>
5:21 pm - Friday July 21, 8519

ለሚገባችሁ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬ ከክብሮትና ፍቅር ጋር ይድረሳችሁ….(አንዱዓለም አራጌ)

“ከኢሕአዴግ ፈርጣማ መዳፍ የሚታደግ እንደሌላ እያወክ ድህረት ከየት አመጣኸው ?” እያሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ። መልሱ ግን ቀላል ነው። የድፍረቴ ምንጭና ተስፋዬ ፣ በእስር ቤት ትቢያ ላይ ስጣል ለአፍታ እንኳን ያልተለየኝ ፣ በመከራ ሁሉ እግሮቼ እንዳይናወጡ ትልቁ ጽኑ አለት የሆነኝ እግዚአብሄር ነው። ለርሱ ክብር ምስጋና አምልኮ ይድረሰው።

የምወዳችሁ ልጆቼ ሩህና ኖላዊ፣ በሕጻንነት አይምሯችሁ ምህዋር ላይ ሲጉላሉ የነበሩ ጥያቄዎቻችሁን መመለስ ባለመቻሌ ፣ እኔን ለመጠየቅ በተመላለሳቹህባችሁ አመታት ለወደቃችሁ፣ ለተነሳችሁት፣ ለደማችሁት ፣ እንዲሁም በጣም በማስፈልጋችሁ ሰዓት ከሕይወታችሁ በግፍ በመጉደሌ በጣም አዝናለሁ።ይቅርታ ታደረጉልኝም ዘንድ እጠይቃለሁ። ምን አልባት አንድ ቀን ለምን ቤተሰባችን  አሁን ባለፈበት ሁኔታ ማለፍ እንደተገደደ በዉል እንደምትረዱ፣ አሁን እንደ ቤተሰብ ካለፍንበት የአፈር ሰርጥ የምንጽናናበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ። በዉል በማታወቁት አለም፣ ሰሙንና ገጽታዉን እንኳን በበዉል የማትለዩትን አባታችሁን ባልጠና እግራችሁ ተመላልሳችሁ ስለጠየቃችሁኝ፣  ሳልሰጣችሁ ስለሰጣችሁን በተትረፈረፈ ንጹህ ፍቅር በጣም አመሰግናቹሃለሁ።

አያሌዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ የዲሞክራሲያው ስርዓት ባለቤት ይሆን ዘንድ በዋጋ የማይታመነውን ክብር ሕይወታቸውን እንኳን ሳይነፍጉ ሰጥተዋል። በኩራት በክብርና በሰላም የምትኖር ኢትዮጵያ ትፈጠር ዘንድ እኔም የበኩሌን ትንሿን አስተዋጾ ለማበርከት ባደረኩት ጥረትና በከፈልኩት ዋጋ በጣም ነው ደስታ የሚሰማኝ።  እራሴን እንደተባረከ አድርጌ ነው የምቆጥረው።

“ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል” እንዲሉ ቀደም ሲል በ”ነውጠኛው ቅንጅት” ወደ ሁለት አመት ገዳማ፣ አሁን ደግሞ በ”አሸባሪነት” ስድስት አመት ተኩል በድምሩ ከስምንት አመት በላይ የሕወሃት ወግ ማእረግ የምናይባቸውን አፍላ አመታት በግፍና በዉሸት በተደረቱ የአገዛዙ የአፈና ተግባራቶች ተነጥቀናል። ከአጠገብሽ ባልነበሩካብቸው በነዚህ ሁሉ አመታት ፣ በጽናት ከጎኔ ስለቆምሽው፣ የኔንም ሚማ ጭምር በመወጣት ልጆቻችን በማሳደግ ለከፈልሽው ዋጋ፣  ላደረግሽልኝ ትልቅ ድጋፍ ሁሉ ባለቤተ ሰላም አስቻለ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረስሽ።

በገጠር በከተማባ በዉጭ ሀገር የምትገኙ ቤተሰቦቼ በሙሉ በተለይም ፍሬሕይወት እንዳለ፣ ሚኪያስ እንዳለ፣ ዜና ደሳለኝና ዳግም ደሳለኝ ለፍቅራችሁና ለጥያቂያችሁ በጣም አመሰግናለሁ።

በድንገት ከአጠገባችሁ ተነጥዪ ብታሰርም በመንፈስ አብራችሁኝ ለታሰራችሁ እኔንም ለማስፈታትና የታሰርኩበት አላማ ዳር ለማድረስ ስላደረጋችሁት ተጋድሎ የፓርቲዬ የቀድሞ አንድነት ለዲሞክራሲ ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) አመራርቾንም አባላትን ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አብሬ ለመስራት በመቻሌ ደስ የሚለኝ በሰሜን አሜሪካ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ የድጋፍ ሰጭ ኮሚቴዎች አባላት ሁሉ ላደረጋችሁት ትግልና ላደረጋችሁልኝ ድጋፍ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ጠበቆቼ አቶ ደርበው ተመስገንና አቶ አበበ ጉታ ብዙዎች እንኳን ጥብቃን ሊቆሙልኝ ቀርቶ በሩቁ በሚሸሹን ሰዓት ፣ ሊደርስባችሁ የሚችለውን ሁሉ ሳትፈሩ የነጻ ያህል በሚቆጠር ክፍያ በከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ሰሚች ችሎት ድረስ አብራችሁን ስለተንከራተታችሁና ስላደረጋችሁት  ጥረት እግዚአብሄር ዉለታችሁን ይክፈላችሁ።

በመላው አለም በተለይም በሰሜን አሜሪካ እስራኤልና አዉሮፓ የምትገኙ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ አባላት በተለይም ትግሉ ለማገዝ ለአመታት ባለመታከት እየሰራችሁ ያላችሁ አክቲቪስቶች ፣ የአየር መለዋወጥና አስቸጋሪው የሕይወት ዉጣ ዉረድ፣  የአሁኑ ዘመን መርዝም ሳያዝላችሁ ከጎኔ ስለቆማችሁ እንዲሁም የታፈነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጩኸት ከፍ አድርጋችሁ ለአለም በማሰማት ስለምታደረጉት አስተዋጾ የላቀ አክብሮትና ምስጋናዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።

በሀገርም በዉጭም የምትገኙ ጋዜጠኞች ፣ ብሎገሮች፣ ድረ-ገጾችና የመገናኛ ብዝሃን ተቋማት እዉነቱን ለሕዝብ ለማሳወቅ ስለሰራችሁ ስራ ሁሉ በጣም እያመሰገንኩ በተለይም ኢሳት ቴሌቭዥንና ዘሃበሻ ድህረ ገጽን እንዲሁም የዞን ዘጠኝ አባላትንና ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።

በአገርም ውስጥ ሆነ በዉጭ ሃገር የምትግኙ በተቃዉሞው ጎራ የተሰለፋችሁ ሃይሎች ሁሉ  ያሉን የፕሮግራምና የ ስትራተጂ ልዩነቲች ሳይገድበን የዲሞራሲና የመበት መገፈፍ ጉዳይ የሁላችንም በመሆኑ በአንዱ ላይ የሚደረሰው በሁላችንም ላይ እንደደረሰ ይቆጠራል ብላችሁ ላሰማችሁት የይፋታ ጥሪ በጣም አመሰግናለሁ።

የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አባላት “ Injustice anywhere is a threat to justice everywhere” ብላችሁ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው አፈና እንዲቆም ስለምታደረጉት ጥረት እኔም እፈታ ዘንድ በራሳችሁ መንገድ ስላደረጋችሁት ጥረት አመሰግናለሁ።

በመጨረሻ ለዘመናት በተንሰራፋው የአገዛዙ ማነቆ ታንቆ የጭቆናንና የጭንቅን አመታትን እየገፉ የሚገኘው የኢትዮዮጵያ ሕዝብ፣  በዉል የሚገባው የግፍ ስቃይ በእኔና በቤተሰቤ ላይም ሲደርስ፣ ፍርድ ወደማያዛበው ፈጣሪ ችሎት አቤት በማለትና በልዩ ልዩ መንገዶች ድጋፉን በመግለጽ እንዲሁም ፍጹም የማይገባኝም ፍቅርና አክብሮት በመለገድ ለእነኤ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቺም ትልቅ ሞራልና ስንቅ ሆኗል። ለኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ ሁሉ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እራሴን ዝቅ አድርጌ ከልቤ የሚቀዳዉን ምስጋናና ፍቅር አቀርባለሁ።

እኔና ጥቂት ኢትዮጵያዉያን ከክፉ እስር መፈታታችን ለብዙዎች በተለይም ለቅርብ ቤተሰብ አባሎቻችን እፎይታን ቢሰጥም እዉነታኛዉና ዘላቂው እፎይታ የሚመጣው ግን ኢትዮጵያ ከዘመን ጠገቡ የአገዛዝ ቀንበር ተፈታ፣ ዴሞክራሲያዊነት ሀገር መሆን ስትችል ብቻ ነው። አንድ ህዝብም ሆን ሀገር በትክክል ታላቅ ነው የሚባለው በሰራው ድልድይ ወይንም መንገድ ሳይሆን የሉዓልዊ ስልጣን ባለቤት ሲሆን ነው። ይህ እስኪሆን ድረስ እጅ  ለእጅ ተያይዘን የጸና ሰላማዊ ትግል ከማድረግ ዉጭ የቀረን አማራጭ የለም።

በዚህ ሂደት ፍጹም ከእኛ ልናርቀው የሚገባው ነገር ካለ የመጀመሪያው ዘረኝነት ነው። ለእኔ ሰውን በዘሩ ምክንያት ከመጥላት ብሎም ከማጥቃት በላይ ኢሰባአዊነት የለም። በምንም አይነት መንገድ ወደዚህ ደረጃ እንዳንወርድ ልንጠነቀቅ ይገባል። ይልቅስ ቀንበሩ የተጫነው ሁላችንም ላይ ነዉና እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን ልንታገል ይገባናል።

ነጻነት እንደ ቀትር ጸሃይ፣  ወንድማማችነት እንደ ጉንጉን አበባ፣ ፍትህ እንደ ሃይለኛ ጅረት በኢትዮጵያ ላይ ይንገስ።

አንዱዓለም አራጌ

Filed in: Amharic