>

"እኔ ስታገል እንጅ ስነግድ አልኖርኩም" ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (በጌታቸው ሽፈራው)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  ከመታሰሩ በፊት ወደ አሜሪካ ሀገር እንዲሄድ ብዙ ግፊት ደርሶበት ነበር። ለበርካታ ጊዜ ተለምኗል።  ያኔ በተደጋጋሚ ወደ አሜሪካ እንዲሄድ “መንገድ ሲሰጠው” ልጅም ትዳርም አልነበረውም። ቪዛ ሊሰጠው የነበረውም የአሜሪካ ኤምባሲ ነው።

ተመስገን ከእስር ከተፈታ በኋላ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት የመጣውን የጀርባ ህመም ለመታከም፣ እንዲሁም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያዘጋጁለት ፕሮግራም ላይ ለመታደም የአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር።

ተመስገን ደሳለኝ ወደ ውጭ ለመሄድ ስለማይፈልግ ፓስፖርቱን እንኳ ያወጣው የሚያከብራቸው ኢትዮጵያውያን አማላጅ ተልከውበት ጭምር ነው። ሆኖም የአሜሪካ ኤምባሲ “ልጅና ትዳር የለህም” በሚል ሰበብ ቪዛ ከልክሎታል።

ተመስገን ወደ አሜሪካ እንዲሄድ በተደጋጋሚ ሲለመን መስፈርት ያልነበር “ልጅና ትዳር” አሁን ደርሶ መስፈርት እና ሰበብ መሆኑ አሳማኝ አይደለም። ያኔ ከእነ ቤተሰቡ ጭምር ወደ አሜሪካ እንዲሄድ ሲለመን ቪዛ ሊሰጠው የነበረው የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ዛሬ  ብቻውን ያውም ለደርሶ መልስ “ልጅና ትዳር የለህም” ማለቱ  እንቆቅልሽ ነው!

መስፈርት ተብሎ ከቀረበው ልጅና ትዳር ባሻገር የአሜሪካ ኤምባሲ ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “ምን ንብረት አለህ?” የሚል  ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም “እኔ ስታገል እንጅ ስነግድ አልኖርኩም” የሚል መልስ መስጠቱ ታውቋል።

Filed in: Amharic