>

ማስክ በነጻ- ሰብአዊነት ካለ የእኛም ፋብሪካዎች ይችላሉ!!! (ቅዱስ ማህሉ)

ማስክ በነጻ- ሰብአዊነት ካለ የእኛም ፋብሪካዎች ይችላሉ!!!

ቅዱስ ማህሉ
 
«ባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ
»ኮምቦልቻ ጭርቃ ጨርቅ ፋብሪካ
»አዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ
« አዲግራት ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ
»ናዝሬት/አዳማ(የቱርክ)ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ
»አርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ  እና ሌሎች
ቱርክ እድሚያቸው ከ21 እስከ 64 ላሉት ዜጎቿ በሙሉ በነፍስ ወከፍ 5 አምስት ማስክ በነጻ በየቤቱ በፖስታ ቤት በኩል ማደል ልትጀምር ነው። ኢትዮጵያ ይህን ማድረግ አይከብዳትም። አንዳንድ ከተሞች ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች አሉ። በነዚያ ከተሞች ለሚገኙ ነዋሪዎች የጨርቅ ማስክ አምርተው በነጻ መስጠት ይኖርባቸዋል። ህዝቡ በፎቶው የምታዩትን ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሚወጣ ኬሚካል ተቀባይ ነው። ይህን የምትመለከቱትን ቦታ መርተው ያሳዩኝ ገበሬዎች ናቸው። የኬሚካሉ ጥልቀት ቢያንስ ከሁለት ሜትር ይበልጣል። አካባቢያዊ ብክለቱን አስቡት። ከውሃው ባሻገር ሁሉ አፈር የለበሰው ኬሚካል ነው። በዙሪያው የሚኖሩት ገበሬዎች ብዙ ከብቶቻቸው ይህን ውሃ እየጠጡ ሞተዋል። ኬሚካሉ እንኳን የሰው ቆዳን ከብቶች ሲሻገሩት ቆዳቸውን ግፍፍ አድርጎ የሚያስቀር ነው። በዚህ አካባቢ እና ውሃው በሚወርድበት ስፍራ ያሉ ገበሬዎች እና ልጆቻቸው አብዛኞቹ ቋሚ የቆዳ እና ተያያዥ በሽታ አለባቸው። ታዲያ ሌላው ቢቀር ትምህርት ቤት ባይሰራላቸው፣ ዘመናዊ የግብርና ዕውቀት እንዲያገኙ ባይደረጉ፣ ለሸመቱት ቋሚ በሽታ ካሳ ባይከፈላቸው ወዘተ ይህን ችሎ ለሚኖረው  የአካባቢው ህዝብ  ዛሬ በችግሩ ቀን ሁለት ሁለት የጨርቅ ማስክ እንዴት አምርተው በነጻ ለማደል ያመነታሉ? ይህ በየአካባቢው የብዙ ፋብሪካዎች መገለጫ ነው። እኔም የፋብሪካውን ስም(ይህ ብቻ አይደለም) እና የሰወቹን በደል አሁን ለህዝቡ የሚያደርጉትን ምላሽ አይቼ ወደፊት አወጣዋለሁ። ሁሉም የሚጠበቅበትን ማህበራዊ ሃላፊነት በተግባር ማሳየት አለበት። ይህ ለሚያስከትሉት አካባቢያዊ ጉዳት ካሳ እንዳልሆነ ግን ልብ ሊባል ይገባል።
የጨርቅ ማስክ መታየት ያለበት ቫይረስን ከመከላከል አንጻር ብቻ ሳይሆን ብዙዎቻችችን በሽታውን የምንሸምትበትን እጅን ወደ አፍ፣አፍንጫ እና ዓይነት በመውሰድ የመንካት አባዜ ይቀንስልናል። ይህ ለበሽታው ተጋላጭነታችንን ይቀንስልናል። ከዚያ ባለፈ የጨርቅ ማስክ 50 በመቶ ባክቴሪያ እና አቧራ እንዲሁም ብናኞችን ወደ ውስጥ እንዳንስብ ይከላከልልናል። ይሄም በራሱ ለቫይረሱ ተጋላጭነታችንን በእጅጉ ይቀንሰዋል።የጨርቅ ማስክ ቢያንስ ድርብ ፖሊስተር ቢሆን ይመረጣል።
የቱርኩን በተመለከተ የዜናው ምንጭ ይሄው: https://bit.ly/2xc39Yf
Filed in: Amharic