>

‹‹ በወጣቶች ላይ የተፈጠረው የአገር ፍቅር ስሜት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ለሚፈልጉ አገራት መልዕክት አለው...!!!››  (አቶ ጌታቸው በለጠ)

‹‹ በወጣቶች ላይ የተፈጠረው የአገር ፍቅር ስሜት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ለሚፈልጉ አገራት መልዕክት አለው…!!!›› 
አቶ ጌታቸው በለጠ የቀድሞው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት
(ኢ ፕ ድ)ዋለልኝ አየለ

አዲስ አበባ፡- አገራዊ ችግር ባጋጠመበት በዚህ ወቅት በወጣቶች ላይ የታየው የአገር ፍቅር ስሜት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ለሚፈልጉ አገራት መልዕክት እንዳለው የቀድሞው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ጌታቸው በለጠ አስታወቁ።

አቶ ጌታቸው በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በወጣቶች ላይ ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ታይቷል። አገራቸውን ከጥፋት ለማዳን ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቅለዋል። ይህም ባለፉት ሦስት ዓመታት በታየው ፖለቲካዊ ለውጥ የመጣ የአገር ፍቅር ስሜት ነው።

የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ሲሉ የነበሩ አገራት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ብቻ ክህደት ፈጽመዋል ያሉት አቶ ጌታቸው ፣ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሚያሴሩበት ወቅት ይህ የወጣቱ ስሜት ትልቅ መልዕክት አለው። ኢትዮጵያ የውስጥ አንድነት ያላት መሆኗን ማወቃቸው ሴራቸው እንደከሸፈ እንዲያውቁት ያደርጋል ብለዋል።

‹‹ከዚህ በፊት የነበሩ የጦርነት ታሪኮቻችንም የሚያሳዩት ወጣቶች ለአገራቸው የከፈሉትን ዋጋ ነው›› ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ኢትዮጵያ አደጋ ባጋጠማት ቁጥር ከጫፍ እስከ ጫፍ በመዝመት የሚታደጓት ወጣቶች መኖራቸው በታሪክ የተሰነደ ነው፤ የአሁኑ ዘመቻም አገርን ከጥፋት የማዳን ደማቅ ታሪክ ሆኖ የሚቀመጥ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት ከነበሩ የጦርነት ታሪኮች መረዳት የሚቻለው አገራዊ አደጋ ውስጥ በወደቀችበት ሰዓቱ ህዝቦቿ ልዩነቶችን ሁሉ ወደጎን ትተው አንድ እንደሚሆኑ ነው ፤ በ1969 ዓ.ም በነበረው የሶማሊያ ወረራ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ የፖለቲካ ልዩነት ነበር፤ ሶማሊያ ኢትዮጵያን ወረረች ሲባል ግን ሁሉም በአንድነት አገርን ለማዳን መስዋዕት እንደሆኑ ጠቁመዋል።

‹‹በአግባቡም ይሁን ያለ አግባብ ወጣቶችን ስንወቅሳቸው ነበር›› ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ከለውጡ በፊት በነበረው ሥርዓት ወጣቶች በሱስና በብዙ ነገሮች ስለአገር እንዳያስቡ የተደረጉበት ስለነበር ለወቀሳ ዳርጓቸዋል፤ ሱሰኛና ለአገር ግደለሽ እየተባሉ ሲወቀሱ ቆይተዋል፤ ዛሬ ግን ያ አመለካከት ተቀይሯል ብለዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ ይህ የተፈጠረው የወጣቶች ስሜት የሚያሳየው ወጣቱ አሁን ባለው ሥርዓት ላይ እምነት ያለው መሆኑን ነው።

‹‹ወጣቶች በመኪና ላይ ተጭነው እየዘመሩ በደስታ ሲሄዱ በዓይኔ አይቻለሁ፤ ጦርነት፣ ሞት ያለበት ነው፣ ወደ ሞት ሲሄዱ ነው እየዘመሩና እየተደሰቱ የሚሄዱት፤ በየትም አገር እንዲህ ዓይነት የአገር ስሜት አለ ብዬ አላምንም›› ብለዋል።

ይህ የሚያሳየው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የማይደራደርና የአገር ፍቅር ስሜት ያለው ወጣት መፈጠሩን አመላካች እንደሆነም አመልክተዋል።

Filed in: Amharic