>
5:21 pm - Saturday July 21, 6345

" ከህልሙ ግዝፈት ከፍላጎቱ ርቀት የተነሳ መከራ የማያስጎነብሰው እስክንድር...!!!"  (መስከረም አበራ )

” ከህልሙ ግዝፈት ከፍላጎቱ ርቀት የተነሳ መከራ የማያስጎነብሰው እስክንድር…!!!”

 መስከረም አበራ 

እስክንድር ሰውነቱም ጋዜጠኝነቱም ለየት ይላል! የማወቅ እና የአስተዳደግ መልካምነት መለያ የሆነውን ትህትና ተሸክሟል፡፡ እንደ ህፃን ልጅ ያለ ቅንነቱን ለማየት ከአስር ደቂቃ በላይ አይፈጅም፡፡ በአንፃሩ በራሱ እስከ መጨከን ድረስ ላመነበት ይፀናል፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያው ከማውቃቸው ሁሉ ገዝፎ ይታየኛል፡፡በማንኛውም ደረጃ ቢያቀርቡት የሚያኮራ መረዳት አለው፡፡ እውቀቱ የወለደው ትንታኔው እንደ ትንቢት ይቃጣዋል፡፡
የእስክንድር ነጋ ነፍስ በብዙ ጌጦች የተዋበች ነች፡፡ ትህትናው ሲባል እውቀቱ፤ እውቀቱ ሲባል ቆራጥነቱ፤ ይህ ሲባል ብሶት እየቆጠረ ጥርስ የማያፋጭ የይቅርታ ሰው መሆኑ ይገርመኛል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ብዙዎቻችን ትልቅ ቦታ የምንሰጠውን ስጋዊ ምቾት ችላ ማለቱ ድንቅ ነው፡፡ ሳር ቅጠሉ ስደት በሚያልምበት ዘመን የሰው ወርቅ እንደማያደምቅ አውቆ ለስደት ያለንን አመለካከት የቀየረ ሰው ነው። ዛሬ ላየነው የለውጥ ጭላንጭል እስክንድር ነጋ የከፈለው ዋጋ ውድ፣ረቂቅ እና ብዙ ገፅ ያለው ነው፡፡
እስክንድር የሚዲያ ነፃነት ፅኑ አርበኛ ነው፡፡ራሱን መሃለኛ አድርጎ ማውራት የማይወድ አዋቂ፣እዩኝ እዩኝ የማይል፣ራሱን ተራ ማድረግ የሚወድ የሃሳብ ሰው፣ ትዕቢት የማይነካካው ትሁት ስለሆነ  እንጂ ቢተረክ ብዙ ገድል የሰራ ሰው ነው፡፡ አጥንቱ እስኪሰበር ተቀጥቅጧል፡፡ “አጥንቴን ተሰብሬላችሁ” ብሎ ግን ውለታ አያስቆጥርም፡፡
የእስክንድር መልካምነት እውቅና ከመስጠት አልፎ ሽልማቶቹን ለማጋራትም ይሞክረዋል፡፡ እስርቤት በነበረበት ጊዜ አንድ ቀን ሞልቶልኝ ልጠይቀው ሄጄ ይህንኑ አስተውያለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ማንነት በነፃው ፕሬስ ባህል አጋጥሞኝ ስለማያውቅ ገርሞኝ ነው ያየሁት፡፡ የሄድኩት እሱ በደምብ ከሚያውቃቸው ሁለት ሰዎች ጋር ነበር፡፡ ስሙ ተጠርቶ ሲመጣ ፀሃያማ ፈገግታው የእስረኛ አይመስልም ነበር፡፡
እኛ የሄድንበት ሰሞን ባለቤቱ እና ልጁ ባህር ማዶ የሄዱ ሰሞን ነበር፡፡ ይህ ለእሱ ቀላል ፈተና እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ “እስኬ ለምን ሰርኬን እንድትሄድ አደረክ? አንተ እዚህ ማን አለህ? ልክ አላደረክም!” አለ አብሮኝ የነበረው ጠያቂ፡፡ “አይ አይ ለእኔ የሚሻለኝ ይሄ ነው” አለ።
መከራ የማያስጎነብሰው፤የብረት ጉልበት አንሶ የሚታየው ደፋር! የሆነበት ሁሉ የማይሰብረው ከነፍሱ ታላቅነት፣ ከህልሙ ግዝፈት ፣ከፍላጎቱ ርቀት የተነሳ ይመስለኛል፡፡በማይመጥናቸው  ወንበር ላይ ቁጢት ያሉ ገዥዎች ደግሞ ይህ አይገባቸውምና ሰላማዊው፣ጨዋው፣ትሁቱ እስክንድር ለነሱ ሞገደኛ ሽብርተኛ ነው፡፡ ቀንድ እንዳለው አውሬ ይፈሩታል፡፡ ከአእምሯቸው በላይ የሆነው ግንዛቤው የሆነ ተዓምር ፈጥሮ ከስልጣናቸው እንዳይመነግላቸው ይሰጋሉ፡፡
ሞትን ንቆ፣ወፌ ላላ ግርፋትን ያላየ፣አጥንቱ ተሰብሮ በሸክም ያልወጣ ያልገባ ይመስል፣ያልወለደ፣ የልጅ ናፍቆት ያላዋተተው ያህል ላመነበት ጉዳይ ይተጋል፡፡
Filed in: Amharic