ደረጄ ገረፋ
ጋዲሳ ሆማ
ሚልኬሳ ሚደጋ
አዲስ ቸኮል
ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ሌሎች ሰዎችም አሉ። ሆኖም እነዚህኛዎቹ ከህወሓት ጋር ንክኪ ስለሌላቸው ነው እንደምሳሌ ያቀረብኳቸው።
—-
አድማው አስፈላጊ አይደለም ያልኩበትን ምክንያት በዝርዝር አስቀምጫለሁ። በበኩሌ አቋሙ የራሴ እንጂ የማንም አልነበረም። ከዚህ በፊት የማልስማማባቸውን አቋሞች በግል የፌስቡክ ገጼ ላይ እገልፅ ነበር።
ታዲያ በቄሮ ከታቀፉት ወጣቶቻችን መካከል ብዙዎቹ ከዓመታት በፊት እንዲህ ዓይነት ልዩነትን የማየት ፍላጎት አልነበራቸውም። ብዙዎቹ አትኩሮት ለመሳብና ሆን ብዬ እነሱን ለማበሳጨት የማደርገው ይመስላቸውና ያልተገባ ጨዋታ ውስጥ ይገቡ ነበር። ለምሳሌ “ወያኔ ነው የላከህ፣ ጎበና ሆነሃል፣ ገንዘብ ተከፍሎሃል” የመሳሰሉ አስተያየቶችን በመስጠት ይጠመዱ ነበር። ዘንድሮ ግን ይህ ሁኔታ ተለውጧል። የቄሮ ወጣቶቻችን የአመለካከት ልዩነትን በማስተናገድ ረገድ በብዙ ርቀት ተራምደው ሄደዋል። ከአድማው መጀመር በፊት የለጠፍኳቸው ጽሑፎች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ብትመለከቱ የሚሸነቁጡ ወይንም ሰውን የሚስቀይሙ ነገሮችን የምታዩት እጅግ በጣም አልፎ አልፎ ነው። ይህ ስንፈለገውና ስንጠብቀው የነበረ ታላቅ ለውጥ ነው።
በሌላ በኩል ቄሮዎች የስርዓቱ ካድሬዎች በሶሻል ሚዲያው ላይ የሚጫወቱትን የማደንዘዝና አትኩሮት የማስቀየር ጨዋታ በዝምታ ንቀው መግደላቸው ብዙዎችን አስደንቋል። ለምሳሌ ዳንኤል ብርሃነ፣ ፍፁም ብርሃነ፣ ሴቭአድና ወዘተ ሰሞኑን ሲያቦኳቸው በነበሩት የተንኮል እንጀራ መጋገሪያ አብሲቶች ውስጥ ላለመግባት ጥንቃቄ አድርገው ትግላቸውን ሲያካሄዱ ነበር። በፌስቡክ ላይ ጭምብል ለብሰው ሲነፋረቁ መንጋው በሚያጎርፍላቸው ላይክና ኮሜንት ሱስ አብደው ራሳቸውን የመጪው ዘመን እሳቤ ስትራቴጂስት አድርገው ለመቁጠር የሚዳዳቸው ወጀላቴዎች ቄሮን ባልተሞረደ ብእራቸው “ዱልዱሞች” እና “የሰገጤ ትግል” እያሉ ቢተነኩሱትም ወጣቶቻችን እነርሱንም ከመጤፍ አልቆጠሯቸውም። ቄሮ ማእቀብ የጣለው በገበያው ላይ ብቻ ሳይሆን በነርሱ ላይ ጭምር ነው። ይህ ብዙዎችን ያስደነቀ ከመሆኑም በላይ ሁላችንም ልንማርበት የሚገባ ቁምነገር ነው።
ሶሰተኛው ነገር ደግሞ ህዝብን ከፖለቲካ ስርዓት ለይቶ የማየት ጉዳይ ነው። እኛ እንደዚህ እያልን የምንወተውትበትን ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜ ገልፀናል። ታዲያ እንደዚህ ስንል አንዳንድ የዋሆች ከስርዓቱ መተያ ተቀብለን የምንለፈልፍ ይመስላቸው ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንዲህ ዓይነት ነገር ቆሟል። በዚህ ረገድ አንድ የኦሮሞ ልጅ የሰራውንና ልቤን የነካውን ሁነኛ ድርጊት ልጥቀስ።
ነጌሳ ኦዱ ዱቤ የሚባል አክቲቪስት እዚህ ፌስቡክ ላይ አለ። ይህ ልጅ “ህዝባችንን እያስጨረሰ ያለው ጌታቸው አሰፋ የሚባል የደህንነት ሹም ይህ ነው” የሚል ጽሑፍ ከአንድ ፎቶግራፍ ጋር በፌስቡክ ላይ ለጠፈ። ወዲያውኑ የአሲምባ ፍቅር የተባለውን ተወዳጅ መጽሐፍ የጻፈው አንጋፋው የኢህአፓ ታጋይ ካህሳይ አብረሃ ወደኔ ኢንቦክስ መጥቶ “እባክህ አፈንዲ፣ ይህ ልጅ ስሜን የሚያጠፋ ነገር ለጥፏልና እንዲያነሳው ንገርልኝ” አለኝ። እኔም ፎቶግራፉን ሳይ የካህሳይ ፎቶ እንደነበረ ተረዳሁና “ነጌሳ: የለጠፍከው መረጃ ስህተት ነውና አንሳው” አልኩት። እውነቱን ከሌሎች ምንጮች እንዲያጣራም ነገርኩት።
ነጌሳ በጥያቄዬ መሰረት አጣራና ፖስቱን አነሳው። ታዲያ በዚያ ብቻ አላበቃም። ለስህተቱ ይቅርታ የጠየቀበትንና በፎቶግራፉ ላይ የተመለከተው ሰው የኢህአፓው ካህሳይ አብረሃ መሆኑን ጭምር ያስታወቀበትንም የማሰተካከያ ፅሑፍ ለጥፏል።
ከሶስት አመታት በፊት እንዲህ አይነት ጽሑፍ ሲጽፉ ያገኘኋቸው ሁለት ሰዎች ስህተታቸውን እንዲያስተካክሉ ስጠይቃቸው ግን “አንተን የትግሬ ጠበቃ ምን አደረገህ? ትግሬ ሁሉ ወያኔ ስለሆነ ብሳሳት እንኳ አይቆጨኝም” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡኝ። ከዚህ እንደምንረዳው የቄሮ ወጣቶች በስልትና በቁርጠኝነት ብቻ ሳይሆን በእይታ፣ በምልከታና በግንዛቤ ክህሎት በጣም አድገዋል።
—–
ቄሮ የገበያና የስራ ማቆም አድማ ሲያውጅ ለአራተኛ ጊዜ ይመስለኛል። የመጀመሪያው አድማ የራሱ ውጤቶች ነበሩት። ሁለተኛውም የራሱ ውጤቶች ነበሩት። ሶስተኛውም ውጤት አምጥቷል። ከሁሉም በላይ በስርዓቱ ላይ ከባድ ተፅእኖ ያሳረፈውና ፈጣን ውጤት ያመጣው ግን የአሁኑ አድማ ነው። ይህኛው አድማ እነ በቀለ ገርባን በአፋጣኝ ሁኔታ ከማስለቀቁም በላይ ስርዓቱ እጅግ በጣም መዳከሙን ያሳየን ሆኗል።
የአሁኑ አድማ በተጨባጭ ሊገቡን ላልቻሉ ጉዳዮችም ምላሽ አስገኝቷል። ለምሳሌ
1ኛ: ብዙ ሰዎች “ቄሮ በኦህዴድ ተጠልፏል፣ በኦህዴድ ቁጥጥር ስር ውሏል፣ ስለዚህ ህልውናው ያስፈራል” የሚል እይታ አላቸው። ዛሬ የተገኘው ውጤት ግን ቄሮ ዛሬም ህልውናው ነፃ እንደሆነ አሳምኖናል። በተለይ ግን በባህሪያቸው ተጠራጣሪ (Skeptic) የሆኑ እኔን የመሳሰሉ ሰዎች ቄሮ ከኦህዴድ ተፅእኖ ነፃ በመሆኑ እጅግ በጣም ተደስተዋል (ኦህዴድ በቅርብ ጊዜ ያመጣቸውን ለውጦች ባደንቅለትም ከመነሻው በህወሓት አማካኝነት ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር በተማረኩ ወታደሮች የተመሠረተ ድርጅት መሆኑ ሙሉ በሙሉ እንዳላምነው ያደርገኛል)።
2ኛ ኦህዴድ እና ኢህአዴግ እንደ ድሮው አለመሆናቸውም ይታወቃል። ኦህዴድ በኢህአዴግ ውስጥ ትግል እያካሄደ እንደሆነም ይታወቃል። ይህ ትግል ቄሮ በቅርብ ጊዜያት ላመጣቸው ለውጦች አስተዋፅኦ እንዳደረገም ይታመናል። ነገር ግን “ወሳኙ የትግል ኃይል የትኛው ነው? ቄሮ ወይንስ የኦህዴድ አመራር?” በሚለው ጥያቄ ላይ ከፍተኛ የሆነ ብዥታ ነበረብን። የዛሬው ውጤት ግን ሁሉንም ገላልጦ አሳይቶናል።
—–
በእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና መፈታት ሲደሰት የከረመው የኦሮሞ ህዝብም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በእነ አቶ በቀለ ገርባ መለቀቅ ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆኗል። በማስከተልም እነ እስክንድር፣ አንዷለም፣ ውብሸት፣ አህመዲን ጀበል፣ አህመድ ሙስጠፋና ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱና ኢትዮጵያን ከዳር እስከ ዳር የሚያጥለቀልቅ የፍስሐ ጎርፍ ይፈሳል ብለን እንጠብቃለን።
ሁላችንም እንኳን ደስ አለን።
አንድዬው አላህ/ዋቃ/አምላክ/ዋቅ/ረቢ ቄሮን ከመጥፎ ነገር ሁሉ ይጠብቅልን!!
—
አፈንዲ መተቂ
ሸገር፣ ገንደ ሀሮሬሳ (አውቶቡስ ተራ)