>
5:14 pm - Tuesday April 30, 2576

የንጉሥ ልደት ሲታሰብ...!!! (ዙኪ ሸዋ)

የንጉሥ ልደት ሲታሰብ…!!!

ዙኪ ሸዋ

*….  “…ምኒልክ በሚል ስም የሚነግስ ንጉስ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታል….” የሚል ትንቢት ነበረ። ሣህለ ሥላሴ ሲነግሱ “…ስሜ ምኒልክ ይሁን…” ብለው ነበረ። ምኒልክ በሚል ስም ሣህለ ሥላሴ ለምን እንዳልነገሱ ክብረ ነገስት ውስጥ ብንመለከት “….የሸዋው ንጉስ ሣህለ ሥላሴ በሚባል ስም ሲነግሱ አንድ መነኩሴ “…….በዚህ ስም አትንገስ ፣ መጥፎ አጋጣሚ ያመጣብሃል ፣ ይህ ስም የሚስማማው ከመጀመሪያው ወንድ ልጅህ ከኃይለ መለኮት ለሚወለደው ነው ። ይህም ስም የሚወጣለት የልጅ ልጅህ ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ ትልቅ ንጉስ ይሆናል…..” አላቸው ይላል
የምኒልክ እናት ወይዘሮ እጅጋየሁ የንጉስ ሣህለ ሥላሴ ሚስት የወይዘሮ በዛብሽ ገረድና የልጆች ሞግዚት ነበሩ፡፡ እጅጋሁ የግርድና ስራ የጀመሩት በንጉስ ሣህለ ሥላሴ ቤት አልነበረም፡፡ ንጉስ ሣህለ ሥላሴ ቤት ከመቀጠራቸው በፊት የአንኮበር ቤተ ክርስቲያን አለቃ የነበሩት የመምህር “…ምላት…” ገረድ ነበሩ፡፡ በአለቃ ምላት ቤት ግርድና ተቀጥረው ሳለ አንድ ቀን ጠዋት ለጓደኞቻቸው “…..ዛሬ ማታ በሕልሜ ከብልቴ ፀሃይ ስትወጣ አየሁ….” ብለው ተናገሩ፡፡ ስራ ቤቶች የሰሙት ወሬ መዛመቱ አይቀርምና ወሬው ከጌትየው ከአለቃ ምላት ዘንድ ደረሰ፡፡ አለቃ ምላትም “….እንግዲያው ይህ ከሆነ ወደ ላይ ቤት ትሂድ!…” አሉ፡፡ የላይ ቤት የሚባለው የአንኮበሩ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤተ መንግሰት ከኮረብታ ላይ በመሆኑ አገሬው በተለምዶ “ላይ ቤት” ይለዋል፡፡
 እጅጋየሁ እንደተመከሩት ከንጉስ ሣህለ ሥላሴ ቤት ሄደው ተቀጠሩ፡፡ የእጅጋየሁ የህልም ወሬ ተዛምቶ ንጉስ ሣህለ ሥላሴ ቤትም ገብቶ ስለነበረ የንጉስ ሣህለ ሥላሴ ባለቤት ወይዘሮ በዛብሽ ያ የታየው ፀሃይ ከልጃቸው እንዲወለድ ፈለጉ፡፡ ወይዘሮ በዛብሽ ከልጆቻቸው ሁሉ አብልጠው ሰይፉ ሣህለ ሥላሴን ይወዱታል፡፡ ስለዚህ ሰይፉ ከእጅጋየሁ ልጅ እንዲወልድ ማታ አጅጋየሁን ወደሰይፉ መኝታ ቤት ልከው ያን ጎረምሳ እንድትጠብቅ አደረጉ።
 የልጅ ሰይፉ እሽከሮች የእጅጋየሁን መላክ እንዳወቁ ለጌታቸው ለልጅ ሰይፉ ተናገሩ። ሰይፉ ሌላ የሚወዳት ሴት አለችው። የአዲሲቱን እጅጋየሁ መምጣት እንደሰማ ተናዶ እንዳያባርራትም እናቱን ፈርቶ ከወንድሙ ከኃይለ መለኮት ዘንድ ሄዶ ….“እባክህ ሌላ ሴት ከሌለህ እሜቴ የላኩዋትን ያቺን ገረድ ውሰድልኝ”….አለ። ኃይለ መለኮትም እሺ ብሎ ከእጅጋየሁ ጋር ባደረጉት ግኑኝነት ልጅ ተፀነሰ።እናትዬውም ወይዘሮ በዛብሽ የእጅጋየሁን መፀነስ እንዳዩ ከሰይፉ ያረገዘች መስሎአቸው ተደሰቱ። በኋላ ግን ከሌላው ልጃቸው ከኃይለ መለኮት ማርገዟን ሲሰሙ ተናደው እጅጋየሁን በእግር ብረት አሰሯት። ቆይቶም በአማላጆች ተፈታች። ንጉስ ሣህለ ሥላሴ ይህን ወሬ ሰሙ። ልጃቸው የንጉስ ልጅ ሆኖ ገረድ በማፀነሱ ተናድው ወሬው እንዳይሰማ እጅጋየሁን ከርስታቸው “አንጎለላ” ላይ ሄዳ እንድትቀመጥ አደረጉ። እጅጋየሁ አንጎላላ ከሚባለው አገር እንዳለች ወንድ ልጅ ወለደች። የእጅጋየሁን መውለድ ንጉስ ሣህለ ሥላሤ ሲሰሙ የልጁን ስም “….ምን ይልህ ሸዋ….” ብለው ስም አወጡ። ምን ይልህ ሸዋ ያሉበት ምክንያት የኔ ልጅ ከገረድ በመውለዱ “…..ሸዋ ምን ይልህ ይሆን?….” ለማለት ነው። በኋላ ግን በህልማቸው ከምን ይልህ ሸዋ ጋር አብረው ቆመው ከእሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረዝሞ አዩ። ይህን ህልም ካዩ በኋላ “….ምኒሊክ የኔ ስም አይደለም። የሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉት…” ብለው አዘዙ። እዚህ ላይ ንጉስ ሣህለሥላሴ “…..ምኒልክ የኔ ስም አይደለም የእርሱ ነው….” ያሉት በጥንት ጊዜ “…ምኒልክ በሚል ስም የሚነግስ ንጉስ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታል….” የሚል ትንቢት ነበረ። ሣህለ ሥላሴ ሲነግሱ “…ስሜ ምኒልክ ይሁን…” ብለው ነበረ። ምኒልክ በሚል ስም ሣህለ ሥላሴ ለምን እንዳልነገሱ ክብረ ነገስት ውስጥ ብንመለከት “….የሸዋው ንጉስ ሣህለ ሥላሴ በሚባል ስም ሲነግሱ አንድ መነኩሴ “…….በዚህ ስም አትንገስ ፣ መጥፎ አጋጣሚ ያመጣብሃል ፣ ይህ ስም የሚስማማው ከመጀመሪያው ወንድ ልጅህ ከኃይለ መለኮት ለሚወለደው ነው ። ይህም ስም የሚወጣለት የልጅ ልጅህ ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ ትልቅ ንጉስ ይሆናል…..” አላቸው ይላል። ስለዚህ ነው የልጁን ስም ምኒልክ ያሉት። ይሄው ከድሃ መወለድ በዘመኑ እንደ ነውር ተቆጥሮ ምኒልክ በሣህለ ሥላሴ ቤተ መንግስት ውስጥ እንዳያድጉ ተደርጓል። ፀሐፊ ትእዛዝ ገብረ ሥላሤ ከፃፉት ብጠቅስ “….ስለ ህዝብ እረፍትና ጤና የተወለደው ምኒልክ በአንጎለላ መቅደላ ኪዳነ ምህረት ክርስትና ተነስቶ ጠምቄ በሚባል አገር በሞገዚት አኖሩት….”
Filed in: Amharic