መሰረት፣ የፖለቲካ ፍርሃትና ደካማነት ከስልጣን የበላይነት ጥማት ጋር አንድና ተመሳሳይ እንደሆነ “Hanna Arendt” እንደሚከተለው ትገልፃለች፡-

“Out of the conviction of one’s own impotence and the fear of the power of all others comes the will to dominate, which is the will of the tyrant. Just as virtue is love of the equality of power, so fear is actually the will to, or, in its perverted form, lust for, power. Politically speaking, there is no other will to power but the will to dominate.” On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding: 329-360

አምባገነናዊ ሽብር

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የፖለቲካ ሽንፈትና ደካማነት የፖለቲካ ስልጣን የበላይነት ጥማት እንደሚያስከትል ተገልጿል። በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የፖለቲካ ቡድን የስልጣን የበላይነቱን ለማረጋገጥ የዴሞክራሲ ተቋማትን ከማገድ፥ ማሽመድመድ፥ ማፍረስና ማስወገድ በተጨማሪ በሕብረተሰቡ ዘንድ ምንም ዓይነት የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት መኖር የለበትም።

ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ የፍርሃት ድባብ ማስፈን፣ ማንኛውም ዓይነት የተለየ የፖለቲካ ሃሳብና አመለካከትን በኃይል ማፈንና ማዳፈን፣ የሕግ-የበላይነትና ተጠያቂነትን በማስቀረት ዜጎች የህግ ዋስትና እንዲያጡ በማድረግ በዜጎች ላይ ፍርሃትና ሽብር መፍጠር ያስፈልጋል። ህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ሽንፈትና ደካማነቱን ለማስወገድ እና የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ከፈጠራቸው የሽብር ዘዴዎች ውስጥ ዋናው “የፀረ ሽብር ሕግ” ነው።

በእርግጥ የፀረ-ሽብር ሕጉ ዜጎችን በነፃነት የሚያስቡበት፥ የሚናገሩበት፥ የሚመካከሩበት፥ የሚመክሩበት፥ የሚፅፉበት፥ የሚንቀሳቀሱበት፥ የሚሰበሰቡበት፥ የሚደራጁበት፥ … ቦታ አሳጥቷቸዋል። በዚህ መሰረት፣ ዜጎችን ያለ ምህረት እርስ-በእርሳቸው የሚያጣብቅ፥ የሚያጣብብ፥ የሚያስጨንቅ፣ መንቀሳቀሻ፥ ማሰቢያ፥ መናገሪያ፥ መፃፊያ፥ መሰብሰቢያ፥ ማላወሻ በማሳጣት ነፃነትን ከነጭራሹ የሚያጠፋ ነው።

የአንድ ሀገር የፀጥታና ደህንነት ስራ መሰረታዊ ዓላማ የዜጎችን ደህንነትና ነፃነት ማረጋገጥ ነው። ሆኖም ግን፣ “በፀረ-ሽብር” ስም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ በራሱ “አሸባሪነት” ነው። ቀደም ሲል በተጠቀሰው የ“Hanna Arendt” ጥናታዊ ፅሁፍ መሰረት፣ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ሕዝብን ማሸበር “አምባገነናዊ ሽብር” (Totalitarian terror) ይባላል። በፀረ-ሽብር ሕጉ መሰረት፣ ባለፉት አስር አመታት ህወሓት/ኢህአዴግ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፥ ሕገ-መንግስታዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማት፣ እንዲሁም በዜጎች ሕይወት፥ ንብረት፥ ሰላምና ደህንነት ላይ ያደረሰው ጉዳት በአብዛኛው በፀረ-ሽብር ሕጉ ውስጥ “Terrorist Acts” ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ የሚመደቡ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ የፀረ-ሽብር ሕጉን ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ፣ በሕጉ ውስጥ የተዘረዘሩትን የሽብር ተግባራት በመፈፀሙ ረገድ በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ የሆነው ህወሓት “አሸባሪ” (Terrorist) ነው። ከዚህ በታች በቀረበው የፀረ-ሽብር አንቀፅ መሰረት “ህወሓት አሸባሪ ነው!”

  1. 3. Terrorist Acts 
  2. Whosoever or a group intending to advance a political, religious or ideological cause by coercing the government, intimidating the public or section of the public, or destabilizing or destroying the fundamental political, constitutional or, economic or social institutions of the country: 
  3. causes a person’s death or serious bodily injury; 
  4. creates serious risk to the safety or health of the public or section of the public; 
  5.  commits kidnapping or hostage taking; 
  6. causes serious damage to property; 
  7. causes damage to natural resource, environment, historical or cultural heritages; 
  8. endangers, seizes or puts under control, causes serious interference or disruption of any public service; or 
  9. threatens to commit any of the acts stipulated under sub-articles (1) to (6) of this Article;

ማጣቀሻዎች

Filed in: Amharic