>
5:21 pm - Monday July 21, 5862

 “ዓላማችን ወራሪውን ቡድን አቁሱሎ በመተው ሳይሆን ዳግም ለሀገራችን ስጋት እንዳይሆን አድርጎ ማስወገድ ብቻ ነው”  ( ዶ/ር ይልቃል ከፋለ)

 “ዓላማችን ወራሪውን ቡድን አቁሱሎ በመተው ሳይሆን ዳግም ለሀገራችን ስጋት እንዳይሆን አድርጎ ማስወገድ ብቻ ነው” 

ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር


የምስረታ ጉባኤውን ዛሬ ሐሙስ መስከረም 2014 ያካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት፤ ዶ/ር ይልቃል ከፋለን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መረጠ። ዶ/ር ይልቃል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተመረጡት፤ ከጥቅምት 2013 ጀምሮ ክልሉን ሲመሩ የነበሩትን አቶ አገኘሁ ተሻገርን በመተካት ነው።

አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር የአማራ ክልል መሪነትን ስልጣን የተረከቡት በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው። ዶ/ር ይልቃል በክልሉ ምክር ቤት ፊት ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግርም፤ የጦርነቱን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ተደርገው ሲሾሙ ሀዘን እና ደስታ እንደተፈራረቀባቸው የጠቀሱት ዶ/ር ይልቃል፤ ሀዘናቸው የመነጨውም በርካታ የክልሉ አካባቢዎች “ወራሪዎች እና ዘራፊዎች” ሲሉ በጠሯቸው ኃይሎች በቁጥጥር ስር በመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ እየደረሰበት ያለው “ስቃይ፣ ህመም እና ጥቃት” ልባቸውን እንደሰበረውም ተናግረዋል።

እመራዋለሁ የሚሉት ህዝብ “እየሞተ፣ እየተፈናቀለ፣ እየተራበ፣ ሀብት እና ንብረቱ እየወደመና እየተዘረፈ” ባለበት ወቅት መሾማቸው ቢያሳዝናቸውም፤ “ወራሪ” የሚሉትን ኃይል “አከርካሪ በመስበር” ህዝቡን ነጻ ለማውጣት ታጥቀው መነሳታቸው እንደሚያስደስታቸው ገልጸዋል። “በክልላችን ህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና በመላው የጸጥታ መዋቅራችን መስዋትነት እና ጀግንነት ወራሪውን ኃይል በአጭር ጊዜ በመደምሰስ ህዝባችንን ነጻ እንደምናወጣው ሙሉ እምነት አለኝ” ሲሉ ዶ/ር ይልቃል ያላቸውን ተስፋ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት አጋርተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከዚህ ቀደም በክልላቸው እና በፌደራል ባለስልጣናት እንዲሁም በወታደራዊ መኮንኖች ተደጋግሞ የሚገለጸውን ህወሓትን ሙሉ ለሙሉ የማስወገድ ሀሳብ በንግግራቸው በድጋሚ አስተጋብተዋል። “ዓላማችን ወራሪውን ቡድን አቁሱሎ በመተው ሳይሆን ዳግም ለሀገራችን ስጋት እንዳይሆን አድርጎ ማስወገድ ብቻ ነው” ብለዋል።

ዛሬ የተመሰረተው የአማራ ክልል መንግስት ቅድሚያ ትኩረት፤ በክልሉ እየተካሄደ ያለውን ውጊያ “በአጠረ ጊዜ በድል ማጠናቀቅ” እና ሰላም ማስፈን እንደሆነ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል። ክልሉ “የህልውና ዘመቻ” የሚል ስያሜ የሰጠው ተልዕኮ እንዲሳካም “የጸጥታ ኃይሉን ማጠናከር፣ ስንቅ እና ትጥቅ ማሰባሰብ እንዲሁም ተፈናቃይ ዜጎችን መደገፍ” አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ዶ/ር ይልቃል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ስልጣን ከመረከባቸው በፊት የክልሉን ትምህርት ቢሮ በኃላፊነት ሲመሩ ቆይተዋል። አዲሱ ተሿሚ የአማራ ክልል ካቢኔን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀሉት በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የስልጣን ዘመን በ2009 ዓ.ም. ነበር።

ሹመት ያገኙበትን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊነታቸውን፤ በአቶ ተመስገን ጥሩነህ እና በተሰናባቹ አቶ አገኘሁ ተሻገር ካቢኔዎች እንዳስጠበቁ ቀጥለዋል። ዶ/ር ይልቃል የአማራ ክልል መንግስትን ከመቀላቀላቸው በፊት በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ለ25 ዓመታት አገልግለዋል። በደብረ ማርቆስ ዩኒቨስርቲ ብቻ በአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንትነት እና በምክትል ፕሬዝዳትነት ከሰባት ዓመት በላይ ሰርተዋል።

አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከሕንዱ አንዱራ ዩኒቨርስቲ ያገኙት በሶሻል አንትሮፖሎጂ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም የሰሩት በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ነው። ዶ/ር ይልቃል የማስተርስ ዲግሪያቸውን የተቀበሉት፣ በታሪክ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ከተከታተሉበት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው።

የዛሬው የዶ/ር ይልቃል ሹመት፤ የአማራ ክልልን በአጭር ዓመታት በርካታ ርዕሰ መስተዳድሮች የተፈራረቁበት ክልል አድርጎታል። ከ2006 ጀምሮ ክልሉን ለአምስት ዓመታት የመሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ፤ ዶ/ር አምባቸው መኮንን የክልሉን መሪነት ስልጣን በየካቲት 2011 ተረክበው ነበር።

ለሶስት ወራት ገደማ በክልሉ የመሪነት ወንበር ላይ የቆዩት ዶ/ር አምባቸው፤ ከሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት ጋር በስብሰባ ላይ በነበሩበት ወቅት በተፈጸመባቸው ጥቃት በሰኔ 2011 ተገድለዋል። ከርዕሰ መስተዳድሩ ግድያ አንድ ወር በኋላ የአማራ ክልልን የማስተዳደር ኃላፊነት የተቀበሉት፤ በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ነበሩ።

አቶ ተመስገንም ቢሆን በክልል ርዕሰ መስተዳድርነታቸው ከአንድ ዓመት ከሶስት ወር በላይ አልቆዩም። በጥቅምት 2013 መጨረሻ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ውጊያ ተከትሎ፤ ከክልል መሪነታቸው ተነስተው የፌደራሉን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ተሹመዋል።

በእርሳቸው ምትክ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በወቅቱ የተሾሙት አቶ አገኘሁ ተሻገር ነበሩ። አቶ አገኘሁ ከሰኔ 15፤ 2011 የክልሉ አመራሮች ግድያ በኋላ በቁልፍ ቦታዎች ተመድበው ሲሰሩ ቆይተዋል። የመጀመሪያ ሹመታቸው የክልሉ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊነት ነበር።

አቶ አገኘሁ በዚህ የኃላፊነት ቦታ የቆዩት ለስምንት ወራት ብቻ ነው። የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤትን እንዲመሩ የተሰጣቸውን ሹመት በየካቲት 2012 ተቀብለዋል። ከዘጠኝ ወራት በኋላ ይህንን የኃላፊነት ቦታቸውን በመልቀቅ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል። በዛሬው ዕለት በለቀቁት የርዕሰ መስተዳድርነት ስልጣናቸው የቆዩበት ጊዜም አስራ አንድ ወራት ብቻ ነው። (

Filed in: Amharic