>

«ዛሬ ጫና ፈጣሪ ነን የሚሉ አገራት እየተሳሳቱ ያሉት ታሪክን በአግባቡ ባለማወቃቸው ነው...!!!» ( ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌዴሌቦ፣ የታሪክ ተመራማሪ)

«ዛሬ ጫና ፈጣሪ ነን የሚሉ አገራት እየተሳሳቱ ያሉት ታሪክን በአግባቡ ባለማወቃቸው ነው…!!!»
 – ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌዴሌቦ፣ የታሪክ ተመራማሪ
(ኢ ፕ ድ) 

ዛሬ ላይ ጫና ፈጣሪ ነን የሚሉ አገራት ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ከመሆኗም በተጨማሪ የምታደርገውን ጠንቅቃ የምታውቅ፣ በየዘመኑ የተነሱባትን ጠላቶች አሳፍራ የመመለስ ታሪክ ያላት አገር የመሆኗን ታሪክ በአግባቡ ባለማወቃቸው ምክንያት እየሳቱ ናቸው ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌዴሌቦ ገለጹ፡፡
ፕሮፌሰር ላጲሶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ከመሆኗም በተጨማሪ የምታደርገውን ጠንቅቃ የምታውቅ አገር ነች፡፡ በየዘመኑ የተነሱባትን ጠላቶችም አሳፍራ የመመለስ እንጂ የሽንፈትና የተላላኪነት ታሪክ ያላት አገር አይደለችም፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን ላይ ጫና ፈጣሪ ነን የሚሉ አገራት እየተሳሳቱ ያሉት ታሪክን በአግባቡ ባለማወቃቸው ነው፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ላጲሶ ገለጻ፤ የአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ኃይል ግዛቴን አላስደፍርም በሚል ተጋድሎ ያደረጉበትና ድንቅ ድል ያስመዘገቡበት ህያው ምስክር ነው፡፡ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር የአሸባሪው ህወሓት እና ጀሌዎቹን ህልውና በማቆየት የራስን ፍላጎት ለማሳካት የሚደረገው ያልተገባ ጫናም ይሄን ታሪክ ካለመገንዘብ የሚመነጭ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የአልደፈርና አልበገር ባይነት የታሪክ ገጽ የሚነበበው ድል አድራጊነት ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ላጲሶ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በባህሪው መገዛትን የማያውቅ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም የቋንቋ ብዛት ሳይለየው ለሚመጣው ነገር ሁሉ የሚተባበር፣ በህብረት ቆሞም ድል የሚያደርግ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
በየትኛውም ዘመን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ለማንም ተገዝቶ ካለማወቁም በላይ ስለ አፍሪካ ነፃነትና አንድነት የሚያቀነቅን መሆኑን በማውሳትም፤ የአጼ ኃይለሥላሴ አፍሪካን አንድ አድርገው ያስተባበሩበትን አካሄድ ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ። በዚህ ተግባራቸውም የኢትዮጵያ ነገስታትና መሪዎች በየትኛውም መልክ ጠላት ኢትዮጵያን ለመድፈር በተነሳ ጊዜ የየራሳቸውን ተጋሎ ፈጽመው የዛሬዋን ኢትዮጵያ ለትውልድ ያቆዩ፤ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ያሉትም ኢትዮጵያውያንን አንድ ለማድረግና ለማስተባበር ተነስተው ለዓላማቸው እስከመሰዋት የደረሱ ስለመሆናቸውም ያስረዳሉ።
ዛሬ ላይ በሽብር ተግባር ላይ የተሰማራው ህወሓት ቀደም ሲልም ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲወጋ እንደነበር ያስታወሱት ፕሮፌሰር ላጲሶ፤ ወደሥልጣን የወጣውም በአሜሪካን መንግሥት ድጋፍ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
Filed in: Amharic