>
5:18 pm - Friday June 15, 7984

የግንቦት7 መሪዎች ከኢህአፓ አነሳስና ውድቀት ሊማሩ የሚችሉት ብዙ ትምህርት ያለ ይመስለኛል (ያሬድ ጥበቡ)

ሰሞኑን የአርበኞች ግንቦት 7 (አግ7) ድርጅታዊ መግለጫ ታላቅ አቧራ አስነስቶ መሰንበቱን ሁላችንም እናውቃለን ። በተለይ ራሳቸውን እንደ አማራ ብሄርተኛ የሚቆጥሩ ወገኖች የመረረ ተቃውሞ ሲያሰሙ ሰንብተዋል ። ይህም የድርጅቱ የአግ7 አመራር አባል የሆኑትን የአቶ ነዓምን ዘለቀን ተጨማሪ ማብራሪያ እስከማስገደድ ደርሷል።

በተጨማሪ ማብራሪያው ላይም አቶ ነዓምን ዘለቀ የሚከተለውን አስፍሯል ። “በአሁኑ ሰአት በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰቦችና ታጋዮች ሁሉ (በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የኣርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮችን ጨምሮ) የህወሓትን ሰላዮችና ገዳዮች ከስርአቱ ጋር ምንም ቁርኘት ከሌላቸው የትግራይ ተወላጆች ነጥሎ መመታት አስፈላጊና ፡ ህዝቡም በትግሉ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ነው በመግለጫው የተገለጸው” ይላል ። አንብቤም ጉዳዩ ከነከነኝ ። ለምን ማለት ደግ ነው።

በመጀመሪያ አርበኞች ግንቦት 7 ይህን መግለጫ ማውጣት የተገደደው በየማእዘኑ በሚነሱት የህዝብ ሰላማዊ ተቃውሞዎች የመንግስት ምላሽ ጥይት በመሆኑ፣ በዚህ ፍጅት የተናደዱ ወጣቶች በደመነፍስ “የወያኔ ተባባሪ ናቸው” በሚባሉ ላይ የሚወስዱት ግብታዊና አመፃዊ እርምጃ ነው አወዛጋቢ ሆኖ የተገኘው።  መግለጫው ራሱ “ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ሰዎች ከትግሬነታቸው ውጪ የተገኘባቸው በደል የለም” ብሎ እስካላስተባበለ ድረስ፣ የአቶ ነዓምን ተጨማሪ ጉዳዩን ይበልጥ ከማወሳሰብ ውጪ ለጥራቱ ሊረዳ አልቻለም።

አቶ ነዓምን እንደሚሉት “የህወሓትን ሰላዮችና ገዳዮች ከስርአቱ ጋር ምንም ቁርኘት ከሌላቸው የትግራይ ተወላጆች ነጥሎ መመታት አስፈላጊ” ከሆነ፣ ያልተደራጀና ግብታዊ የህዝብ ትግል እንዴት አድርጎ ከሥርአቱ ጋት ቁርኝት ያላቸውን ከሌላቸው መለየት እንደሚችል ወንፊቱን ማቅረብ ነበረባቸው ። ያንን ማድረግ አልፈቀዱም ወይም አልቻሉም፣ ደግሞም አይችሉምም። እንኳንስ እንዲህ ዓይነት የቃና ዘገሊላ በዓልን ለማክበር ወጥቶ ታቦት ያጀበ ወጣት በደረሰበት ግፈኛ ጭፍጨፋ ተናዶ በወሰደው የመልስ ምት የደረሰ የንብረት ውድመት ቀርቶ፣ የተደራጀ ትግል ባለበት ሁኔታ እንኳ ጠቅላላ አቅሙን በመከላከያና ደህንነተ  ላይ የሚያውል መንግስትን በዚህን መሰል የትግል ስልት መግጠም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ። የትዬለሌ የሆነ የድርጅት አቅም፣ ዲሲፕሊንና አመራር የነበረው ኢህአፓ እንኳ በከተሞች ጥንካሬ ካለው መንግስት ጋር ያደረገው የሞትና ሽረት ትግል ለሽንፈት የዳረገው ከመሆኑም ባሻገር ፣ ስንት ስህተቶችና መዝረክረኮች እንደነበሩት የምናውቀው ነው።  በስንት ጦር የተከበበውን መንግስቱን ሳይሆን፣ የአርቆ አሳቢውን የዶክተር ፍቅሬ መርእድን ህይወት ነው በአጭር የቀጠፈው። ለዚህ ዘመን ወጣቶች ትምህርት ሊሆን የሚችለውም፣ እስከ አፍንጫው ከታጠቀ ሥርአት ጋር፣ የርሱ ጥንካሬ ባለባቸው ከተሞች፣ የሥርአቱ ደጋፊዎች ናቸው የሚባሉትን በጠራራ ፀሃይ መግደል ወይም ንብረታቸውን ማቃጠል፣ የሥርአቱን እድሜ የሚቀጥል እርምጃ ብቻ እንጂ ነው። ደርጉ ከቀዩ ሽብር በኋላ ለ15 ዓመታት ሊገዛ የቻለው፣ የከተማው ሽብር የፈጠረለትን አመፅ ተገን በማድረግ ነው። ስለሆነም እንኳንስ ሰሞኑን በሰሜን ወሎ ከተሞች ያየናቸው የወጣቶች የደመነብስና ስሜታዊ እርምጃዎች ቀርቶ ፣ ኢህአፓን በመሰሉ እንደ ብረት የጠነከረ ዲሲፕሊን የነበራቸው እንቅስቃሴዎች እንኳ ለወጣት አባሎቻቸው የሰጧቸው “የነፃ እርምጃ” መብቶች የጋዜጠኛ የሸዋልዑል መንግስቱን ዓይነት ዜጎች መረሸንን ነው ያስከተለው ። እዚያ የተጨማለቀና አሸማቃቂ ታሪክ ውስጥ ዳግም መንቦጫረቅ የለብንም። የተወሰኑት የግንቦት 7 መሪዎችም በዚያ ታሪክ ውስጥ ያለፉ ስለነበሩ፣ ያንን ልምዳቸውን ዘወር ብለው ማየትና መመርመር ይገባቸዋል። የግንቦት7 መሪዎች ከኢህአፓ አነሳስና ውድቀት ሊማሩ የሚችሉት ብዙ ትምህርት ያለ ይመስለኛል።

ከላይ በግልፅ እንዳስቀመጥኩት ከአቶ ነአምን ተጨማሪ መግለጫ ውስጥ ያልተስማማኝን ተችቻለሁ። የሰሞኑን የሰሜን ወሎ ወጣቶችን ተጋድሎ በተመለከተ፣ ንብረት አወደማችሁ ብዬ ላወግዛቸው ፈቃደኛ አይደለሁም። ወንድሙ፣ ጓደኛው በአላሚ ተኳሽ ከጎኑ ሲወድቅ የተናደደ ወጣት ሄዶ የወርቅ ቤት ቢዘርፍ ወይም ቢያቃጥል ስሜቱ ይገባኛል፣ ይረዳኛልም። የተከፈለውንም መስዋእትነት አከብራለሁ ። ሆኖም በዚህ መንገድ ነፃነት ይገኛል ብዬ ለማመን እድሜዬም፣ ልምዴም፣ እውቀቴም አይፈቅዱልኝም። አስተማማኝና ዘላቂ ለውጥ የሚገኘው ከተራዘመ ሰላማዊ ህዝባዊ ትግ ል ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ትግል ሥርአቱን አወዛውዞ “ከጭንቅላቴ በስብሻለሁ” ባሰኘበት ወቅት፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች ውስጥ ህዝባዊ ትግሎቹን የሚደግፉ ሃይሎች በተበራከቱበት ወቅት፣ የግንቦት7ና የአቶ ነዓምን “የህወሓትን ሰላዮችና ገዳዮች ከስርአቱ ጋር ምንም ቁርኘት ከሌላቸው የትግራይ ተወላጆች ነጥሎ መመታት አስፈላጊ” ነው አስተሳሰብና እርምጃ፣ ወያኔ ከገባበት ማጥ ወጥቶ የበለጠ እንዲጠናከር የሚረዳው ይሆናል የሚል ፍርሃት አለኝ ። ወቅቱ በጣም ስሱ በመሆኑ፣ በተለይ ከፖለቲካ መሪዎች የበከጠ ስሱነት የሚጠየቅበት ነው። በእንዲህ ያለ ወቅት አመፅን የመጠቀም መብት ላልተደራጀ ህዝብ መስጠት ብዙ ሊያስከፍል ሰለሚችል፣ ቢያንስ ከታሪካችን እንማር! የተራዘመ ሰላማዊ ህዝባዊ ትግል ውስጥ በአላሚ ተኳሽ አጋዚ መገደል አለ፣ በዚያው መጠን በደምፍላት የሚደረግ መልስ ይኖራል፣ ለዚህም ተጠያቂው አልሞ ተኳሹ ነው። ይህን ሃቅ ህዝቡም ይረዳል። ከዚህ በላይ ሄደን ግን በፖለቲካ አመራር ደረጃ “የህወሓትን ሰላዮችና ገዳዮች ከስርአቱ ጋር ምንም ቁርኘት ከሌላቸው የትግራይ ተወላጆች ነጥሎ መመታት አስፈላጊ” ነው ብለን አናውጅ ። ያ ፍፁም ስህተት ነው። የህወሓትን ሰላዮችና ገዳዮች የመፋረድ ጥያቄ የህዝብ ነፃ እርምጃ ሳይሆን፣ ትግሉ ድል ካደረገ በኋላ በመደበኛ ፍርድቤቶች የሚያዝ የፍትህ ጉዳይ ነው ።

Filed in: Amharic