>
5:14 pm - Wednesday April 20, 6259

የሕዝብ ትግልን የወነጀለው የግንቦት 7 መግለጫ (ጌታቸው ሺፈራው)

 

ግንቦት 7 ከትህዴን ጋር አወጣሁት ባለው መግለጫ ባለፉት 3 አመት የተደረጉትን የሕዝብ እንቅስቃሴዎች በአንድ ዐረፍተ ነገር አፈር ድሜ አብልቷል። በቀል የተፈፀመባቸው ናቸው ሲልም ወንጅሏል። በመግለጫው የትህነግ/ህወሓት አባላት ያልሆኑት እርምጃ እንደተወሰደባቸው ከመግለፁም ባሻገር፣ “ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተነሱ የጸረ ወያኔ እንቅስቃሴዎች የበቀል እርምጃ እየተወሰደባቸው ካሉ የህወሃት ካድሬዎች በተጨማሪ ከህወሃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ያልነበራቸው ሰዎችም የጥቃቱ ሰልባ እንደሆኑ መስማት እየተለመደ መጥቶአል።” ሲል “የበቀል እርምጃ ተወስዷል” ሲል የሕዝብ ትግልን ያልተገባ ትርጉም ሰጥቷል።

ግንቦት 7 በሰሜን፣ ይሁን በደቡብ የተነሳ እንቅስቃሴ ላይ እጁ እንዳለበት ሲገልፅ ቆይቷል። በ2006 ዓም የቴፒ ወጣቶች እንቅስቃሴ ላይ እጄ አለበት ብሎ ነበር። ቂሊንጦ ያገኘሁት የቴፒ ወጣቶች መሪ እንዳጫወተኝ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ሊኖረው ቀርቶ ስለ ግንቦት 7 የሚያውቀው እስር ቤት ከገባ በኋላ ነው። ግንቦት 7 የሌለባቸውን በርካታ እንቅስቃሴዎች የእኔ ናቸው እንደሚል የተረዳሁት ከዚህ በኋላ ነው። ሆኖም ሕዝብ የስነ ልቦና ብርታት እንዲኖረው፣ እንቅስቃሴውን እውቅና የሰጠው አካል እንዳለ እንዲያውቅ ከሚል ቀናኢ የፕሮፖጋንዳ ይሆናል በሚል በርካቶች ዝምታን ሲመርጡ ቆይተዋል። ይሁንና ግንቦት 7 የእኔ እጅ አለበት እያለ መግለጫ ሲያወጣበት የነበር የሕዝብ ትግል ከገዥዎቹ እኩል “በማንነት ላይ የተወሰደ በቀል” አድርጎ መግለጫ አውጥቷል። ለዚህ ፍረጃውም የገዥዎቹ ተከፋዮች ሳይቀሩ “ደግ አደረክ” ብለውታል።

ግራ የሚያጋባው መግለጫ

ሁለቱ ድርጅቶች የሰጡት መግለጫ “በትግራይ ሥም እየማለና እየተገዘተ ለመንግሥት በትረ ሥልጣን የበቃው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ላለፉት 26 አመታት በአገራችንና በህዝባችን ላይ ያልፈጸመው በደል የለም።” የሚል መንደርደሪያ አስቀምጠዋል። እንደ ድርጅት መሪዎቻቸው ተማክረው፣ መክረው ዘክረው ትህነግ “በትግራይ ስም እየማለ” በፈፀመው በደል ባለፉት 3 አመታት እነሱ አለንበት እያሉም ቢሆን የተበደለ፣ ፊቱ ላይ የንፁሃንም ደም ያየ ሕዝብ ያለ መሪ ድርጅት (በግብታዊነት) ባደረገው ትግል አጣርቶ፣ መርምሮ……” እርምጃ ሊወስድ ይችል ነበር” ብሎ ማሰብ ከመቼው የባሰ ትዝብት ውስጥ የሚከት ነው።

በመጀመርያ ደረጃ ባለፉት 3 አመታት በተደረጉት የሕዝብ ትግሎች “ተገደለ፣ ቆሰለ፣ ተቃጠለ” ብለው በቀዳሚነት መረጃ ሲያሰራጩ የነበሩት በውጭ የሚገኙት የንቅናቄው አባላት እና ኤርትራ የሚገኘው ሬድዮ ጣቢያው ናቸው። አባላቱና ሬድዮ ጣቢያው በ”ሰበር” ዜና የሚያሰራጩዋቸው ዜናዎች ባሻገር “ግፋ በለው” አይነት መልዕክት ሲያስተላልፉ እንደነበር የሚካድ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ “አለሁበት” የሚል መግለጫ ሲጨምር፣ ጉዳዩ ሲበርድ በርካቶች በግንቦት 7 ስም ተከሰዋል። ግንቦት 7 አለሁበት አለም አላለም ገዥዎቹ የፈለጉትን በስሙ ሊከሱት ይችላሉ። ሆኖም እነዚህን እንቅስቃሴዎች ሳይኖር አለሁ እያለ በመግለጫ ሳይቀር ሲያበረታታ የነበር ድርጅት “በቀል ተፈፅሟል” የሚል መግለጫው በገዥዎቹ የሚቀለቡት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንኳን ደፍተው ያልፈፀሙት ሀጥያት ነው። በእጅጉ የሚያሳዝነው ግንቦት 7 “በቀል ሲወሰድ መስማት የተለመደ ነው” ሲል “በቀል ተወሰደ” የሚለውን ከሕዝብ ሊሰማው እንደማይችል ግልፅ ነው። ይህን የሕዝብ ትግል የሚያጠለሽ ወሬ ሊሰማ የሚችለው “ወያኔ” ብሎ ከሚጠራው እና እሱን ሲያብጠለጥሉት ከሚውሉት የስርዓቱ ደጋፊ ሚዲያዎች ብቻ ነው። በዚህም ግንቦት ሰባት ወያኔ የሚለው አካል “በትግራይ ስም እየማለ” ስቃይ ከሚፈፅምበት ሕዝብ ይልቅ “ወያኔን” እና አፈቀላጤዎችን አምኗል ማለት ነው። ለጊዜውም በዚህ መግለጫውም መግባባት የቻለው ከእነዚህ አካላት ጋር ነው።

በሕዝባዊ እንቅስቃሴው “እርምጃ የተወሰደበት”

ግንቦት 7 እና ትህዴን ባወጡት መግለጫ የህወሓት አባላት ያልሆኑ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ሲሉ ሰማነው ያሉትን አስፍረዋል። ይሁንና በመግለጫው ከትግራይ ውጭ የሚኖረው የትግይራ ህዝብ በግድም ሆነ በውድ የትህነግ/ ህወሓት አባል መሆኑን ያትታል። ከዚህም ባሻገር ይህ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ትህነግ/ህወሓት ለፈፀመው በደል ሁሉ “መረጃ አቀባይ፤ ጉዳይ አስፈጻሚና ያካባቢው የሥርዓቱ የድጋፍ ኃይል አድርጎ ተጠቅሞበታል።” ይላል። ከትግራይ ውጭ ያለውን የትግራይ ተወላጅ በአንድ በሌላም መንገድ የትህነግ/ህወሓት አባል፣ጉዳይ አስፈፃሚ ነው ሲል የደመደመው፣ “የህወሓት አባላት ያልሆኑት በቀል ተወስዶባቸዋል” የሚል ሌላ መደምደሚያ ላይ መድረሱ መግለጫውን የተምታታ እና ግራ አጋቢ አድርጎታል።

“ባለፉት 3 አመታት በተካሄዱት ፀረ ወያኔ እንቅስቃሴዎች የሕወሓት አባል ያልሆኑትም የበቀል እርምጃ እንደተወሰደባቸው ይሰማል” ብሎ የሕዝብ ትግልን የፈረጀው መግለጫ “የትግራይ ሕዝብና ህወሓት የተለያዩ ናቸው” ሲል በማስረጃነት ያቀረበው የሞላ አስግዶሙን “የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ትህዴን” ነው። በመግለጫው ደግሞ “በቀል ተፈፅሟል” የተባለው ኤርትራ ያለ ድርጅት ላይ ሳይሆን በአማራና በኦሮሚያ የሚኖሩ የ”ትግራይ ተወላጆች” ላይ እንደሆነ ግልፅ ነው። ግንቦት 7 ለዚህ በአስረጅነት የሚያቀርብልን ኤርትራ ውስጥ ያለውን ድርጅት አባላት ነው።

በዚህ አጋጣሚ “የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ” ስለሚባለው የእነ ሞላ አስግዶም ድርጅት አንዳንድ መረጃዎችን መጥቀስ ተገቢ ነው። ይህ ድርጅት ስሙ የ”ትግራይ” ይሁን እንጅ አብዛኛዎቹ አባላቱ የአማራ እና ኦሮሞ ልጆች እንደሆኑ እስር ቤት የሚገኙት የግንቦት 7፣ የኦነግ፣ የትህዴን፣ እና የአዴኃን ታጋዮች ገልፀውልኛል። ከዚህም በተጨማሪ ከሞላ አስግዶም ጋር የገቡት ወደ ትውልድ ቦታቸው (አማራና ኦሮሚያ ክልል) መበተናቸው የሚታወቅ ነው። የአማራ እና ኦሮሞ ልጆች ወደዚህ ግንቦት 7 አብሬው እየሰራሁ ነው ወደሚለው ድርጅት የሚገቡት ወደውና ፈቅደው አይደለም። በበርሃው ለቀን ስራ የሚንከራተቱትን፣ ወልቃይት ውስጥ በእርሻ እና በወርቅ ቁፋሮ የተሰማሩትን የአማራ ወጣቶች እያፈነ እየወሰደ አባል እንደሚያደርግ የታወቀ ነው። ሌላው ቀርቶ የግንቦት 7 እና የአዴኃን ታጋዮችን እያፈነ በግድ የራሱ አባል እንደሚያደርግ ፀኃይ የሞቀው ሀቅ ነው። ግንቦት 7 እና አርበኞች ግንባር አንድ ከሆኑ በኋላ ይህ ጠለፋ እንዲቀር ምክር ቢሰጡም የእነ ሞላ ድርጅት የተቀመለው አይመስልም። በመሆኑም ትህዴን ውስጥ የሚታገሉ ወጣቶች የትግራይ ህዝብ የህወሓት አባል አይደለም ለሚል መከራከሪያ ብቁ ካለመሆኑም ባሻገር ሌላ ጉድ የሚጎትት ይሆናል።

እንደ አጠቃላይ መግለጫው የእነ ሞላ አስግዶምን ድርጅት፣ ወይም ሞላ አስግዶምን ያስጠለለውን “ወያኔን” ለማስደሰት ግልፅ ባይሆንም ኮሽ ባለ ቁጥር አለሁ የሚለውን ግንቦት 7 የህዝብን ትግል የወነጀለበት፣ ግንቦት 7ንም ከመቸውም ጊዜ በላይ ትዝብት ውስጥ የከተተ እንደሆነ ግልፅ ነው።

Filed in: Amharic