>

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ዛሬም ትግራይ የርሶ እዳ ነች.....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ዛሬም ትግራይ የርሶ እዳ ነች…..!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ከቀናቶች በፊት የፌደራል መንግስቱ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለቆ የመውጣቱን ዜና ሲሰሙ እጅግ ከደነገጡት ኢትዮጵያዊያን አንዱ መሆኔን ልሸሽግዎ አልችልም። ነገር ግን ከተገረሙት ወገን አይደለሁም። አዎ አልገረመኝም። ምክንያቱም ህውሃት የሰሜን ዕዝን በማጥቃት አገሪቱን ወደ ጦርነት ከዶለበት ጊዜ አንስቶ የእርሶ የህግ ማስከበር ዘመቻ አዋጅ ጭምር ኢትዮጵያን ሁለተኛ አገር የማዋለድ ጥንስስ የመጀመሩ ምልክት አድርጌ ስለወሰድኩት የነገሩ አቅጣጫ ገና በጊዜ ወዴት ሊያደርሰን እንደሚችል በቀላሉ እንድገምት አድርጎኛል። ደጋግሜም ባገኘሁት መድረክ ሁሉ ድምጼን ሳሰማ ይህ ጦርነት እና የምዕራቡ አለም ያደረገብን ከበባ ከአገር ውስጥ አገር የማዋለድን ሂደት ያፋጥነው ይሆናል እንጂ ለኢትዮጵያ አይበጅም የሚል ነበር።
ከቀናቶች በፊት ድንገት ብድግ ብለው ትግራይን፤ እንደ ዱቄት አቡንኛቸዋለሁ፤ ከዛም ከረም ብለው ባሉ መልሰው ዱቴቱን ሽብርተኛ ብለው ለፈረጇቸው የወያኔ ወንጀለኞች አገር አስረክበው የወጡበት መንገድ በብዙ መልኩ በታሪክ ተወቃሽ እና በሕግም ተጠያቂ እንደሚያደርግዎት ለአፍታም ያሰቡበት አይመስለኝም ወይም ጥሩ አማካሪ አላገኙም። ከውሳኔ አሰጣጥዎት እና ለሕዝብ ከገለጿቸው ምክንያቶች ጋር በተያያዘ ያሉኝን እና መሰረታዊ ያልኳቸውን ጥያቄዎች በማንሳት ልጀምር እና ወደ ዋና ቁምነገሬ እገባለሁ።
+ በመጀመሪያ እንዲህ ያለ የአገርን አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ከባድ ውሳኔ ለመወሰን ማን ስልጣን ሰጠዎት? በዚህ ጉዳይ ፓርላማውን ማሳወቅና መምከር አልነበረብዎትም ወይ? ጦርነትም ሲታወጅ፣ ከጦርነትም ሲወጣ እና እንዲህ ያለ እርምጃ ሲወሰድ ፈቃጁ ማነው?
+ እሺ፤ ከሥልጣንዎስ በላይ ሄደው እንዲወስኑ የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጠረ እንበልና ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስቀድመው ወይም እርምጃው በተወሰደ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ወግና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ማሳወቅ አልነበረብዎትም ወይ? ይህን ማድረግ ለሕዝብና ለአገር ያለዎትን ክብር ማሳያ ጥሩ እድል አይደለም ወይ? አለማድረጉስ ከንቀት አይቆጠርም ወይ?
+ ሕዝብ ለሁለት ቀናት በርሶ የድንገተኛ ውሳኔ እንቅልፍ አጥቶ ሲደናበር፣ ሲጨነቅ እና ለተሳሳቱ ተንታኞች የዩቲዩብ ገቢ ሲሳይ ሲሆን እርሶ እንደተለመደው ወሳኝ በሆነ አገራዊ ጉዳይ መግለጫ ለመስጠት ድግስ ወይም የምርቃት ዝግጅት መጠበቅዎ አግባብ ነው ወይ? ለሚያስተዳድሩት ሕዝብ እና አገር ክብር ካለዎት ለምን ይሆን እጅግ አፋጣኝ የመንግስት ማብራሪያ በሚፈልጉ አገራዊ ጉዳዮች ሁሉ እራስዎን ደብቀው እየቆዩ በሌላ የአደባባይ ክስተት እያስታከኩ ማብራሪያ የሚሰጡት? ይሄ አንድ ሥልጡን የሆነ እና በዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ላይ ካለ መሪ የሚጠበቅ ነው ወይ?
ዘግይተውም ቢሆን ትግራይን ለመልቀቅ እንደ ምክንያት የገለጹዋቸውን ነገሮች በተመለከተም በተወሰኑት ላይ ያለኝን ጥያቄ ላንሳ፤
+ አንዱ እና ደጋግመው የሰጡት ምክንያት ሰራዊቱ ከሕውሃት ታጣቂዎች ይልቅ በሕዝቡ በራሱ ጥቃት ደርሶበታል የሚል ነው። ሕውሃት በተለምዶ ሕዝብን እንደ ከለላ እየተጠቀመች ወንጀሎችን እንደምትፈጽም እንኳን እርሶ በነሱ ጉያ ስር ያደጉት እና አብረዋቸው ከጦርነት እስከ ሲቪል አስተዳደር የሰሩ ሰው ይቅር እና እኔ በርቀት የማውቃቸው ሰው ሳይቀር በደንብ የምናውቀው ወያኔ ጥርስ የነቀለችበት ተንኮል ነው። ታዲያ በሕዝቡ መካከል ሰርጋ ገብታ ጥቃቱ የምትፈጽመው እራሷ ወያኔ መሆኗን ስተውት ነው ወይ?
+ ከላይ በጠቀሱት ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ለጦራችን ደጀን መሆን ስላልፈለገ ደጀን ወደሚሆነን ሕዝብ ሸሽተናል የሚል ምክንያት ገልጸዋል። እራሱን መከላከል ያልቻለ፣ ለዘመናት በሕውሃት ምርኮ ተይዞ የኖረ፣ በየቤቱ አንዳንድ የህውሃት ሰላይ ባለበት፣ እርሶ የሰየሙት ጊዜያዊ አስተዳደር ሹሞች እኳ በየሜዳው በህውሃት ሰርጎ ገቦች ሲገደሉ ያየ፣ ልጁ፣ ሚስቱ፣ ህጻናት እና አሮጊቶች በሻቢያ ወታደሮች ሲደፈሩ ያየ፣ በጦርነቱ ቅስሙ የተሰበረ፣ ቤት ንብረቱ የወደመና የተዘረፈ፣ በርሃብ አለንጋ የተጠበሰ ሕዝብ በምን አቅሙ ነው ለእርሶ ደጀን ሊሆንዎት የሚችለው? ከእርሶ ጋር የወገኑ ሰዎች በየቀኑ ደጃፉ ላይ ሲደፉ የሚያይ ሰው እንዴት ደፍሮ ከርሶ ጋር አብሮ ሊቆም ይችላል?
+ ከላይ ያሉትን ሁለት ምክንያቶች አያይዘው ለትግራይ ሕዝብ ‘የጥሞና ጊዜ’ ልስጠው ብዮ ነው ጦሩን ያስወጣሁት ብለዋል። ይህ አባባልዎ ለእኔ የገባኝ ሁለት ነገር ነው፤ አንደኛ በሕዝቡ መካከል ሰርገው ገብተው ጦሩን የሚያጠቁ ሰዎችን የሕዝቡ አካል አድርጎ በማየት የትግራይ ሕዝብ ከእኔ ይልቅ ወያኔን መርጧል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስዎትን እና ከዚህም በመነሳት የትግራይ ሕዝብ ህውሃትን ከመረጠ እስኪ ማን እንደሚያዋጣው ከሚገጥመው መከራ እና ስቃይ አይቶ ይወስን የሚል ነው። ይህ አገላለጽዎት በነገራችን ላይ የኮ/ል መንግስቱ ንግግር፤ ‘ወርቅ ሲያነጥፉለት ፋንድያ …’ ከምትለዋ ጋር ተመሳስላብኛለች። ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታን በቅጡ ለገመገመ ሰው ሕዝቡ የመከላከያ ደጀን ይሆናል ብሎ መገመት ይቻላል ወይ? ደጀንስ ባይሆን ይገርማል ወይ? ሕዝቡ ደጀን አልሆነም ተብሎ የሚወሰደው እርምጃ ክልልን ሽብርተኛ ለተባለ ቡድን ለቆ መውጣት ላይ ያደርሳል ወይ? በክልሉ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ እና ለጦሩ የወገኑ፣ ከጊዜያዊው አስተዳደር ጋር ተባብረው ሲሰሩ የቆዩ ሰዎች እጣ ፈንታስ ታስቦበታል ወይ? ሕዝብን በመከራ መፈታተንስ አግባብ ነው ወይ?
+ አንድ መንግስት በጦርነት እየታመሰ ባለ ክልል ውስጥ ሕዝብ ደጀን አልሆነኝም በሚል ድፍን ምክንያት ክልሉን እና ሕዝቡን ሽብርተኛ ብሎ ለፈረጀው አካል አሳልፎ ይሰጣል ወይ? ይሄ ውሳኔ ህውሃትና የአለም አቀፍ ኃይሎች ክልሉን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ለሚያደርጉት የተቀናጀ እንቅስቃሴ መንገዱን ማመቻቸት አይደለም ወይ?
+ የትግራይ ሕዝብ ደጀን ስላልሆነን ደጀን ወደሚሆነን ሕዝብ ሸሽተናል የሚልው ጥቅል ፍረጃስ በእርሶ ደረጃ ካለ እና ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት ከተሸከመ መሪ የሚጠበቅ ነው ወይ? ይህ አገላለጽ ለዘመናት ተቻችሎ፣ ተሳስቦ እና ተዋህዶ ይኖር በነበረው በትግራይ እና በአማራ፤ በትግራይ እና በአፋር ሕዝብ መካከል ሌላ የእድሜ ልክ ቁርሾ እና ጠባሳ አይፈጥርም ወይ?
+ የትግራይ ሕዝብ ደጀን ያልሆነዎት ለምን እንደሆነ አውቆ ችግሩን መቅረፍ ይሻላል ወይስ ደጀን ስላልሆንከኝ ብሎ ለወያኔ ሽብርተኛ ቡድኖች ሕዝቡ አሳልፎ መስጠት? ያ ሕዝብ ለምን ይሆን ደጀን ያልሆንዎት? ለምን ይሆን ከመንግስት ጦር ይልቅ ለሽብርተኞች ምሽግ የሆነው? ለምን ይሆን እንዲያ ጦርነቱ ተጠናቋል ባሉበት ጊዜ መቀሌ ሄደው ባደረጉት ንግግር ያሞካሹት የትግራይ ሕዝብ እንዲህ በወራት ጊዜ ውስጥ ከጦሩ በተቃራኒ የቆመው?
+ ሌላው በአደባባይ ዲስኩርዎ ያነሱት ነገር የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና ነው። አዎ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ከልክ ያለፈ ጫና ፈጥሮብዎታል። ይሁንና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ደጋግሞ ያነሳው ጥያቄ የኤርትራ እና የአማራ ልዩ ኃይል ከክልሉ ይውጣ የሚል ነው እንጂ የአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ይውጣ የሚል አይደለም። ስለዚህ ጦሩን ከሁሉም ክልሎች በተወጣጣይ ልዩ ኃይሎች እንዲደገፍ እና በሕዝብ መካከል ተሸሽገው ከሚያጠቁት የወያኔ ሰርጎ ገቦች መታደግ ይሻላል ወይስ የልጅ ኩርፊያ በሚመስል መልኩ ከዚህ ሁሉ መስዋዕትነት በኋላ ጦሩ እንደገና ሙሉ በሙሉ ክልሉን ጥሎ እንዲወጣ ማድረግ? ይሄ ሁኔታ ወያኔ እንደገና እንድታንሰራራ እና አንዳዶች በማህበራዊ ድህረ ገጽ፤ እርሶ አየር ላይ የበተኑት ዱቄት አንባሻ ሆኖ መጣ፤ እያሉ እንደሚያሽሟጥጡት ህውሃት እንዲፈረጥም አያደርገውም ወይ? ይሄ ደግሞ እያደር ሽብርተኛ የተባለው አካል ትግራይን አንድም በድርድር አለያም በፍልሚያ ገንጥሎ አገር ለማድረግ ለሚያረገው የሞት ሽረት ትንቅንቅ የእርሶ ውሳኔ ለወያኔ የተበረከተ ትልቅ ገጸ በረከት አይደለም ወይ?
+ ነገ ደግሞ ሃሳብዎትን ቀይረው ትግራይን መቆጣጠር ቢፈልጉ ደም ተገብሮበት ለተያዘ መሬት እንደገና ሌላ አዲስ ጦርነት የግድ አይልም ወይ? ይች አገር እንዲህ ያሉ እና የልጅ ጨዋታ የመሰሉ ነገር ግን ትልቅ የሕይወት እና የገንዘብ ዋጋ የሚያስከፍሉ ጦርነቶችን ለማካሄድ የቀራት አቅምስ አለው ወይ?
+ ሌላው አስደማሚ ነገር የተናገሩት፤ ብዙ አሳሳቢ የሆኑ እና ሊደርሱ የተቃረቡ አደጋዎች አገሪቷን ስለከበቧት ለዛ የሚሆን ኃይል ለማደራጀት ጦሩን ከትግራይ ማስወጣት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ይሄ ግምገማዎን ለሕዝቡ በዝርዝር ቢያስረዱ ጥሩ ነበር። ለመሆኑ ትግራይ ላይ ካለው ችግር የከፋ አደጋ በአሁን ሰዓት አለ ወይ? ካለም ሊኖር የሚችለው ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘው ነው። እሱ ደግሞ በራሱ ትግራይ ላይ ካለው ችግር ጋር እየተያያዘ መጥቷል። ግብጽ እና ሱዳን፤ ወያኔን እና ሌሎች የአገር ውስጥ ታጣቂ ኃይሎችን እየደገፉ ኢትዮጵያን የማዳከም ሥራ እየሰሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ ከመንግስትዎ ጭምር ሲገለጽ ነበር። ስለዚህ ትግራይ ላይ ያለው ችግር ለሌሎቹ እርሶ በዝርዝር ላልገለጿቸው ችግሮች እንደ አንድ እና ዋና መንስዔ የሚቆጠር ከሆነ፤ ችግሩን ተጋፍጦ ትግራይን ማረጋጋት ሌሎቹን አደጋዎች ለመከላከልስ ፋይዳ የለውም ወይ?
+ መንግስት በትግራይ ውስጥ ለሚኖሩ ሌሎች የማህበረሰ ክፍሎች፣ በተለይም መንግስትን ተማምነው ለሥራ እና ለትምህርት ወደ ክልሉ የሄዱ ሰዎች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ቅድመ ዝግጅት ሳያደርግ በዚህ መልኩ ክልሉን ለሽብርተኛው ቡድን ለቆ መውጣቱስ ለምን አልታሰበበትም? በእነዚህ ሰዎች ላይ ለሚደርሰው ማናቸው ጉዳት ማነው ተጠያቂው? በእኔ እምነት እርሶ ራስዎ ይመስሉኛል።
+ ሌላው በእርሶም ሆነ በሌሎች የመንግስት ኃላፊዎች ሲገለጽ የተሰማው እና በምንም መልኩ በአገሪቱ ሕገ መንግስትም ሆነ በአለም አቀፍ ሕጎች ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ጦሩ ጥሎ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ውስጥ ለሚደርስ የሰብአዊ መብት ጥሰትም ሆነ ሰብአዊ ቀውስ መንግስት ኃላፊነት የለበትም የሚለው ነው። ይህ የመንግስት አቋም እጅግ ስህተት እና ምንም የሕግ መሰረትም ሆነ የፖለቲካ አመክኒዮ የሌለው መሆኑን አበክሬ ልገልጽልዎ እወዳለሁ። አዎ ትግራይ ውስጥ ዛሬ በንጹሐን ዜጎች ላይ ለሚደርሰው ማናቸውን ጥቃትም ሆነ ስቃይ፤ ወንጀሉን ፈጻሚው አሸባሪው ወያኔ ብቻ ሳይሆን ሕዝዎን ከጥቃት መታደግ ያልቻሉት እርሶ እና አስተዳደርዎ በቀጥታ ተጠያቂዎች ናችሁ። አንድ መንግስት የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍሎ ሕዝቡን እና ግዛቱን ከአሸባሪ ኃይል እጅ ነጻ ያወጣል፣ ነጻ ለማውጣት ቁጭ ብሎ ይደራደራል እንጂ ደጀን ስላልሆንከኝ ሥራህ ያውጣህ፣ ኃላፊነትም የለብኝም ብሎ ሜዳ ላይ በትኖ ይቀመጣል ወይ?
+ ይህ እርምጃዎትስ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ጣልቃ ገብነት የበለጠ እንዲጨምር እና ምናልባትም መልኩን እንዲቀይር አያደርገውም ወይ? እርሶ እኔ መቆጣጠር አቅቶኛል ያሉትን ክልል አለም አቀፍ ማህበረሰቡ የሰላም አስከባሪ ጦር ላስገባ ካለ የአገሪቱ ህልውና ይበልጥ አደጋ ላይ አይወድቅም ወይ? ነው ወይስ ለቀው መውጣትዎ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ‘ክልሉን ተረከቡኝ እና የምታደርጉትን አድርጉ’፤ በሚል እንደቀረበ ጥሪ እንቁጠረው? እንዲያ ከሆነ ገና በጊዜ ጦርነቱ እንደተጀመረ ጣልቃ ገብነታችሁን አቁሙ በሚል የሰጡትን እና ወቅጣን ሳይጠብቅ ያሰሙትን የተቃዎሞ ድምጽ አሁን በተዘዋዋሪ ግብዣ የሃሳብ መቀየር አይሆንም ወይ?
ጥያቄዎቼን እዚህ ላይ ልግታና መልዕክቴን ልደምድም።
የፌዴራል መንግስቱ ጦር ትግራይን ለቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ መስጠትዎን ተከትሎ የደነገጠው ኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ቆየት ብለው በሰጡት እና ለእኔ መያዣ መጨበጫ ባጣሁለት የድግስ ላይ መግለጫ የተረጋጋ ይመስላል። ለእኔ ግን እንደ ምክንያት አድርገው የዘረዘሩዋቸው ነገሮች ይበልጥ እንድሰጋ እና የፖለቲካ ምሪትዎም የበለጠ አደጋ ውስጥ እንደወደቀ ነው የተሰማኝ። ትግራይን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደ አገር ወደ መጥፎ አቅጣጫ ይዞ እየሄደ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ስላሳየኝ መጪውን ጊዜ ይበልጥ እንድፈራና እንድሰጋ አድርጎኛል። ከዚህ ውሳኔዎት ተነስቼ ኢትዮጵያ በዚህ እጅግ ፈታኝ ወቅት ብልህ፣ አርቆ ተመልካች፣ አስተዋይ፣ ቆራጥ እና ለሁሉም ወገኖቹ እኩል የሚቆረቆር መሪ ገና አላገኘችም ብዮ ባስብ እንደማይቀየሙኝ ተስፋ አደርጋለሁ።
ለማንኛውም የትግራይ ነገር ለጊዜው ከአፍ ያመለጠ አፋፍ አይነት ነገር የሆነ ይመስላል። እርግጥ ነው ትግራይ ውስጥ ሆነው እና በወያኔ በኩል እየተተኮሰ የአንድ ወገን ውጊያ ማቆም ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም። ወያኔ ተኩሱን ስላላቆመ ክልሉን ሽብርተኛ ላሉት ቡድን ለቆ መውጣትም መፍትሔ አይሆንም። ያለም አቀፉን ማህበረሰብ ጫና ለመመልስ ሲባል ተኩስ አቁሙ ከተባልን ክልሉን ለቀን እንውጣ ማለት እንደኔ በቅጡ ያልታሰበበት ክፉና የተሳሳተ የፖለቲካ ውሳኔ ነው። ከዛ ይልቅ መንግስት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተኩስ አቁም ምክሩን እንደሚቀበል እና ያለውን ኃይሉን ወደ ከተሞች አሰባስቦ ሰርጎ ገቦቹን ቢቆጣጠር እና በተመሳሳይ ወያኔም ባለበት ጫካ ውስጥ ሆኑ ውሳኔውን እንዲቀበል ጫና ያደርግ ዘንድ እዳውን ወደ አለም አቀፉ ማህበረሰብ መልሶ መወርወር ይቻል ነበር። ያልተጠበቀው የመንግስት ክልሉን ለቆ የመውጣት ውስኔ ግን የወያኔን የመደራደር አቅም ከተኩስ አቁም ወደ አገር የመፍጠር ደረጃ ከፍ እንዲል አድርጎታል። ከዱቄትም ወደ አንባሻ፤ ከአሸባሪም ወደ ክልል አስተዳዳሪ ቀይሮታል።
ጽሁፌን በክልሉ ካለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ጋር አያይዤ መደምደም ወደድኩ። መንግስት ክልሉን ጥዬ ስለወጣሁ ከዚህ በኋላ ትግራይ ውስጥ የሚፈጸሙ የመብት እረገጣዎችንም ሆኑ ሰብአዊ ቀውሶች አይመለከቱኝም፤ ከደሙ ነጻ ነኝ የሚለው አቋሙ ከተጠያቂነት የማያድነው መሆኑን አበክሬ ለመግለጽ እወዳለሁ። አዎ፤ ዛሬ ትግራይ ውስጥ ለሚፈጸመው ሰቆቃ ወያኔ ብቻ ሳይሆን የእርሶም አስተዳደር በእኩል ተጠያቂ ነው፡፡ አሁንም በድርድርም ቢሆን በክልሉ ውስጥ ለጥቃት ተጋላጭ  የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመታደግ ኃላፊነት የእርሶ አስተዳደር ላይ መውደቁን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እና የመብት ተሟጋች ላሳስብዎ እወዳለሁ።
ይህን ኃላፊነትዎን እንዲወጡ ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን እንዲሳካልዎትም እመኛለሁ። ይህን ካደረጉ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎንዎ እንደሚቆም ተስፋ አደርጋለሁ።
ከታላቅ አክብሮት ጋር
Filed in: Amharic