>
9:51 am - Saturday December 10, 2022

እስክንድር ዛሬም ለጋዜጠኞች መግለጫ እንዳይሰጥ የእግድ ትእዛዝ ወጥቶበታል !!!  (ዮናስ ሀጎስ)


እስክንድር ዛሬም ለጋዜጠኞች መግለጫ እንዳይሰጥ የእግድ ትእዛዝ ወጥቶበታል !!!
 ዮናስ ሀጎስ
የሆነ ከተማ የእኛ ነው የሚሉ ገጠሬዎች ፀባይ በከተማው ተወልዶ ያደገን ሰው ከገጠር መጥተው  በገዛ ሃገሩ ህጋዊ በሆነ መንገድም ቢሆን እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ ነው። ይህን የሚያደርጉት ከገጠር መጥተው  ሳይወደዱ፣ሳይመረጡ እና ሳይፈለጉ የከተማ ስልጣን ላይ የተሳፈሩ ዘረኛ ሹማምንት ዘመዶቻቸውን ተተግነው ነው።
 የሰሩትን ከሰሩ በሃላ ታዲያ የገጠር አራዳን የሚመጥን  ከተሜን አመት የሚያስቅ ማታለያ ይዘው ይመጣሉ – “ለራሳችሁ ደህንነት ነው” የሚል የገጠር እርድና!
 የዛሬው የእስክንድር እግድም ምክንያቱ  “አጥፍቶ ጠፊ ጋዜጠኛ ወደ አዳራሹ እንደሚገባ ከተፎው የሃገር ደህንነት መስሪያቤት ከሞሳድ ጋር በጥምር ባደረገው እንቅስቃሴ ስለተገነዘበ ነው” መባሉ አይቀርም፨ “እውነት ነው እስኪ በጎ አስቡ” የሚል ቤተዘመድም፣ወዶ ገባ ተቃዋሚም አይጠፋም!
 
የመንግስት ክልከላዎች ነገር…
1) እስክንድር ነጋን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያሉበት አዲስ የሚድያ ተቋም መቋቋምን አስመልክቶ ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል የተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ በፌደራል ፖሊስ ጣልቃ ገብነት እንዲሰረዝ ተደርጓል። ሰናይ ሚድያ የሚል ስያሜ ለተሰጠው ለዚህ 24 ሰዓት አገልግሎት ስለሚሰጠው የቴሌቭዥን ጣቢያ ጉዳይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ለመስጠት የተያዘው ቀጠሮ ለምን ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ሊሰርዘው እንደቻለ ባይታወቅም ቅሉ ይህ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የመጣስ ድርጊት በእስክንድር ነጋ ላይ ሲፈፀም ያሁኑ ለሁለተኛ ጊዜው ነው። ከዚህ ቀደምም በራስ ሆቴል እስክንድር ጠርቶት የነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ፖሊስ «ለራሱ ለእስክንድር ደህንነት ሲባል»  በሚል ውኃ የማይቋጥር ምክንያት እንደሰረዘው የሚታወስ ነው።
2) የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከቀናት በፊት በአንድ የትግራይ ተወላጅ ላይ በደረሰ ጥቃት የተነሳ ለደህንነታቸው የፈሩ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ጓዛቸውን ሸክፈው በመውጣት አዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ ተሰባስበው የሚገኙ ሲሆን ፌደራል ፖሊስ ያሉበትን ቦታ በመክበብ ወደ ዩኒቨርሲቲው ከመመለስ ውጭ ምንም ዓይነት አማራጭ እንደሌላቸው በመግለፅ እያስፈራራቸው ይገኛል። ተማሪዎቹ በትግራይ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ እንዲመደቡ ጥያቄ ቢያቀርቡም ጥያቄያቸው ተሰሚነት አጥቷል። ከመንግስት ባለስልጣናት ውጭ ማንም እንዳይገባ ተከልክሎም በረሃብ እየተቀጡ ይገኛሉ። መንግስት ተማሪዎቹ ጥያቄውን ያነሱበት ተገቢ ምክንያት እንዳለ በማመን ቢቻል ከአማራ ክልል አስተዳደር ተወካዮች በመጨመር የተማሪዎችን የደህንነት ሁኔታ አስመልክቶ ዋስትና በመስጠት ወደነበሩበት ዩኒቨርሲቲ እንዲመለሱ የማግባባት ስራ መስራት አሊያም የትግራይ ክልል አስተዳደር ተወካዮች በመጨመር ተማሪዎቹ ወደ ክልላቸው ለመሄድ ከፈለጉም ያንን ፋሲሊቴት እንዲያደርጉ ነገሮችን ማመቻቸት ሲገባው ያላንዳች ዋስትናና ከለላ ወደ ዩኒቨርሲቲያችሁ በግዴታ ትመለሳላችሁ በማለት ጠያቂም እንዳይኖራቸው አድርጎ አፍኖ ማስቀመጡ ብልህነት የጎደለው ውሳኔ ይመስለኛል። ተማሪዎቹ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስለ ደህንነታቸው የመንግስትን ዋስትና ይሻሉ። ያንን ፕሮቫይድ ማድረግ ደግሞ የመንግስት ስራ ነው። ከዚያ በተረፈ ምግብ እንኳ ከበጎ አድራጊዎች እንዳያልፍ ክልከላ አድርጎ እንደ ጦር ምርኮኛ ከብቦ ማስቀመጥ ፍትሐዊ ያልሆነና የመንግሥትን አምባገነንነት በግልፅ የሚያሳይ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic