>
5:18 pm - Thursday February 2, 2023

የኢትዮጵያ ሕክምና ታሪክ  (አቻምየለህ ታምሩ)

የኢትዮጵያ ሕክምና ታሪክ 

 

አቻምየለህ ታምሩ
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና እጀ መድኀኒቱ ሐኪም ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ  የጻፉት «የኢትዮጵያ ሕክምና ታሪክ» ወይም Medical History of Ethiopia መጽሐፍ  በዚህ ወቅት መነበብ ያለበት  ድንቅ የኢትዮጵያ ሕክምና ታሪክ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የኢትዮጵያ የመንግሥት ማዕከል አክሱም ከነበረበት  ዘመን ጀምሮ  እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ  ዘመን ድረስ ኢትዮጵያውያን ወረርሽኝና በሽታ ባጋጠማቸው ቁጥር  እንደምን እንደተቋቋሙት፤  በኢትዮጵያውያን የሕክምና አዋቂዎች ይሰጡ ስለነበሩ ዘመናዊና ባሕላዊ  ሕክምናዎች፤ በተለይም ጎንደር የማዕከላዊው መንግሥት መቀመጫ ሆና ከተቆረቆረች በኋላ በስፋት ይሰጥ ስለነበረው የወሻባ ሕክምናና አይነት፤  የማዕከላዊው መንግሥት መናገሻ እንደገና ወደ ሸዋ በተዛወረበት ወቅት ደግሞ  በወረርሽኝ የተጠቁ ሰዎችን ለማከም በተለም በሸዋ ይደረግ ስለነበረው ሕክምናና  ከሕክምናው በኋላ ተጠቂዎች ወረርሽኙን ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላልፉ እስኪድኑ ድረስ አንፍጫቸውን፣ አፋቸውና ጆሯቸውን እንዲሸፍኑ ይደረግ  ስለነበረው ሕክምና በስፋት ያትታል።
በተለይም ከመካከለኛው ዘመን እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ድረስ  የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች  ለሚከሰት ወረርሽኝና በሽታ ተቋማዊ መፍትሔ ለመስጠት ይወስዷቸው የነበሩ እርምጃዎችና  ያበጇቸው የነበሩ ዘዴዎች አስደናቂዎች ነበሩ። ቀደምቶቻችን ሳንባ ነቀርሳን፣ ስጋደዌን፣ ቂጥኝና ጨብጥን፣  ወባን፣ ኮሌራ፣ ደስታ በሽታና ያጋጥሙ የነበሩ ወረርሽኞችን  ለመከላከል  የቻሉት  በዘመቻ ሳይሆን  ተቋማዊ መፍትሔዎችን  በማበጀትና ተቋማትን በመገንባት ነበር። በዚህ ረገድ Medical History of Ethiopia ጎንደር ዋና ከተማ ሆኖ ከተቋቋመ በኋላ በከተማው ይሰጥ ስለነበረው  የወሸባ  ሕክምናና  አስደናቂ ስለነበረው ተቋማዊ  የሕክምና  አደረጃጀት  ያቀረበውን ታሪክ ማየት ይቻላል።
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን  የተከፈተው  የሐረሩ የስጋ ደዌ  ሕክምና መስጫ ሆስፒታል  የተቋቋመው በአካባቢው ብዙ ሰው በስጋደዌ በመጠቃቱ  በሽታውን በተቋማዊ መንገድ ለመቋቋም መሆኑን መጽሐፉ ይነግረናል። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን  በጎንደር ከተማ  የተቋቋመው የጤና ሳይንስ ኮሌጅም  በጎጃምና በጎንደር አካባቢ ወባ ሰው ስለፈጀ  ወባን  ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመከላከል  የተሰጠ መፍትሔ ነበር። ቀደምቶቻችን የሰጡትን ይህን ተቋማዊ መፍትሔ ያመከነው ወያኔ ነው።  ወያኔ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በጎጃም በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ  በወባ ያለቀው  ቀደምቶቻችን  ወባን  በተቋማዊ መንገድ  ለመከላከልና ለማጥፋት ያቆሟቸውን  የሕክምና ኮሌጁንና ፍኖተ ሰላም የነበረውን የወባ ማጥፊያ ማዕከሉን ዘርፈው በውስጣቸው የነበረውን የሕክምና መስጫ ቁሳቁስ  መርፌ እንኳን ሳያስቀሩ  ወደ ክልላቸው አግዘው ተቋማቱ በመፍረሳቸው ነው።
ባጭሩ መጽሐፉ ቀደምቶቻችን በኖሩበት ዘመን ያጋጠማቸውን ሕዝብን  የጎዳ  ወረርሽኝና በሽታ ለመቋቋም ሲወስዷቸው ስለነበሩ ተቋማዊ መፍትሔዎች ብዙ ቁምነገር ያስጨብጠናል። ከነበረን  የደለበ ተቋማዊ መፍትሔ የመስጠት  ባሕል  ትምህርት ባለመውሰዳችን  የተነሳ ዛሬ ላይ በራችንን ያንኳኳውን ኮሮናን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመቋቋም የተበጀ እዚህ ግባ የሚባል  ተቋማዊ መፍትሔ የለም። አንድ እንኳ ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት ያልቻለው የዐቢይ አሕመድ የአፓርታይድ አገዛዝ መማር ያልቻለው  አምርሮ የሚጠላቸው ቀደምቶቻች ሲወስዱት ከነበረው ተቋማዊ የመፍትሔ አሰጣት ባሕል ብቻ   ሳይሆን ወዳጅ አገር የሚላት ቻይና  አባቶቻችን  ያደረጉትን በማድረግ  በተቋማዊ መንገድ ኮሮናን ከተቋቋመችበት እመርታም ጭምር ነው።
ቀደምቶቻችን ወረርሽኝና በሽታን ለመከላከል ያለፉበትን ተቋማዊ ውጣ ውረድ በተደራጁ የታሪክ ምንጮች ላይ ተመስርተው  በማጥናት  Medical History of Ethiopia   የመሰለ ድንቅ መጽሐፍ ጽፈው የቀደምቶቻችንን ድካም እንድናውቅ  ላደረጉን ለሁለቱ ታላላቅ ፕሮፌሰሮች  ዘላለማዊ  ክብርና ሞገስ ይድረሳቸው!
በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት Medical History of Ethiopia ከሚለው  ድንቅ መጽሐፍ  በተጨማሪ  772 ገጾች ያሉት “Economics History of Ethiopia” እና  371 ገጾችን የያዘ  ”A Social History of Ethiopia” የሚሉ ድንቅ መጽሐፍቶችንም  የጻፉ ሲሆን እናታቸው ታላቋ የኢትዮጵያ አርበኛና  የኢትዮጵያ ድምጽ  የሆኑት  ሲልቪያ ፓንክረስት ደግሞ  ”A Cultural History of  Ethiopia” የሚል ዳጎስ ያለ 746  ገጾች ያሉት  ድንቅ መጽሐፍ  ጽፈዋል። እነዚህን አራት ድንቅ  መጽሐፍት ያላነበበ  ሰው የኢትዮጵያንና  የተቋም ግንባታ  ታሪካችንን  ማወቅ አይቻለውም።   በመሆኑም የኢትዮጵያንና የተቋም  ግንባታ ታሪኳን ለማወቅ የሚሻ  ሰው ቢኖር እነዚህን አራት ድንቅ መጽሐፍት ካሉበት ፈልጎ ያንብብ። የመንፈስ  ምግብ ናቸውና አብዝቶ ያተርፍባቸዋል!
Filed in: Amharic