>

አስራ ስምንተኛዋ መርፌ (አቢ ጌቱ)

በጦርነቱ ያሸነፉ ጎፈሬ ወታደሮች አዲስ አበባን ተቆጣጥረዋት በደስታ እየጨፈሩ ነው ። ከዚም ከዛም ቅልጥ ያለ ጭፈራና ሁካታ ይሰማል!
ከሚተረማመሱ ታጋዮች መሀል ፣ አንዱ ይዞት ከመጣው በጨርቅ የተጠቀለለ ንብረቱ ውስጥ ምንም አለመጉደሉን መፈተሽ ጀመረ ፤
ሽጉጥ ፣ በሶ መበጥበጫ ፣ በሶ ፣ የቆረፈደ ቆዳ ጫማ ፣ መጽሀፍ ፣ አሁንም ሌላ መጽሀፍ ፣ቁምጣ ( አቧራ ስለነበረው አራገፈው) ፣መነጸር ፣ ለብቻቸው በትንሽ ጨርቅ የተቋጠሩ ሌሎች መጽሀፍቶች ( በትግል ወቅት ካነበባቸው ውስጥ የወደዳቸውና የደጋገማቸው ናቸው ) … በመጨረሻም ደግሞ ማበጠሪያ ( የጓደኛው ነው) ። እቃው ሙሉ መሆኑን እንዳረጋገጠ መላጣውን እያሸ ወደ ፊት ተራመደ ።

መርፌዋ መሬት ላይ ባፍጢሟ ተደፍታ ለጥቂት ደቂቃዎች ከቆየች በኋላ ከሰመመኗ ነቃች ። ዙሪያዋን ስትቃኝ…ብቻዋን ናት! ። አፈር የቃመ አንድ አይኗን በደንብ አራግፋ ወደ ፊት ተመለከተች፣ የመርፌዋ ባለቤት ጓዙን ጠቅልሎ እየገሰገሰ ነው ። ጫማዎቹ በየተራ መሬት ሲረግጡ ይታያታል ፤ ቅድም እቃውን ሲፈትሽ ተሰክታ ከነበረበት ቁምጣ ተራግፋ እንደወደቀች ገባት ። “ኸረ ኡኡ …ኸረ ኡኡ…ኸረ እኔ ተረስቻለሁ ” መጮህ ጀመረች ግን..ማንም አልሰማትም ።

ብዙ ቀናቶች አለፉ…እሷ ግን አሁንም እየጮኸች ነው ። ከወደቀችበት ቦታ ትንሽ ፈቀቅ ብሎ የተደረደሩ የቆርቆሮ ቤቶች አሉ ። ከቤቶቹ ያረጁ ግድግዳዎች ውስጥ አንዳንድ ሚስማሮች አንገታቸውን ብቅ ያደርጉና ” እብዷ..እብዷ ” እያሉ ይስቁባታል ። በጣም ትናደዳለች …እነሱ ግን በጮኸችና በተናገረች ቁጥር ማብሸቃቸውን ይቀጥላሉ ። ሁሌም ትጮሀለች እነሱም ድምጿን ለምደውታል ። የአካባቢው ሚስማሮች ማለዳቸውን የሚጀምሩት በዶሮ ጩኸት ሳይሆን በእሷ ቅዠት ነው ። ” ኸረ ኡኡ ..ኸረ እኔ ተረስቻለሁ” በሚለው ጩኸቷ ።

አንድ ቀን …ሁሉም ሚስማሮች አርፍደው ከእንቅልፋቸው ነቁ…ለምን?..ምክንያቱም መርፌዋ አልጮኸችም ። ከሰጠሙበት ግድግዳ ውስጥ አንገታቸውን አስግገው ተመለከቷት ፥ ተጣማ ወድቃለች ! እርስ በርሳቸው ምን ሁና ነው መባባል ጀመሩ ፤ አንድ ሸምገል ያለ ሚስማር ” ዛሬ በአል አይደል?..ግርግሩን እዩት..ምናልባት የሆነ ሰው ሲራመድ በእግሩ ደፍጥጧት አልያም በመኪና ጨፍልቋት ይሆናል ” አለ ።

ብዙ ወቅቶች ተቀያየሩ …የስልጣን ድልድል ወቅቶች ፣ የትያትር ወቅቶች ፣ የልብወለድ ወቅቶች፣ የስእል ወቅቶች …ብዙ ወቅቶች …
ከሙዚቃ ወቅቶች ባንዱ
የ ቴዎድሮስ ካሳሁን አንድ አልበም ተለቀቀ ። አልበሙ ወዲያውኑ በህዝቡ ጆሮ ውስጥ አስተጋባ ። በተለይም ” ጃ ያስተርያል ” የሚለው ዘፈን በጣም ተወደደ ። አልበሙ እንደተለቀቀ አንድ ረጅምና ሾጣጣ ጭንቅላት ያለው ቀጭን ሰው ፣ ተቀምጦበት ከነበረው ምግብ ቤት እንደ ድንገት መድረፍ ብሎ በመነሳት ተፈተለከ ።
መልስ ልትሰጠው እጇን አንከርፍፋ የነበረችው አስተናጋጅ ፥ አፏን ከፍታ በአይኖቿ ተከተለችው ።
ምግብ ቤቱ ውስጥ የነበሩና ድንገተኛ አሯሯጡን ያዩ ሰዎች በመገረም አዩት።
ሰውየው በንዴትና በአልህ ተሞልቶ ሮጠ…ድንገት ግን ድንጋይ አንከላፍቶት በአፍጢሙ ተተከለ ። ግራና ቀኙን ሲያማትር ሰው ሁላ እያየው ነው…ለመነሳት ሞከረ..በአይኑ ትክክል አንዲት የተጣመመች መርፌ ተመለከተ…በኪሱ ያዛትና ጥድፊያውን ቀጠለ ፤
ታክሲ መያዣው ጋር እንደደረሰ ፥ ወደ ቦሌ በሚወስደው ታክሲ ውስጥ ተሳፈረና ከሰው እይታ ተሰወረ ። ሲሳፈር ረዳቱና ታክሲው ውስጥ የነበሩ ሰዎች ትኩረታቸውን ወደ እሱ አዞሩ …አለመረጋጋት ይታይበት ነበር ።

ከስብሰባ ወቅቶች ባንዱ …
ስምንት ትልልቅ ባለስልጣናት አንድ ቅንጡ ሆቴል ውስጥ ዝግ ስብሰባ ይዘው ተፋጠዋል ።
ለ አንድ ሰአት ተኩል ያህል ያለ ምንም መግባባት የቀጠለው ይህ ስብሰባ አሁንም ከነ ውጥረቱ እንደቀጠለ ነው ።
“ምን ብናደርግ ይሻለናል?” አሉ መሀል ላይ የተቀመጡትና ሌሎቹን እንደፈለጉ የማዘዝ ስልጣን ያላቸው ሸምገል ያሉ ሰውዬ! ሁሉም ጸጥ አለ ።
በዛ ሁሉ የጦፈ ክርክርና ውይይት ውስጥ ምንም ቃል ትንፍሽ ያላለው ሾጣጣ ሰው ለመናገር ጉሮሮውን ጠረገ ። ሽማግሌው ቀጥል የሚል ምልክት በእጃቸው አሳዩት
“ይሄ የወጣት ሀይል ሁሌም ሰው መናቅ ልማዱ ነው።” ብሎ ጀመረ! ሁሉም እያዳመጡት ነው ። መናገሩን ቀጠለ
” ወጣቱ ሀይል ሰው የመናቅ ልምድ አለበት ….
ጃንሆይ እንደ አምላክ ይታዩ በነበሩበት ወቅት ፥ ህዝቡ እርቃኑን ሁኖ የቀረችው እራፊ ላይ እንዲራመዱ ይፈቅድ በነበረበት ወቅት ፥ ወጣቱ የአዲስ አበባ ተማሪ ” ሽማግሌ ” ብሎ ሰደባቸው! አድማ አደረገባቸው ፥አሳመጸባቸው! ንጉሱ ከዚያ በኋላ ስልጣን ላይ መቆየት አልቻሉም ። ይታያቹህ እንግዲህ ” ምራቁን ዋጠና መናገሩን ቀጠለ ።
” ሽማግሌው ንጉስ ከእድሜያቸው በሚያንሱ ወጣቶች ተረግመው እንጦሮጦስ ወረዱ ።
ተተኪው ደርግ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን በዘመቻ የጨፈጨፈው ያለ ነገር አልነበረም! የወጣቱ ሀይል እሱንም እንደ ንጉሱ አንድ ቀን እንደሚዘረጥጠው ያውቅ ስለነበር ነው ። ”
” ወደ ነጥብህ! ” አሉ የሀሳቡን መጠቅለያ ቶሎ መስማት የፈለጉ ሌላኛው ባለ ስልጣን!
” አዎን ወደ ዋናው ነጥብ ቶሎ ግባ ” አሉት ሌላኛውም ባለ ስልጣን ተቀብለው!
” እንግዲህ እኛም ብንሆን ከትምህርት ርቆ የነበረውን ይህንን ማህበረሰብ ባስተማርን ፥የውሀ ቦኑ በከፈትን ፥ ህንጻ ባቆምን..እንናቃቹ እየተባልን ነው! !
ትናንትና የሞቀ አቀባበል ያደረገልን የወጣት ሀይል ዛሬ ዝቅ አድርጎ በመርፌ ይገልጸናል! በእሳት እየተለበለብን ከእሳት አድነነው ፥ ዛሬ እኛን እንደቀላል “በ 17 መርፌ ” ብሎ ያሽሟጥጥብናል ይጠራናል!”
” እና ምን ይሻለናል ነውኮ ዋናው ጥያቄ? አሉ የቅድሙ ባለስልጣን
” እንግዲህ አንድ አባባል አለ …ለሰው መልካም ሁን…ሰይጣን ብሎ እስኪሰድብህ ድረስ ክፉ አትሁንበት!..መልካም ሁነህለት ሰይጣን ካለህ ግን ሰይጣን ሁነህ አሳየው ”
“ምን ማለት ነው? ” አሉት ሽማግሌው..አጠያየቃቸው ( ቀድሞውንም ሰይጣን መሆናችን ይካዳል እንዴ የሚሉ ነው የሚመስሉት)
” ጓዶች ሌላ መርፌ ያስፈልገናል ….አስራ ስምንተኛ መርፌ !” አለ ሾጣጣው!
ከኪሱ አንዲት ጎባጣ መርፌ አወጥቶ ከፍ አድርጎ እያሳያቸው!

ከጥቂት ጊዜ በኋላ አስራ ስምንተኛ መርፌ ደረቷን ነፍታ በከተማው መሀል መታየት ጀመረች! ሲያሾፉባት የነበሩትን ሚስማሮች እንዳለ ከነ ማገራቸው አስፈረሰቻቸው !! ” አዲስ አበባ ውስጥ ካርታ የሌላቸው ህገ ወጥ ቤቶች በመፍረሳቸው ግጭት ተቀሰቀሰ ” የሚል ዜና ተሰማ !
ከዛ በፊትም ብዙ ዜናዎች ተሰምተዋል ። መርፌዋ ጎዳና ላይ ጥላዋን ከጣለች በኋላ
ብዙ ሙዚቀኞችን ሸቤ ወርውራ ጀርባቸውን ጠቅጥቃለች ! …ለብዙ ሰዎች ክንዳቸው ላይ የክስ ታቶ ( ንቅሳት) ሰርታለች ።
በአል ለማክበር ከቤታቸው የወጡ ነዋሪዎች መጨረሻቸውን የልብ ውጋት አድርጋለች….እስካሁን ያገኘችውን እየረገጠች ነው…እንደቀድሞው የረገጣት የለም ..አስራ ስምንተኛዋ መርፌ …ማንም ይፈራታል!!

( አቢ ጌቱ / Natnael Getu )

Filed in: Amharic