ያሬድ ሀይለማርያም
ኢትዮጵያን በተመለከተም ይሁን ከኢትዮጵያዊነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሁለቱ ግለሰቦች ፍጹም የተለያየ እሳቤ እና አቋም እንዳላቸው ግልጽ ነው። ሁለቱም ባመኑበት መንገድ የመሔድ፣ ያሻቸውን የማሰብ እና የመረጡትን የፖለቲካ አቋምም ሆነ ምልከታ የመያዝ መብታቸው ለውይይት የሚቀርብ አይደለም። ጃዋርን በአደባባይ መንቀፍ የሚፈሩ ሰዎች እስክንድርን ሲያብጠለጥሉ፣ ሲዘልፉ እና ሲያጣጥሉ ሳይ ገርሞኝ ነው ይህን አጭር ትዝብት ለመጻፍ የተነሳሁት። ትዝብቴም ኢትዮጵያ ሁለቱን ልጆቿን እንዴት ነው የያዘቻቸው የሚለውን ጉዳይ አንስቶ መወያየት የግድ ሳይል አልቀረም በሚል ነው።
ኢትዮጵያ የሁለቱም ነች። ኢትዮጵያን በተመለከተ እነሱ ያላቸው ምልከታ ከግምት ሳይገባ ማለት ነው። ጃዋር በአደባባይ ኢትዮጵያን ቅኝ ገዥ አድርጎ እና Ethiopia out of Oromia የሚል መፈክር አያሰማ የፖለቲካውን ፍልሚያ የተቀላቀለ አክራሪ ብሔረተኛ ነው። ትግሉንም በብዙ ሺ ማይልስ ላይ ሆኖ እና ከወላፈኑም እርቆ የመራና የተሳካለት የመብት አቀንቃኝ ነው። እስክንድር ኢትዮጵያ የሁላችንም ነች፤ አንድ አገር፤ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ባንዲራ የሚል መፈክር አንግቦ ለዲሞክራሲ የሚታገል ኢትዮጵያዊ ብሔረተኛ ነው። እዛው እሳት ውስጥ ቆሞ ሲታገል የኖረ፣ ለዛም እራሱ እና ቤተሰቦቹ ትልቅ ዋጋ የከፈሉ፣ እሱም በረዥም የእስር ዘመን ቁም ስቅሉን ሲያይ የኖረና በጽናቱ የሚታወቅ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ነው።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ለጃዋር የተደላደለችና ያሻውን ለማድረግ የሚችልባት ምቹ ደሴት ስትሆን፤ ለእስክንድር ነጋ ደግሞ ትልቅ እስር ቤትና እሾህ የሆነችበት ምክንያት ምንድን ነው? ጃዋር ሲያዋርዳት፣ ሲዘልፋት እና ሲያንቋሻት በነበረችዋ ኢትዮጵያ እንደ አንድ መሪ ተከብሮ፣ በከፍተኛ የታጣቂዎች አጀብ ታጅቦ ከአንድ የአገሪቱ ጫፍ ወደ ሌላ እንደልቡ እየተዘዋወረ፣ ያሻውን እየተናገረ፣ መንግስትንም ጭምር እያስፈራራ እና እየዘለፈ ያሻውን ሲያደርግ፣ በሕዝብና መንግስት ላይ ሲዝት እና ሲፎክር፣ ተከታይ ጀሌዎቹን እያዘዘ የሚፈልገውን ሲያደርግ ጠያቂ የለውም። ባጭሩ ኢትዮጵያን እንደልቡ ያለ ሕግ እና ሃይ ባይ ሳይኖርበት እየፈነጨባትም ነው። ሲሻው ሸምጋይ፣ ሲሻው ምሁርና መካሪ፣ ሲሻውም እንደ አንድ የመንግስት ባለሥልጣን፣ ሲሻውም እንደ ለውጥ አቀንቃኝም ሆኖ በመንግስት መድረኮች እንደልቡ ይናገራል።

ጃዋርም ሆነ እስክንድር ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች የሚያራምዷቸው ሃሳቦች ላይ በዝርዝር መግባት አልፈልግም። ከሁለቱም ጋር የምስማማበትም የምለያይበትም ጉዳይ አለ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ለሁለቱ ልጆቿ፤ ለአንዱ ሲኦል ለሌላው ገነት የምትሆንበት ጊዜ ግን ማብቃት አለበት። መንግስት አንዱን ዜጋ ከነወንጀሉ እና ጥፋቱ እያሽሞነሞነ ሌላውን የሚገፋባት አገር የምትሆንበት ጊዜ መቀጠል የለበትም። ጃዋርም ሆኑ እስክንድር ባጠፉት ልክ ሊወቀሱ፣ በጣሱት ሕግ ልክ ሊጠየቁ ይገባል። እንዲሁም በሰሩት መልካም ነገርም ልክ ሊመሰገኑ እና ሊሸለሙ ይገባል። ለጃዋር እናት ለእስክንድር እንጀራ እናት የምትሆን ኢትዮጵያ ለሁላችንም አትሆንም።
የአንዱን ዜጋ ነጻነት ለማስፋት የሌላውን ዜጋ መብት እና ነጻነት ማጥበብ ተቀባይነት የለውም። ሁሉም ዜጋ እኩል መብት እና ነጻነት አለው። ሁሉም ዜጋ እኩል መብትሙ፣ ነጻነቱም ሊጠበቅለት ይገባል። ሁሉም ዜጋም ከሕግ በታች ሆኖ እኩል ተጠያቂነትም መስፈን አለበት።