>

ከሩቅ ሳይሆን ከቅርብ የሚሰማው አስገምጋሚው የለውጥ ድምፅ (መሳይ መኮንን)

ነገሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ ነው። ይህ ሳምንት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁነኛ ለውጦች የምናይበት ሊሆን እንደሚችል በባለፈው ጽሁፌ አንስቼ ነበር። ቄሮዎች ኦሮሚያ ክልልን ለሶስት ቀናት በአድማ ቀጥ አድርገው አቆሟት። እነበቀለ ገርባ ተፈቱ። እነእስክንድር ከማጎሪያ እስር ቤት ወጡ። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣኑን ለቀቀ። የአስቸኳይ ጊዜ ከዛሬ ጀምሮ ለ3ወራት ታወጀ። አሜሪካን አደጋ አለ እያለች ነው። ምዕራባውያን ቅጥረኛ መንግስታቸው፡ ዶላር፡ ፓውንድና ዩሮ እየጋቱ ወፌ ላላ ያቆሙት አገዛዝ እንደበርሊን ግምብ ሊደረመስባቸው ተቃርቧል።
ፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል። ኦህዴድ በአሸናፊነት ስሜት ለቀጣዩ ትንቅንቅ አድፍጦ እየጠበቀ ነው። ብአዴን የህወሀት አሽከርነት ወይም ነጻነት ላይ ሪፈረንደም ተቀምጧል። የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ሳይቀር በተነሳበት የብአዴኑ ጉባዔ የመጪው የኢህአዴግ ጉልበት ላይ ሚዛኑን ይወስናል። የኢህአዴግ ቀጣዩ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆን? የኢትዮጵያውያን ራስ ምታት አይደለም። አይሆንምም። የራሳቸው ጉዳይ።
የጉራጌዋ ወልቂጤ ተነስታለች። ከወዲያ ማዶ ማሻ ከተማም ነጻነት ርቧታል። ጋምቤላ ጥሪ አድርጋለች። አርባምንጭ እያሟሟቀች ናት። ኦሮሚያ ክልል ለሌላ ዙር ህዝባዊ ንቅናቄ ትንፋሽ እየወሰደች ናት። አማራ ክልል ቀጠሮ ላይ ናት። የፈረቃ ትግሉ እያበቃ ነው። ሁሉም ስለአንድ ጉዳይ በአንድ ላይ የሚነሳበት ጊዜ እየቀረበ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስቆመው ይሆን? በፍጹም!!
አዲስ አበባ ታክሲ ውስጥ ስለለውጥ አብዝቶ እየተወራ ነው። መንገድ ላይ በሰዉ ፊት የሚነበበው ለውጥ ነው። የነጻነት ረሃብ። በከተማ አውቶብስ ውስጥ፡ ባጃጅ ላይ የተሳፈረ ሁላ ወሬው እያስገመገመ በመምጣት ላይ ስላለው ለውጥ ነው። አንዱዓለም አራጌ እንዳለው ”ኢትዮጵያ ስትፈታ ነው ደስታዬ ሙሉ የሚሆነው”። የሁላቸንም ህልም ይሄው ነው።
Filed in: Amharic