>
5:26 pm - Sunday September 15, 9675

በፖለቲካ እብደት ወደ ገደል የተገፋች አገር፤ እየተንደረደርን ከምንወርድበት ቁልቁለት ማን ያስቆመን ይሆን...??? (ያሬድ ሀይለማርያም

በፖለቲካ እብደት ወደ ገደል የተገፋች አገር፤ እየተንደረደርን ከምንወርድበት ቁልቁለት ማን ያስቆመን ይሆን…???

ያሬድ ሀይለማርያም

“Political madness is the worst of all form of madness.” Bamigboye Olurotimi
የፖለቲካ እብደት የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት አደጋ ላይ ከመጣል እና ዜጎቿንም ለቀጣይ ስቃይ ከመዳረግም አልፎ  ህልውናዋን አደጋ ላይ ጥሎታል። ፖለቲካችን ጤና ካጣ ብዙ አሥርት አመታት ቢቆጠሩም ጥሩ ሐኪም ማግኘት ባለመቻሉ ወደ ለየለት የፖለቲካ እብደት አምርቷል። የእብደት ፖለቲካ ደግሞ አገር ያፈርሳል፣ ትውልድ ያመክናል፣ ዜጎችን እርስ በርስ ያጫርሳል፣ ሚሊዮኖችን የኑሮ ዋስትና ያሳጣል፣ ዲሞክራሲን ያቀጭጫል፣ ፍትሕን ያዛባል፣ ዜጎችን ያንጓልላል፣ አገር በክህደት ቁልቁለት ተንከባላ እንድትንኮታኮት መንገዱን ይጠርጋል። ኢትዮጵያ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለባት እና የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላት አገር ብትሆንም እብደት በተጠናወታቸው የቀነጨሩ ፖለቲከኞች ህልውናዋ የከፋ አደጋ ላይ ውድቋል። በረዥም ታሪኳ ውስጥም ከጥፋት አፋፍ እየደረሰች የተመለሰችበት አጋጣሚዎች ብዙ ቢሆንም የዛሬው ግን እጅግ የከፋ ይመስላል።
ፖለቲከኞቻችን ከእብደታቸው መለስ ብለው አገርን እና ሕዝብን ቢያስቡ መልካም ነበር። የተደላደለ የፖለቲካ ምህዳር እና ዲሞክራሲ በሰፈነበት አገር የፖለቲከኞች እብደት በጦፈ ውይይት፣ ክርክር እና አንዳንዴም ትኩሳቱ ከፍ ሲል እስከ ስም መጠፋፋት ይደርሳል። በምንም ተአምር ግን ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት አይዘልቅም። የዲሞክራሲ ድርቅ ክፉኛ በመታው እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ደግሞ በፖለቲካ እብደት ውስጥ ውይይት፣ ድርድር፣ መቻቻል፣ ተጠያቂነት፣ ሕዝብና አገርን ማስቀደም የመሳሰሉ ቀና እሳቤዎች እብደት ለተጠናወታቸው ፖለቲከኞች እንደ ሽንፈት ስለሚቆጠሩ ቦታ አይኖራቸውም። ሁሉም የእውነት እና የጽድቅ መንገድ እኔው ብቻ ነኝ ብሎ ስለሚያስብ መጨረሻው አካላዊ ግጭት ነው። ታሪካችን ከዚህ የክሽፈት መንገድ ጸድቶ አያውቅም።  ዛሬም እብደት በተጠናወታቸው ፖለቲከኞች ሳቢያ ዜጎች በየጥሻው እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት፣ ሴቶች እና አዛውንቶች ከቅያቸው ተፈናቅለው በየዱሩ እየማቀቁ ነው። ብዙ ሺዎች ቤትና ንብረታቸውን አጥተዋል። ሴቶች ተደፍረዋል። ተቋማት እየወደሙ ነው። ዛሬም እንደ ትላንቱ ሕጻናት እና ታዳጊ ወጣቶች በሁሉም ግንባር ተሰልፈው እርስ በርስ እየተፋለሙ ነው። የኢትዮጵያ እናቶች ልክ በደርግ ጊዜ እንደሆነው ሁሉ አገር ለማዳን ሲባል ልጆቻቸውን ለሰሜን አሞራዎች አሳልፈው ሰጥተዋል።
የፖለቲከኞች እብደት ኢትዮጵያን እንደገና ማባሪያ ወደሌለው የጦርነት አዙሪት እየዶላት ነው። እርግጥ ነው፤ አይናችን እያየ እና ጆሯችን እየሰማ ‘ኢትዮጵያን ለመበተን ሲኦልም ቢሆን እንገባለን’ የሚሉ እብድ ፖለቲከኞች ለሦስት አሥርት አመታት ግድም ያስተዳድሯት አገር ዛሬ ያለችበት ቅርቃር ውስጥ መገኘቷ ላያስገርም ይችላል። የፖለቲከኞች እብደት አገር ያበላሻል። ብዙዎች አብረዋቸው ካበዱ ደግሞ የተበላሸ አገርም ይዞ መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል። የፖለቲከኞቹን እብደት ማስቆምም ሆነ ማከም ጊዜ ይወስዳል። ሕዝብ አብሯቸው እንዳያብድ ግን የአገር ሽማግሌዎች (ካሉ)፣ የኃይማኖት አባቶች (ካሉ)፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራን እና ልሂቃን ዝምታቸውን ሰብረው አገራቸውን ሊታደጉ ይገባል።
ኢትዮጵያ አደገኛውን ቁልቁለት እብደት በተጠናወታቸው ፖለቲከኞች ተገፍታ መንደርደር ከጀመረች አሥርት አመታቶች ተቆጥረዋል። የፕ/ር መስፍንን “የክህደት ቁልቁለት” የሚለውን መጽሐፍ ያላነበባችሁ አንብቡት፤ አንብባችሁ የዘነጋችሁት ድገሙት። ዛሬ ግን ይህን የክህደት ቁልቁለት የምትወርድበት ፍጥነት በብዙ እጥፍ ጨምሯል። መቆሚያው የት እንደሆነም አይታወቅም። መመለሻውም እንዲያው እሩቅ ነው። አገራችንን ከፖለቲካ እብደት መታደግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ስለሆነ ዝምታችሁን ስበሩ፣ ስለ ሰላም ሁሉም ድምጹን ያሰማ፣ የመቶ ሚሊዮኖች አገር በጥቂት የከሸፉ ፖለቲከኞች ስትጠፋ ማየት እኩል ተጠያቂነትን ያመጣል። ኢትዮጵያ ከባድ አደጋ ውስጥ እንዳለች ሁሉም ቢረዳም የአደጋውን መጠን እና የት ሊያደርሳት እንደሚችል የተረዱ ግን ጥቂቶች ይመስሉኛል። የዛሬው አደጋ የትላንቱንም ጨምሮ ስለመጣ በቀላሉ ላይመለስ ይችላል። አሁንም የአደጋውን መጠን ላልተረዳችሁ ኢትዮጵያ አስፈሪ ሁኔታ ላይ ነች። ስለአገር እና ስለሕዝብ ሲባል ሁሉም ድምጹን ያሰማ።
ሰላም ለኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic